የጋሞ እናቶች ባህላዊ የሙዚቃ ቡድን በጀርመን
ሐሙስ፣ ሰኔ 2 2014«በጀርመን ያየነዉ ነገር ሁሉ በጣም ደስ የሚል ነዉ። ሃገሩ አረንጓዴ፤ እርጥብ ሃገር ነዉ። ህዝቡም በደስታና በእንክብካቤ ነዉ የተቀበለን። ክብር ምስጋና ይድረሰዉ።»
ወ/ሮ ታደለች በላይነህ ይባላሉ። የ75 ዓመት ባለፀጋ ናቸዉ ። ወ/ሮ ታደለች ባለፈዉ ሳምንት በጀርመን ለሦስት ቀናት በተካሄደዉ በታዋቂዉ ዓለም አቀፍ የጃዝ ፊስቲቫል ላይ ከሌሎች 11 የጋሞ የሙዚቃ ማህበር ባልደረቦቻቸዉ ጋር፤ የጋሞ ብሔረሰብባህላዊ ዘፈንን አቅርበዉ፤ ብሔረሰቡን ብሎም የብሔር ብሔረሰቦች መገኛ የሆነችዉን ኢትዮጵያን በደማቁ አስተዋዉቀዋል። የአምስት ልጆች እናት እና የስምንት የልጅ ልጆች አያት የሆኑት የ 75 ዓመትዋ ወ/ሮ ታደለች፤ ከልጅ ልጆቻቸዉ እና ከልጆቻቸዉ የኑሮ ብልሃቱን ለማሸነፍ ድጋፍ ያግኙ እንጂ፤ የማገዶ እንጨት ቅጠል በመሸጥ እንደሚተዳደሩ አልደበቁም። በሙዚቃዉ ከእኩዮቻቸዉ ጋር ማህበር መስርተዉ በኢትዮጵያ የአደባባይ ዝግጅት ሲኖር፤ በየቦታዉ እየተጠሩ ባህላቸዉን ያስተዋዉቃሉ። አሁን ደግሞ ከ 11 ባልንጀሮቻቸዉ ጋር በመሆን በሰማዩ ፈረስ ዳምናዉን ጥሰዉ፤ ለሦስት ቀናት ጀርመን፤ ሞርዝ በሚባል ከተማ በየዓመቱ በሚካሄድ ዓለም አቀፍ ጃዝ ፊስቲቫል ላይ ተገኝተዉ እድምተኛዉን አስደምመዋል። መድረኩ እጅግ ዉብ እንደነበር የሚናገሩት ወ/ሮ ታደለች በጀርመን ስላዩት ስለተደረገላቸዉ አቀባበል ለመግለጽ ግን ትንሽ ቃላት ያንሳቸዋል።
«ታደለች በላይነህ እባላለሁ። 75 ዓመቴ ነዉ ። አምስት ልጆችና ስምንት የልጅ ልጆች አሉኝ። ጀርመን ዉስጥ የጋሞ ብሔረሰብ ባህላዊ ሙዚቃን አሳይተናል የህዝቡ አቀባበል እና ያደረገልን እንክብካቤ በጣም የሚደነቅ ነዉ። የጀርመን ህዝብ ምስጋና ይድረሰዉ። በአዉሮፕላን ስሄድ መጀመርያ ፈርቼ ነበር። አራት ጊዜ ነዉ አዉሮፕላን ላይ የወጣነዉ። እዝያ ስንደርስ ሃገሩ ሁሉ አረንጓዴ ነዉ። ለምለም ነዉ። አየሩም ጥሩ ነዉ። ምግቡም ተስማምቶናል። ወተትም ጠጥተናል። ስራዬ ሙዚቃ ስለነበር አልደከምኩም። መዝፈን በጉሮሮዬ ድምፅን ማዉጣት ብቻ ስለሆነ አያደክምም። ጉዞዉም አላደከመኝም። ሦስት ፈረንጆች ናቸዉ አዉሮፕላን ማረፍያ ድረስ የሸኙን። አንዱ ፈረንጅ በመሄዳችን አዝኖ አለቀሰ። ሁልጊዜ ወደ ጀርመን ብመጣ ደስታዬን አልችለዉም። »
12 የጋሞ ብሔረሰብ አባላትን በጀርመኑ ዓለም አቅፍ የጃዝ ፊስቲቫል ላይ ባህልን እንዲያስተዋዉቁ ይዞአቸዉ የመጣዉ በአዲስ አበባ የፈንድቃ ባህላዊ መድረክ መስራች እና የሃገሪቱን ባህልን በመማስተዋወቁ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ያገኘዉ የዓለም ሎሬት አርቲስ መላኩ በላይ ነዉ።
