የጀርመን መራኄ መንግሥት የኢትዮጵያ ጉብኝት
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 26 2015የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልትስ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ዛሬ አዲስ አበባ ገቡ። መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልትስ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከኢትዮጵያ ርእሠ ብሔር፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጋር በሁለትዮሽ ፣ አካባቢያዊ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ተብሏል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ እና ጀርመን ጠንካራ ግንኙነት ያላቸውና በብዙ የኢትዮጵያ ፈታኝ ወቅቶች ጀርመን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን የቆየች አገር ናት ተብሏል።
በሌላ በኩል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያ ላይ ችግር የሚፈጥር ነው የተባለው የሱዳን ቀውስ ክስተቱ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ደህንነት ጋር በቀጥታ የሚያያዝ ነው ተብሏል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም እንዳሉት እስካሁን 61 አገሮች 7726 ዜጎቻቸውን በኢትዮጵያ በኩል ከሱዳን ማስወጣታቸውን እና ከነዚህም 3,517ቱ ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን ገልፀዋል። የኢትዮጵያ እና የጀርመን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከተጀመረ አንድ ምዕተ ዓመት ተሻግሯል። የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ዛሬ ከቀትር በኋላ አዲስ አበባ ሲደርሱ የንግድ ተቋማት ባለቤቶችን እና ኃላፊዎች ጭምር አስከትለው ነበር። ከጀርመን ሰፊ ቁጥር ያለው ባለሃብት ስለመግባቱ የገለፁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ጀርመን የኢትዮጵያ ሰፊ የልማት አጋር መሆኗን ጠቅሰዋል። በትምህርት እና በስልጠና ከምታደርገው ሰፊ ድጋፍ ባለፈ አሁን የሰላም ስምምነት ሒደቱ በላቀ እንዲሳካ ታግዛለች፣ ለመልሶ ግንባታ ሥራዎችም ድጋፍ ታደርጋለች ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በየሁለት ሳምንቱ በተለይ በአውሮጳ ሀገራት መሪዎች እየተጎበኘች መሆኑን የጠቀሱት መለስ ይህም ከአውሮጳ ሕብረት ሃገራት ጋር የግንኙነት መሻሻል ስለመኖሩ መሳያ ነው ብለዋል። «ከመጠራጠር ወደ መተባበር እያደገ ያለ ግንኙነት ስለመኖሩ ማሳያ ነው።»
ሱዳንን በተመለከተው የመግለጫቸው ጭብጥ ጦርነቱ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያ ላይ ተጽእኖ አለው ያሉት ቃል ዐቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ጋር የሚገናኝ በመሆኑ መንግሥት ጦርነቱ በውይይት ብቻ መፈታት አለበት የሚል አቋም እንዳለው ገልፀዋል።
1 ሚሊየን ያህል ኢትዮጵያዊያን በሱዳን ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል ያሉት መለስ ጦርነቱን ተከትሎ 1469 ሱዳናዊያን ስደተኞች ሆነው ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ለስደተኞች ድንበር እንደማይዘጋ እና ያንን የማድረግ ልምድ እንደሌለውም ድንበር ዘግታለች ወይ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።
በመግለጫው ዩናይትፍ ስቴትስ ወደ ትግራይ ክልል የምትልከውን የምግብ እርዳታ ላልተወሰነ ጊዜ ማቋረጧን እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም ( WFP ) የምግብ እርዳታው ለህዝቡ እንደሚደርስ ዋስትና እስከሚሰጠው ድረስ እርዳታ ወደ ትግራይ ማቅረብ እንደሚያቆም ስለመግለፁ የተጠየቀት ቃል ዐቀባዩ የኢትዮጵያ መንግሥት እርዳታ እንደማያከፋፍል፣ ይልቁንም እርዳታ ለሚያቀርቡ አካላት የፀጥታ እና የቦታ ሁኔታዎችን እንደሚያመቻች ገልፀው የተፈፀመ ችግር ካለም ከመንግሥት ጋር የሚያያዝ ነገር እንዳልሆነ ተናግረዋል። ሆኖም ግን የቀረበውን ሁኔታ አስምልክቶ የሚደረገው ምርመራ ተገቢ ነው። እርዳታውም ለተረጂዎች መዋል አለበት ብለዋል።
ሰሎሞን ሙጬ
ሸዋዬ ለገሠ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር