1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጠቅላይ ሚንስትሩ የእንታረቅ ጥሪ

ረቡዕ፣ የካቲት 13 2016

በአማራ ክልል የተፈጠርውን የሰላም እጦት በሰላም፣ በእርቅና በውይይት ለመፍታት መንግስታቸው ዝግጁ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጡ ። የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሰላም ጥሪ በመልካም ጎኑ የተቀበሉት እንዳሉ ሁሉ በጥርጣሬ የተመለከቱትም አሉ ።

https://p.dw.com/p/4chHY
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ። ፎቶ ከማኅደርምስል Seyoum Getu/DW

«ካሳም ካስፈለገ ካሳ ከፍለን፣ እንታረቅ፣ እንስማማ እኔ ችግር የለብኝም» ጠ/ሚ

በአማራ ክልል የተፈጠርውን የሰላም እጦት በሰላም፣ በእርቅና በውይይት ለመፍታት መንግስታቸው ዝግጁ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ገለጡ ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአማራ ክልል ሁሉም ዞኖች ከተውጣጡ የአማራ ክልል ተወካዮች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በአዲስ አበባ ውይይት አድርገዋል ። የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሰላም ጥሪ በመልካም ጎኑ የተቀበሉት እንዳሉ ሁሉ በጥርጣሬ የተመለከቱትም አሉ ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባለፈው ሰኞ ከአማራ ክልል ሁሉም ዞኖች ከተውጣጡ አካላላት ጋር በአማራ ክልል ወቅታዊ ጉዳይl  ላይ በአዲስ አበባ ተወያይተዋል ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ በአማራ ክልል ታጥቀው ከሚንቀሳቀሱ አካላት ጋር ለመወያየት፣ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መንግስታቸው ፈቃደኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዐቢይ፣ «ለአማራ ክልል ተደጋጋሚ ጥሪ አቅርበናል ። እንነጋገርና፣ እንወያይና በእኛ አቅም የሚመለስ ነገር ካለ መልሰን የማይመለስ ካለ ደግሞ ሕዝቡ በሚሰማው መንገድ በዚህ ጊዜ እንመልሳለን፣ እንፈታዋለን፣ ይቅርታ ብለን፣ ካሳም ካስፈለገ ካሳ ከፍለን፣ እንታረቅ፣ እንስማማ እኔ ችግር የለብኝም ። ደስ ይለኛል ። ሰላም ነው የምፈልገው ። በውስጣችን ያለውን ጉዳይ ብንፈታ ጥሩ ነው» ብለዋል፡፡

የልማት ጉድለት ያለባቸው አካባቢዎች የሚለሙበት መንገድ እንዲታይላቸው ተሳታፊዎቹ የጠየቁ ሲሆን፣ በታችኛው የአስተዳደር እርከን ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ህብረተሰቡን አለንቀሳቀስ እደረጉት እንደሆነ ተወያዮቹ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርበዋል፡፡

በመራዊው ግጭት ከ80 በላይ ሰዎች ተገድለዋል ፤ ኢሰመጉ

የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ያላግባብ ለመበልፀግ የሚሯሯጡ ሰዎችን ተጠያቂ እንዲሆኑ እያደረጉ እንደሆነ ዶ/ር ዐቢይ ምለሽ ሰጥተዋል፣ ግን ደግሞ ገና የሚቀሩ ስራዎች እንዳሉ ነው ያመለከቱት፣ የልማት ጥያቄን በተመለከተ የአንድ አካባቢ ችግር እንዳልሆነ ጠቁመው በሁሉም አካባቢዎች ያሉ የልማት ጥያቄዎች በሂደት ህብረተሰቡን በማሳተፍ የሚመለሱ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

በአማራ ክልል በርካታ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ ተወያዮቹ አንስተዋል፣ በመሆኑም እነኚህ ወገኖች ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ መንግስት እገዛ እንዲያደርግ ተጠይቋል፡፡

በአማራ ክልል በርካታ ተፈናቃዮች  የጃራ መጠለያ
በአማራ ክልል በርካታ ተፈናቃዮች እጅግ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ። ፎቶ ከማኅደርምስል Alamata City Youth League

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተፈናቃዮችን በተመለከተ ሲመልሱ፦ "የኦሮሚያ ክልል መንግስትም፣ የፌደራል መንግስትም ባላቸው አቅም ደግፈው ይቋቋሙ፣ ኮሚቴ አዋቅረው አካባቢውን ሄደው አይተው ህዝቡ ይምጡ እንቀበላቸዋልን አለ፣ ሂዱና አምጡ ተባለ፣ ሊያመጡ ሄደው ተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ያሉ ሰዎች ተፈናቃዮችን ለፖለቲካ ንግድ ስለሚጠቀሙባቸው፣ ከለከሏቸው፣ ይህ እውነት ነው፤ መጠለያ ጣቢያ የተቀመጠው ጎጃምም፣ ሰሜን ሸዋም ያለው ሰው ይመለስ፣ ከህዝቡ ከወንድሞቹ ጋር ያለውን ችግር ተጋፍጦ ይኑር፡፡”

