የጀርመንና ፈረንሳይ ስድሳ የዲፕሎማሲ ዓመታት
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 10 2015ጀርመንና ፈረንሳይ ይፋዊ የዲፕሎማሲያዊ ግኑኝነት ከጀመሩ 60 ዓመታትን አሳልፈዋል። ሁለቱም ሃገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከመጀመራቸውን በፊት ያሳለፉትን ጦርነት፤ ከዚያም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከጀመሩ በኋላ የነበሩ ታሪካዊ ፍጻሜዎችን በወፍ በረር እንቃኛለን። ከዝግጅታችን ጋር ታዋቂው የታሪክ ሙሁርና ተመራማሪ እንዲሁም በርካታ የታሪክ መጻሕፍት ደራሲ ልዑል ዶክተር አስፋወሰን አስራተ እንግዳችን ናቸው።
እንደጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር በጥር 22, 1963 ዓ.ም ጀርመንና ፈረንሳይ የዲፕሎማስያዊ ግንኙነት ለመጀመር የመሰረት ድንጋይ የሆነውን የኤሊዜ ስምምነት የተፈራረሙበት ነው። በጀርመኑ ቻንስለር አድናወር እና በፈረንሳዩ ፕረዚደን ደ ጎል የተፈረመው ይህ ስምምነት የሁለቱንም ሃገራት የጦርነት ምዕራፍ ዘግቶ ወደ አዲስ ሰላማዊ የትብብርና የወዳጅነት ምዕራፍ ያሸጋገረ ነበር። የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከመጀመሩ በፊት ጀርመንና ፈረንሳይ የነበራቸውን የጦርነት ታሪክ መጠነኛ ምልከታ እናደርጋለን።
ጀርመንና ፈረንሳይ በተለይም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ከ1871 ዓ.ም እስከ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከፍተኛ የጠላትነት መንፈስና የመተላለቅ ታሪክ ነበራቸው። ታዋቂው የታሪክ ሙሁርና ተመራማሪ ልኡል ዶክተር አስፋወሰን አስራተ እንዲህ ያስታውሱታል.
"ጀርመንና ፈረንሳይ እኤአ ከ1871 እስከሁለተኛው የዓለም ጦርነትከፍተኛ የሆነ የጠላትነት ስሜት ነበራቸው። "
በ1ኛ የዓለም ጦርነት ጀርመንና ፈረንሳይ ባደረጉት ደም አፋሳሽ ውግያ ከሁለቱም ወገን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች አልቆባቸዋል ሲሉ ልዑል ዶክተር አስፋወሰን አጫውተውናል።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነትም የሂትለር ፈረንሳይን መውረር ተከትሎ ደም መቃባቱ ቀጥሎ የብዙዎች ሕይወት የቀጠፈ ጦርነት አካሂደዋል።
ይህ በሁለቱም ሃገራት ያለማቋረጥ የቀጠለው ቁርሾ ተወግዶ በጦርነት ከመፈላለግ ወደ መተባበር ያሸጋገረች ቀን ነበረች እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ጥር 22 ቀን 1963 ዓም፤ በሁለቱም ሃገራት መካከል የኤሊዜ ስምምነት የተፈረመበት። የታሪክ ተመራማሪው ልዑል ዶክተር አስፋወሰን አስራተ
" የዛኔ የጀርመን ቻንስለር የነበሩት አድንአወርና የፈረንሳይ ፕሬዚደንት የነበሩት ዶጎል ይሄ ነገር በዚህ ከቀጠለ፤ ደም እየተቃባን መሄድ የለብንም ብለው እኤአ በ1963 ዓም የኤሊዜ ስምምnmት ተፈራረሙ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የሁለቱም ሃገት ዲፕሎማሲያዊ ግኑኝነት እየተጠናከረ መጥቷል። ከዚህ ባሻገርም የተጠናከረች አውሮፓን ለመመስረት መሰረት ጥለዋል። "
የፈረንሳዩ የያኔው ፕረዚደንት ዶ ጎል በያኔው የጀርመን የማዕከላዊ መንግስት መቀመጫ አሁን ዶይቼቬለ የሚገኝባት ቦን ከተማ ተገኝተው በማዘጋጃቤት አደባባይ ለተገኘው በሺዎች የሚቆጠር ነዋሪ ያደረጉት ንግግር የሁለቱም ሃገራት የወደፊት የጋራ ትብብርና የአውሮፓን መጠናከር ያመላከተ እንደነበር ዶክተር አስፋወሰን አጫውተውናል።
በየጊዜው የሁለቱም አገራት ግንኙነት እየተጠናከረ የአውሮፓ ሕብረትን በመመስረት የአንበሳውን ድርሻ ከመውሰዳቸውም በላይ በሕብረቱ በኩል በርካታ ዓለም አቀፋዊ ክንውኖች ፈጽመዋል እየፈጸሙም ይገኛሉ። የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን እንዲጠናከርና እስከ የሩስያ የዩክሬይን ወረራ በርካታ የኢኮኖሚ፤ ፖለቲካ ዲፕሎማሲያዊና ወታደራዊ ስራዎችን በጋራ አከናውነዋል። በሁለቱም ሃገራት እንደነበሩት ሃገረ ገዢዎች ግን ግንኙነታተቸው አንዴ በርታ አንዴ ቀዝቀዝ ማለቱን አልቀረም።
በጀርመንና ፈረንሳይ 60ኛ ዓመት የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ታሪካዊ ዳራ በመጠኑ የቃኘንበት ዝግጅታችን በዚሁ አበቃ። ማብራሪያ በመስጠት የተባበሩንን የዘወትር ተባባሪያችን የሆኑትን የታሪክ ሙሁርና ተመራማሪ ልዑል ዶክተር አስፋወሰን አስራተን እናመሰግናለን።
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
እሸቴ በቀለ