1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን መራኄ መንግሥት የአፍሪቃ ጉብኝት

ማክሰኞ፣ ግንቦት 16 2014

የጀርመን ፓርላማ ባለፈው ዓርብ የሀገሪቱ ጦር የአውሮጳ ኅብረት ተልዕኮ እንዲያበቃ ወስኗል። የኒዠር ወታደራዊ ተልዕኮን አስፈላጊ ግን ደግሞ አደገኛ ያሉት ሾልዝ በእቅዱ መሠረት ተልዕኮው በጎርጎሮሳዊው 2022 መጨረሻ የሚያበቃ ቢሆንም ሊራዘም እንደሚችል ጠቁመዋል። የኒዠር ፕሬዝዳንት ሞሀመድ ባዙም ቆይታው መራዘሙን በደስታ ተቀብለዋል።

https://p.dw.com/p/4BoEj
Südafrika Besuch des Bundeskanzlers Olaf Scholz
ምስል Siphiwe Sibeko/REUTERS

የሾልዝ የአፍሪቃ ጉብኝት


ሥልጣን ከያዙ 6 ወር ሊሆናቸው ጥቂት ቀናት የቀሯቸው የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ የሦስት የአፍሪቃ ሀገራት ጉብኝታቸውን ባለፈው እሁድ በምዕራብ አፍሪቃዊቷ ሀገር ሴኔጋል ነበር የጀመሩት። በማግስቱ ሰኞ ኒዠር ከሄዱ በኋላ ትናንት ማታ ደግሞ ደቡብ አፍሪቃ ገብተዋል። ሾልዝ መራኄ መንግሥት ከሆኑ በኋላ በአፍሪቃ ጉብኝት ሲያደርጉ የዚህ ሰሞኑ ጉብኝታቸው የመጀመሪያው ነው። የቀድሞዋ የጀርመን መራኄ መንግሥት አንጌላ ሜርክል አፍሪቃ ለአውሮጳ አስፈላጊ ናት የሚል አቋም ነበር የሚያራምዱት። ዛሬ ደቡብ አፍሪቃን በመጎብኘት ላይ ያሉት ሶሻል ዴሞክራቱ ፖለቲከኛ ሾልዝ ለዶቼቬለዋ ጋዜጠኛ ሚሻኤላ ክዩፍነር በሰጡት ቃለ ምልልስ በሦስቱ የአፍሪቃ ሀገራት ጉብኝት ያደረጉበትን ምክንያት አስረድተዋል። በአጠቃላይ የአፍሪቃና የአውሮጳ ግንኙነት ለአውሮጳ ህልውና  ወሳኝ መሆኑንም  ተናግረዋል።
«አፍሪቃ ከአውሮጳ አጠገብ የምትገኝ ክፍለ ዓለም ናት። ስለዚህ ከአፍሪቃ ሀገራት ጋር በሙሉ፣በጣም ጥሩ በሆነ ግንኙነት መሥራታችን ለህልውናችን አስፈላጊ ነው። ከዚሁ ጋርም ከዓለማችን ዴሞክራሲያዊ መንግስታትም ጋር  ግንኙነቶቻችንን ማጠናከርም ጠቃሚ ነው። ዴሞክራሲ፣ የሕግ የበላይነት እና ሌሎች ለእኛ አስፈላጊ የሆኑ ጥያቄዎች «ምዕራባውያን ሀገራት» ተብሎ ከሚጠራው ጋር የሚገናኝ ብቻ አይደለም። ከዚህ ሌላ በዓለማችን የሚገኙ ሌሎች ሀገራትን መቃኘትም አስፈላጊ ነው። ስለዚህ ደቡብ አፍሪቃ ዴሞክራሲያዊ ሀገር ናት።ሴኔጋል ኒዠርም እንዲሁ። ለዚህም ነው እነዚህን ሀገራት የጎበኘሁት ።ከነዚህ ሀገራት ጋር አብረን መስራት መቀጠላችንም ጠቃሚ ነው የምለውም ለዚህ ነው። ብንተባበር ዓለማችን ጥሩ መጻኤ እድል ይኖራታል። በአሁኑ ጊዜም በዓለማችን በተለያዩ ሀገራት መካከል ጥሩ ትብብርን እውን ማድረግ አለብን።»
 ሾልዝ የጉብኝታቸው መጀመሪያ ባደረጓት በሴኔጋል ካተኮሩባቸው ጉዳዮች ዋነኛው የኃይል አቅርቦት ነበር። ጀርመን በአሁኑ ጊዜ ከሩስያ ጋዝ ጥገኝነት ለመላቀቅ ጥረት በማድረግ ላይ ካሉ የአውሮጳ ሀገራት አንዷ ናት። የሴኔጋል ጉብኝታቸውም የዚህ ጥረት አንዱ አካል ነው። የዩክሬኑ ጦርነት ላስከተለው የጋዝ አቅርቦት ቀውስ መፍትሄ ለማግኘት ሾልዝ የተጓዙባት ሴኔጋል ፣ ከሞሪታንያ ጋር በሚያዋስናት ድንበር ላይ  ሰፊ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት አላት ተብሎ ይታመናል። ሾልዝ ከትናንት በስተያ ዳካር ሴኔጋል ውስጥ ከሴኔጋል ፕሬዝዳንት  ማኪ ሳሊ ጋር ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ በአሁኑ ጊዜ  በጉዳዩ ላይ በሁለቱ ሀገራት መካከል በባለሞያዎች ደረጃ የሃሳብ ልውውጦች እየተካሄዱ መሆኑን ገልጸው መንግሥታቸው ውይይቱ ውጤት እንዲያመጣ ምኞቱ መሆኑን አስታውቀዋል። ሾልዝ ሴኔጋል የሚገኙ ታዳሽ የኃይል ምንጮችን ከመጎብኘታቸው አስቀድሞ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት የጀርመን የኃይል ፍላጎት ከፍተኛ ነው። ሀገራቸው በተለይ ለሴኔጋል የታዳሽ ኃይል ማመንጫዎች ድጋፍ ማድረጓን እንደምትቀጥልም በዚሁ ወቅት ቃል ገብተዋል።
« የኃይል ትብብርን በሚመለከት ጥያቄው ሰፊ ነው። ትኩረቱ ተዳሽ የኃይል ምንጭ ላይ ነው ።የሴኔጋል ፕሬዝዳንት በዚህ ረገድ ያነሱት የማከመቻ አቅምን፣ ከፀሐይና ከንፋስ የሚገኝ ኃይልን የተመለከቱ ጉዳዮችን ነው።አዎ ሴኔጋል ያላትን የተፈጥሮ ጋዝ ሀብት በመጠቀም ረገድ ትብብር ማድረግንም የሚመለከት ነበር ።  ከቅርብ ጊዜያት አንስቶ ሴኔጋል ታዳሽ ኃይሏን በፍጥነት እያስፋፋች።ዲያስ የሚገኘውን የፀሐይ ኃይል ማመንጫ እጎበኛለሁ። ይህ የኃይል ማመንጫ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚረዳ ለተፈጥሮ ጥበቃ የሚመረጥ የኃይል አቅርቦት ነው። በዚህ ረገድ በቡድን ሰባት ማዕቀፍና ሁለተኛው ትብብር በሚባለው ማዕቀፍ ስር ሴኔጋልን መደገፋችንን እንቀጥላለን። 
የሴኔጋሉ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳልም ኃይልን በሚመለከት ሁለቱ ሀገራት የሚያደርጉት ስምምነት ትኩረት በተለይ ተዳሽ የኃይል ምንጮች ላይ መሆኑን አረጋግጠዋል።በዚህ የኃይል ዘርፍ የሚደረገው ትብብርም ልዩ ልዩ ድጋፎችን የሚያካትት መሆኑን ነው የገለጹት ።
«ዛሬ ትብብሩ የሚያተኩረው ለታዳሽ የኃይል ምንጮች በሚደረግ ድጋፍ ፣ከምንም በላይ ደግሞ ከፀሐይ ኃይል በሚያስገኝ  ቴክኖሎጂ እንዲሁም በኃይል አቅርቦቱ ቅልጥፍና እና በባለሞያዎች ስልጠና ላይ ነው።»  
በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን በእጅጉ የጨመረው የነዳጅ ዘይት ዋጋ እንዲወርድ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው።ከመካከላቸው አንዱ ዩናይትድ ስቴትስና የአውሮጳ ኅብረት በጋራ የጀመሩት ጥረት ነው። ሾልዝ ዛሬ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ለዶቼቬለ ጋዜጠኛ ሚሻኤላ ክዩፍነር በሰጡት ቃለ ምልልስ እንዳስረዱት ጥረቱ የነዳጅ ዘይት ዋጋ እንዲወርድ ለማድረግ ይረዳል ተብሎ ይታመናል።
«የነዳጅ ዘይት ዋጋን ስንመለከት በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ይገጥመናል። በነዳጅ ዋጋ ላይ ድጎማ ማድረጉ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃም ተግባራዊ ሊሆን እንደማይችል ግልጽ ነው።ሆኖም የጋዝና የነዳጅ ዘይት አቅርቦትን መጨመር መጀመር አስፈላጊ ነው።ለዚህም በአሁኑ ጊዜ በዚህ ጉዳይ ላይ ከነዳጅ ዘይትና ጋዝ አምራች ሀገራት በምናደርጋቸው ውይይቶች የምርታቸውን መጠን እንዲጨምሩ ለማሳመን እየሞከርን ነው። ይህም ለዓለም ገበያ እገዛ ያደርጋል።  
ሾልዝ ከሴኔጋል ቀጥሎ የጎበኟት ኒዠር የጀርመን ወታደሮች  ስልጠና የሚሰጡባት ሀገራት ናት።
ስልጠናውም በሳህል ሀገራት የአሸባሪዎች  ጥቃቶችን ለመካላከል የተመሰረተው በአውሮጳ ኅብረት «የጋዝል ተልዕኮ» ስር የሚካሄድ መርኃ ግብር ነው። ሾልዝ ትናንት ቲሊያ ኒዠር በሚገኘው ወታደራዊ ጦር ሰፈር የኒዠር  ልዩ ኃይሎችን በማሰልጠን ላይ የሚገኙ የጀርመን ባሕር ኃይል ኮማንዶዎችን ጎብኝተዋል። በዚህ  ተልዕኮ ቁጥራቸው 200 የሚጠጋ የጀርመን ወታደሮች ተካፋይ ናቸው ። ሾልዝ በጉብኝቱ  ወቅት  «በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ተልዕኮውን በማሳካት ላይ ላለው ለጀርመን ጦር አድናቆታቸውን ገልጸዋል።ተልዕኮው ስኬታማ ነውም ብለዋል። 
« ጀርመንና ኒዠር በጋዝል ዘመቻ ስለሚጋሩት ተግባር ተነጋግረናል። የተገኘውን ስኬት በዓይኔ አይቻለሁ። በጣም በጣም ጥሩ የሆነውን የቅርብ ትብብሩንም እንዲሁ ተመልክቻለሁ። ትልቅ ስኬት ነበር።»
የጀርመን ፓርላማ ባለፈው ዓርብ የሀገሪቱ ጦር የአውሮጳ ኅብረት ተልዕኮ እንዲያበቃ ቢወስንም የጀርመን ጦር ለኒዠር ወታደሮች የሚሰጠው ስልጠና ግን እስከ ጎሮጎሮሳዊው 2022 መጨረሻ ድረስ ይቀጥላል ተብሏል። ሆኖም 
የኒዠር ወታደራዊ ተልዕኮን አስፈላጊ ግን ደግሞ አደገኛ ያሉት ሾልዝ  በእቅዱ መሠረት ተልዕኮው በጎርጎሮሳዊው 2022 መጨረሻ የሚያበቃ ቢሆንም ሊራዘም እንደሚችል ጠቁመዋል። የኒዠር ፕሬዝዳንት ሞሀመድ ባዙም ትብብሩ ውጤታማ እንደነበር ከሾልዝ ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
« የኒዠር ልዩ ኃይል የሚሰለጥንበትን ይህን ተልዕኮ እንዴት ማራዘም እንደሚቻል አብረን እንድናጠና የጀርመን መራኄ መንግሥትን ጠይቄያቸዋለሁ። ይህ ጦራችን ለሌሎች አጋሮች እንደ ፍኖተ ካርታ የሚያቀርበው ስልጠና ነው። በጋራ ለሰራነውለሌሎች አጋሮች እንደ አርአያ ልናሳይ በምንችለው  በዚህ  ፕሮጀክት መሳካት እንኳን ደስ አለዎ ለማለት እፈልጋለሁ። »
ሞሀመድ ባዙም በበኩላቸው የጀርመን ወታደሮችን የኒዠር ቆይታን የማራዘም ሀሳብን በደስታ ተቀብለዋል።ይሁን የሳህል ጸጥታ ጉዳይ አሁን የአውሮጳ ኅብረት እንቅልፍ መንሳቱ ቀጥሏል። በማሊ በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን የያዘው ወታደራዊ ኃይል ዋግነር ከሚባለው የሩስያ የግል ቅጥረኛ ተዋጊ ድርጅት ጋር ቅርብ ግንኙነት በመመስረት በማሊ የፈረንሳይ ሰላም ማስከበር ተልዕኮን እንዲተካ ካደረገ በኋላ የማሊ መንግሥት ከምዕራባውያን ጋር ተቃቅሯል። ሾልዝ ከዶቼቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሰዎችን ለስደት የሚዳርግ አለመረጋጋት ባለበት በሳህል አካባቢ ከማሊው መፈንቅለ መንግሥት በኋላ አሸባሪዎችን ለመከላከል የሚሰጠው ድጋፍ  ለአጥፊው ወገን ሊውል መቻሉ ምን ያህል አስጊ ነው ተብለው ተጠይቀው ነበር። ሾልዝ ድጋፉ መቀጠሉን ገልጸው ሆኖም የሩስያ ወታደሮች በማሊው ውጊያ መካፈላቸ  ተቀባይነት እንደሌለው አስረድተዋል። 
«የተመድ በሳህል የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በተለይም ሚኑስማ የተባለውን ተልዕኮ እደግፋለን። ይህ አካባቢውን ለማረጋጋት ጥሩ ነው። ይሁንና በማሊ የሩስያ ወታደሮች በሚሰጡት ድጋፍ የሚካሄድ ህዝቡ ላያ ያነጣጠረ ውጊያ ያለበትን ሁኔታ መቼም ቢሆን እንደማንቀበል በጣም ግልጽ አድርገናል። ስለዚህ በማሊ ወደ ቀደመው ዴሞክራሲያዊ አመለካከት መመለስ አስፈላጊ ነው።»