የትግራይና የአማራ ክልሎች የይገባናል ጥያቄ የሚያነሱባቸው አካባቢዎችን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ችግሩ የሚፈታው ፣በንግግር፣ በውይይትና በነዋሪዎቹ ፍላጎት ስምምነት ብቻ መሆኑን በሚከተለው መልኩ አስቀምተዋል፡፡

"መጀመሪያ የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደ ቦታቸው እንመልስ፣ ሁለተኛ፣ ራሳቸው የወልቃይት ሰዎች በቀበሌም በወረዳም ምርጫ አካሂደው ራሳቸውን በራሳቸው ያስተዳድሩ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሰላም ስከብር፣ ሲረጋጋና ጊዜው ሲፈቅድ ደግሞ ህዝቡ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ባሉበት፣ የትግራይና የአማራ ታዛቢዎች ባሉበት ህዝበ ውሳኔ ይድርግ፤ በዚያ መንገድ ብንቋጨው አማራም እፎይ ብሎ ይኖራል፣ ትግራይም እፎይ ብሎ ይኖራል፤ በዚህ እንፍታው ብለን መቀሌን ከያዝን ከመጀመሪያው ጊዜ ጀምሮ ነው ውይይት የተጀመረው፣ ሰነድ አለ፣ አልግባባ ብንል፣ ህዝቡን አወያዩ ብለን ኮሚቴ አዋቅረን ወደ ወልቃይትና ራያ ላክን፣ ኮሚቴዎቹ ህዝብ አወያይተው መጥተው ትክክል ነው መፍትሄው ህዝቡ የሚፈልገው ሰላማዊ በሆነ መንገድ መብቱ ተረጋግጦለት፣ ወስኖ፣ ራሱን በራሱ ማስተዳደር ነው፣ የሚል ምላሽ አመጡ፣ እኔ አሁንም ያለኝ ሀሳብና ምክር ተስማምተን መኖር ይሻላል ነው፡፡”

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ። ፎቶ ከማኅደር
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ። ፎቶ ከማኅደርምስል Fana Broadcasting Corporate S.C.

ከምስራቅ ጎጃም ዞን ተወክለው በውይይቱ የተሳተፉት አቶ የሺጥላ አየለ በሰጡን አስተያየት በውይይቱ በርካታ የመሰረተ ልማት፣ የፀጥታና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ተነስተዋል ብለዋል፡፡ በክልሉ ከመንግስት ጋር ከሚዋጉ አካላ ጋር ለመወያየት በራቸው ክፍት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለፀቸውን አመልክተው፣ የክልል ባለስልጣናት፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና መላው የክልሉ ህዝብ ውይይት፣ ድርድር፣ ሰላምና እርቅ እንደሚጣ እንዲሰሩ መጠየቃቸውንም ተሳታፊው አቶ የሺጥላ ለዶይቼ ቬሌ በስልክ ተናግረዋል፡፡

የተደረገውን የሰላም ጥሪ በተመለከተ ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች አስተያየቶችን ጠይቀናል፣ የምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ ገንዳ ውሀ ከተማ አስተያየት ሰጪ "ጥሪው ተቀባይነት ያለውና ወቅታዊ ነው” ብለዋል፡፡

ከደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ ወገልጤና ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡን ነዋሪም ጥሪው መልክም ቢሆንም "የታሰሩ የአማራ ተቆርቀቋሪዎች” ያሏቸው መጀመሪያ ሊፈቱ ይገባል የሚል  ቅድመመ ሁኔታ አስቀምጠዋል፡፡

በምዕራብ ጎጃም ዞን ደንበጫ ከተማ አስተዳደር ያነጋገርናቸው አስተያየት ሰጪም ጥሪውን በአዎንታዊ መልኩ ተቀበሉት ሲሆን በውይት የሚሳተፉ አካላት እውነተኛ የህዝብ ጥያቄ ሊያቅርቡ የሚችሉ ሰዎች መሆን እንደሚገባቸው አመልክተዋል፡፡

በአማራ ክልል ከነሐሴ 2015 ዓ ም ጀምሮ በፋኖና በኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች መካከል የተጀመረው ግጭት ብዙ ሕይወትን ቀጥፎ፣ ንብረትን አውድሞ አሁንም ማቆሚያ አላገኘም፡፡ በክልሉ በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንት የአማራ ክልል ከሐምሌ 2015 ዓ ም ለ6 ወራት በሚዘልቅ የአስቸኳ ጊዜ አዋጅ ስር የቆየ ሲሆን ጊዜው ከተጠናቀቀ በኋላ ደግሞ አዋጁ ለሌላ ቀጣይ 4 ወራት ተራዝሟል፡፡

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሠ