የጀርመንና አፍሪካውያን ትብብር
ሰኞ፣ ጥቅምት 7 2015የጀርመንና አፍሪካውያን ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የጀርመን ውጭ ጉዳ ሚኒስትር ዲኤታ አስታወቁ፣ ጀርመን ለጣና ፎረም የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀትልም ተመልክቷል፣ አፍሪካውያን ችግሮቻቸውን በውይይት እንዲፈቱም የአገሪቱ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታዋ አሳስበዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታዋ ካቲያ ኮይል ሰሞኑን በጣና ፎረም ከተሳተፉ እንግዶች መካከል አንዷ ናቸው፣ ሚስ ኮይል ከዶይቼ ቬሌ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት በጀርመንና በአፍሪካ መካከል የነበረው ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል፣ በጋራ ልንፈታቸው በሚችሉ ዓለም አቀፍ ቀውሶች ላይ ከአፍሪካውያን ጋር በትብብር እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል፡፡
“ በጀርመንና በአፍሪካ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት በጣም የጠበቀ ነው፣ ይህ ወደፊት ተጠናክሮ ይቀጥላል፣ ይህ ማለት ከአፍሪካውያን ጋር እውነተኛ የሆነ አጋርነት ይኖረናል ማለት ነው፡፡
ትኩረት የሚሹና በጋራ ልንፈታቸው የሚገቡ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች አሉ፣ ለምሳሌ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የሰላምና የደህንነት ጉዳዮች፣ በተለይ በአውሮፓ ያለው አስከፊ ጦርነት በአፍሪካውያን ላይ ጫናና ተፅዕኖው ከባድ እንደሆነ ሁሉም ያውቀዋል፣
ስለሆነም ዓለማችንን የተሻለችና ሰላሟ የተጠበቀ እንዲሆን ከአፍሪካውያን ጋር በጋራ እንሰራለን”
በአህጉሪቱ የሰላምና ደህንነት ዙሪያ በየዓመቱ በባህር ዳር ከተማ የሚደረገውን የጣና ፎረም ውይይት በገንዘብ የሚደግፈው የጀርመን መንግስት መሆኑን ጠቁመው ይህን ድጋፍ ጀርመን አጠናክራ እንደምትቀጥልም አመልክተዋል፡፡
“በዚህ መድረክ ላይ በመሳተፌ በእጅጉ ተደስቻለሁ፣ በአውሮፓም የሙኒክ የፀጥታ ኮንፈረንስ የሚባል አለ፣ጣና ፎረም ደግሞ የአፍሪካ የሰላም፣ የፀጥታና የደህንነት ሁኔታዎች የሚመከርበት ነው፣ ጣና ፎረምን በገንዘብ መደገፋችን በጣም ያስደስተናል፣ ይህንም አተናክረን እንቀትላለን፣ በጣና ፎረም ላይ ከበርካታ አፍሪካውያን ጋር ተገናኝቶ በአህጉሪቱ ሰላም ላይ መምከር በጣም ጠቃሚና አስደሳች ጉዳይ ነው፡፡”
“በጣም ጥሩ አጋጣሚ ነው፣ በዚህ መድረክ ጠንካራ አፍሪካዊ ሴቶችን፣ የህግ ባለሙያዎችን፣ ፖለቲከኞችንና ተመራማሪዎችን አይቻለሁ፡፡”
በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች የሚታዩ ግጭቶችንና ጦርነቶችን አፍሪካውያን በራሳቸው መፍታት እንደሚጠበቅባቸው የተናገሩት ሚስ ካቲያ ለዚህም ብሔራዊ ውይይቶችን ማካሄድ፣ ማጠናከርና ፖለቲከኞች ደግሞ ለውይይት ፈቃደኛ መሆን እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡
“አንዳንድ ችግሮች ባለባቸው አገሮች ውስጥ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ብሔራዊ ውይይት በጣም አስፈላጊ ነው፣ ሁሉም አገሮች በእርግጥ ተመሳሳይ መነሻ ላይኖራቸው ይችላል፣ ሁሉም ችግሮች የየራሳቸው ምክንያት ሊኖራቸው ስለሚችል ነው፡፡ በጀርመን መንግስት የሚደገፈው ቤርጎፍ ፋውንዴሽን ብሔራዊ ውይይት ያለውን ጠቀሜታ በተመለከተ በዚህ ፎረም ላይ የውይይት መነሻ ጽሁፍ አቅርቦ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በብሔራዊ ውይይት የፖለቲካ መሪዎች ቁርጠኛ ሊሆኑ ይገባል፣ ውይይት ሲካሄድም ሴቶችን፣ የታችኞቹን የህብረተሰብ ክፍሎች አካታች መሆን አለበት፣ የተሳካ ብሔራዊ ውይይት ወደ ተግባር ይለወጣል፣ በመጨረሻም የሚፈለገው ሰላምና መረጋጋት ይመጠል፡፡”
ኢትዮጵያን ሲጎበኙ የመጀመሪያቸው እንደሆነ የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታዋ በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር ተመኝተዋል፡፡
“ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ የአሁኑ የመጀመሪያ ነው፣ በመምጣቴ በጣም ደስ ብሎኛል፣ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የገጠማቸው ግጭትና ጦርነት ተወግዶ በሰላምና በብልፅግና የሚኖሩበት ጊዜ እንዲመጣ እመኛለሁ፡፡”
የጣና ፎረም በኮቪድና በፀጥታ ምክንያቶች ለሁለት ዓመታት ያህል ተቋርጦ ቆይቶ ሰሞኑን ከጥቅምት 4 እስከ ጥቅምት 6/2015 በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ሲወያይ ሰንብቶ ትናንት ተጠናቅቋል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ኂሩት መለሰ