«የጋሞ ብሔረሰብ አባላቱ፤ በጣም የሚያሳዝኑ፤ በጣም ደስ የሚሉ፤ በ50 እና 75 ዓመት እድሜ ክልል ዉስጥ የሚገኙ ናቸዉ። የሚተዳደሩት የማገዶ እንጨት እና ቅጠል በጀርባቸዉ እየተሸከሙ፤ ጥጥ እየፈተሉ ነጠላ ጋቢ እየሰሩ፤ የሚተዳደሩ ሰዎች ናቸዉ። እንደገና ደግሞ በተለያዩ ፊስቲቫሎች በተለያዩ ድግሶች ላይ ሰዉ እየጠራቸዉ ዘፈን እየዘፈኑ ይተዳደራሉ። እኔም በተለያዩ ፊስቲቫሎች ላይ አሰራቸዋለሁ። ከኔ ጋር የዘፈን ሞያቸዉን ይዘዉ ሲሰሩ 15 ዓመት ሆንዋቸዋል። በጣም ጨዋ፤ ነገር የሚያቀሉ፤ ዉስብስብ ነገር የማያዉቁ፤ በጣም የሚገርሙ አይነት አስተማሪ ሰዎች ናቸዉ።»
12ቱም አዛዉንቶች ናቸዉ ። የቤተሰብ ሃላፊ ናቸዉ?
«የልጅ ልጆች ያላቸዉ ናቸዉ። ነገር ግን በዚህ የኪነ-ጥበብ ሥራቸዉ ሁሉም ሰዉ ይጠራቸዋል። ያሰራቸዋል። ያላቸዉ እዉቀት ጥልቅ ነዉ። በተለይ ሀ ፤ ሁ የሚባለዉ ዘፈናቸዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ታዋቂ ነዉ። ስታዲዮም ላይ ህዝብ በተሰበሰበበት ቦታ ላይ በተለይ ወጣቱ የሚዘፍነዉ ዘፈን ነዉ። አንዳንድ ሙዚቃ አወጣን የሚሉ ሰዎች ሙዚቃዎቻቸዉን እና ዜማቸዉን ወስደዉባቸዉ፤ ትንሽ ቀየር አድርገዉ ያወጡና፤ በነሱ ዘፈን ታዋቂ ይሆናሉ። እነሱን ግን ማመስገን ይረሳሉ። ይረሱዋቸዋል። እና ስለዚህ እንዲህ አይነቱን ዋናዉን ከምንጩ ይዞ መድረክ ላይ ሲወጣ ፤ ሃገርን ማስተዋወቅ ነዉ። እነሱንም መካስ ነዉ።»
አርቲስት መላኩ ከጋሞ ባህላዊ የሙዚቃ ቡድን ጋር ስትሰራ 15 ዓመት እንደሆን ተናግረሃል። በፈንድቃዉ መድረክህ ላይ ምንድን ነዉ የሚያቀርቡት ?
«ድምፃቸዉን እየተጠባበቁ ሲያወጡ ደስ ይላል። ሸማቸዉን ሰርተዉ ዘፈን ሲጀምር የሚሰሩትን ጋቢ ጠቅለል አድርገዉ ፌስታል ዉስጥ ከተዉ ከበሮ ያደርጉታል። በጣም ደስ ይላሉ። የአብሮነት ዉህደቱን በድምፃቸዉ በደንብ ነዉ የሚገልፁት ። ሲደመጥ በጣም ማራኪ ነዉ። ጥምቀት ፊስቲቫል ላይም በራሴ ወጭ ሆቴል ከፍዬ እነሱን እና ሌሎች ከአርባ ምንጭ የምጋብዛቸዉ አሉ አዝማሪዎችንም ጨምሪ ይዤያቸዉ እሄዳለሁ። በዓመት አንድ ጊዜ በማዘጋጀዉ ፍለጋ በተባለዉ ፊስቲቫል ላይም ሁሉን ወጭ ችዬ ይዤያቸዉ እሄዳለሁ። ሙዚቃቸዉን ያቀርባሉ። ይህን ፊስቲቫል የማካሂደዉ ሰዉ ባህሉን ይወቅ፤ ከባህሉ ይተሳሰር በሚል ነዉ። ፊስቲቫሉ የሚካሄደዉ አዲስ አበባ ዉስጥ የካ ሚካኤል ነዉ። ዘንድሮ ለስምንተኛ ጊዜ ነዉ የተካሄደዉ። ከኛ የሚጠበቀዉ በዚህ መልኩ ግዴታን መወጣት እና የጥበብን ኃይል ማሳየት ነዉ። ከዚህ በተጨማሪ ሰርግ ላይ ሰዉ እንዲጠቀማቸዉ በስጦታ መልክ ወይ እራሴ ከፍዬ ሰርግ ላይም ይሰራሉ። በጣም ጎበዞች ናቸዉ። ብዙ ነገር ያሳምራሉ»
አሁን ደሞ ወደ ጀርመን ይዘኻቸዉ መጥተሃል። እንዴት ሃሳቡ መጣልህ? እንዴትስ ቪዚ፤ ፓስፖርቱን አገኙ እንደነገርከን፤ የሙዚቃ ቡድኑ በ 50 እና በ 75 ዓመት እድሜ ክልል ዉስጥ የሚገኙ ሰዎች ናቸዉ። አልተቸገርክም?
«ጥሩ ጥያቄ ነዉ። ሰዉ ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ይመስለዋል። በመጀመርያ ደረጃ ሞርዝ ዓለም አቀፍ ፊስቲቫል፤ በጣም ትልቅ ፊስቲቫል ነዉ። ፊስቲቫሉ ሲካሄድ ከሃምሳ ዓመት በላይ ሆኖታል። ከዚህ በፊትም እዚህ ፊስቲቫል ላይ ለመካፈል መጥተን «DW» ኢንተርቪዉ አድርጎናል። እኔ እዚህ ፊስቲቫል ላይ ስመጣ ለሦስተኛ ጊዜ ነዉ። ከአዘጋጁም ጋር ተዋዉቄያለሁ። አዲስ አበባም መጥቶ አስጎብኝቸዋለሁ። የኢትዮጵያ ሙዚቃን በተመለከተ ያዉቃል። ባለፈዉ መርካቶ ብረት ከሚቀጠቅጡ ጋር ስሰራ አይቶኝ በነገሩ ተማርኮ ነበር። ብረት የሚቀጠቅጡትንም ጋሞቹንም እንዲሁም የኢትዮጵያ ጃዝ ተጫዋቾችንም ለመጋበዝ ነበር የፈለገዉ። ግን ኮቪድ ገባና ሁሉ እቅድ ተሰረዘ። ጋሞዎቹን ግን ሊረሳቸዉ አልቻለም ነበር። ከዛ በኃላ እንደገና ግብዣ ላከልኝ እና ይቅናህ አለኝ። ምክንያቱም ለነሱ ቪዛ የማግኘቱ ጉዳይ በጣም ከባድ እንደሆነ ስለሚያዉቅ ነበር። አዲስ አበባ ያለዉ የጀርመን ኤንባሲ ደግሞ ያዉቁኛል። ስለፈንድቃም ምስክር ናቸዉ። ግን በተለይ አንድ ሰዉ ቪዛ ለመስጠት በጣም ተቸገረ። ምክንያቱም ኤንባሲዉ ቪዛ ለመስጠት የሚጠይቀዉን መስፈርቶች ጋሞዎቹ ማሟላት አይችሉም። የጋብቻ ወረቀት የላቸዉም። የልደት ምስክር ወረቀት የላቸዉም። የባንክ አካዉንት ዜሮ ነዉ። ስለዚህ በምን ላግዝህ አለኝ የኤንባሲዉ ሰራተኛ። በምን ላግዝህ ምንም አያሟሉም ። ከህግ በላይ እንዴት ልስራ አለኝ። እኔ ደግሞ፤ አይ እኔ ፈንድቃን ማስያዝ እችላለሁ አልኩት። ይህ ባህልን ለማስተዋወቅ የምሰራዉ ነዉ አልኩት። ይገባኛል ግን፤ ነገሩ ከህግ በላይ ነዉ፤ ቢሆንም እስቲ የልጆቻቸዉን፤ የልጅ ልጆቻቸዉን የልደት ሰርተፊኬት አምጣ አለኝ። ሁሉም የልጆቻቸዉን የልጅ ልጆቻቸዉን የልደት ሰርተፊኬት አመጡ እና ሰጠሁ። አንዱ ግን አሁንም ማምጣት አልቻለም። ከዛም ትንሽ ቆይ አለኝ። በቀጠሮዬ ቀን ሲሄድ፤ ለሁሉም ቪዛ ተሰጣቸዉ። በጣም ይገርማል\። በጣም ደስ አለኝ። ቪዛዉን እንዳገኘሁ ፓስፖርቱን ልሰጣቸዉ ስል ፤ አንተዉ ጋር ይቀመጥ እኛ ምን ይሰራልናል። አይተነዉ የማናዉቀዉ ነገር አሉኝ።
ለማንኛዉም ፈንድቃ እየሰራ ያለዉ ገንዘብ እየከፈሉ ዉጭ ሃገር የሚቀሩትን የሚያስቀር፤ የሃገር ፍቅርን የሚፈጥር ፤ በሁለት ሃገሮች መካከል የባህል ልዉዉጥ እንዲደረግ የሚሰራ ብዙ ብዙ ምስክርነቶችን ያሳየ ነዉ። እንደሚታወቀዉ የዓለም አቀፍ ሽልማት ከየቦታዉ ነዉ የሚጎርፍልኝ። እሱ እሱ እዉቅና ጠቀመ። ከዛም በላይ፤ የነሱ የዋህነት እና ፀሎት እና ምርቃት ተጨምሮበት ሊሳካ ችሏል። እና ቪዛ እንደተሰጠ ስነግራቸዉ ማመን አልቻሉም።
ደግሞ የሚገርመዉ በጉዞ ላይ ሄደዉ እንደማያዉቁ እንደ አዲስ ሰዉ አይደሉም። በጣም በዲሲፕሊን የተሞሉ ናቸዉ። ብዙ ኮተት የሌላቸዉ፤ አመስጋኝ ናቸዉ። እንደ አንድ ሰዉ እንጂ እንደ አስራ ሁለት ሰዉ አይቼያቸዉ አላዉቅም። »
ከቪዛዉ በኃላ አዉሮፕላን ላይ ወጣችሁ። ለነሱ ደግሞ ይህ ሁኔታ ለመጀመርያ ጊዜ ነዉ። አልተደናገራቸዉም? ሰዉስ ምን አለ? ተሳፋሪዉ?
«ግራ ገባቸዉ። ግን በሥነ-ስርዓት ስለተሞሉ ነገሩ ሁሉ ቀላል ነበር። ፈረንጅ ደግሞ የሆነ ነገር መስራት ያልቻልከዉን ያሳያይል እንጂ፤ አይስቅም ወይም አይፎትትም። ቋንቋ አይቻሉ እንጂ ሁሉንም ሊረዱ ሊተባበሩ ዝግጁ ናቸዉ። እንዴ ለአንዱ ቀበቶ ሲታሰር እንዴት እንደሆነ ሳሳይ ፤ ሌላዉ ደግሞ ሌላዉን ይረዳል። እነሱም ለማወቅ ወደ ኋላ አይሉም። መጸዳጃ ቤቱን ለማየት ይነሳሉ ፤ አሳያለሁ። በጣም በሥነ-ስርዓት የተሞሉ ናቸዉ። ጀርመን ከደረስን በኋላ ሆቴል ቤት፤ መፀዳጃ ቤት አጠቃቀም አሳያለሁ። ቁልፍ አከፋፈት አሳያለሁ ።ብቻ እጅግ ዉብ ነበር።
12 የጋሞ ባህላዊ ዘፈን ቡድን በጀርመን ሞርዝ መሃል ከተማ እና በዓለም አቀፉ የጃዝ መድረክ ላይ ዝግጅታቸዉን አቅርበዋል። ከፍተኛ አድናቆት እንዳገኙ የጀርመን ሚዲያዎች እንዲሁም ጋዜጦች ዘግበዋል።
በሸማ ስራና በጥበቃ ስራ የሚተዳደሩት እና በጀርመኑ ዓለም አቀፍ የጃዝ መድረክ ላይ የቀረቡት ሌላዉ የጋሞ ሙዚቃ ቡድን አባል አቶ መኮንን ዜማ ወጆ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቃለ-ምልልስ አድርገዋል። የዘጠኝ ልጆች አባት እና የሦስት ልጆች አያት የሆኑት አቶ መኮንን፤ በጀርመን ያዩትን አረንጓዴነት ለልጆቻቸዉ ለመንገር እና ኢትዮጵያን ለማልማት እቅድ ይዘዋል።
የጋሞ የሙዚቃ ቡድን አባላት የሚያደርጉት ባህልን እና ማኅበረሰቡን የማስተዋወቅ ሥራ ይበል የሚያሰኝ ነዉ። ቃለ-ምልልስ የሰጡንን የኪነ-ጥበብ አባላት በሙሉ እያመሰገንን፤ ሙሉ ቃለ ምልልሱን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።
አዜብ ታደሰ
ኂሩት መለሰ