Niamey, Niger | Kanzler Scholz besucht den Niger
ምስል Michael Kappeler/dpa/picture alliance
Senegal Besuch Kanzler Scholz | PK mit Präsident Macky Sall
ምስል Michael Kappeler/dpa/picture alliance
Südafrika Interview Bundeskanzler Olaf Scholz
ምስል Dirk Thiele/DW

 የኒዠር ጉብኝታቸውን ትናንት ያጠናቀቁት ሾልዝ ዛሬ ደቡብ አፍሪቃ ናቸው ። የሾልዝ የደቡብ አፍሪቃ ጉብኝት አንዱ ትኩረት ለዩክሬኑ ጦርነት ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍን ማጠናከር ነው ። ሩስያ ዩክሬንን መውረሯን ለማውገዝ በተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ሀገራት ድምጽ በተሰጠበት ወቅት ደቡብ አፍሪቃ ድምጻቸውን ካቀቡት ሀገራት አንዷ ናት። የዚህ ምክንያቱ የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራሞፎሳ ዛሬ ፕሪቶሪያ ውስጥ እንደተናገሩት ሀገራቸው ከሞስኮ ጋር ያላት ታሪካዊ ግንኙነት ነው። ራማፎሳ ከሾልዝ ጋር ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት ምክንያቱ ሶቭየት ኅብረት ለደቡብ አፍሪቃውያን ጸረ አፓርታይድ ትግል የሰጠችው ድጋፍ መሆኑን ተናግረዋል። ራማፎሳ የአውሮጳ ኅብረት ሞስኮ ለመቅጣት በተከታታይ የጣላቸው ከባድ ማዕቀቦች እንደ ራማፎሳ ተጨማሪ ጥፋቶችን አስከትሏል ባይ ናቸው። በዚህ የተነሳም በሩስያ ወረራ ላይ  አቋም ያልያዙ ሀገራት በሩስያ ላይ በተጣለው ማዕቀብ ምክንያት እየተሰቃዩ ስለሆነ የአፍሪቃ ኅብረት በጉዳዩ ላይ እንዲነጋገር ጠይቀዋል። ነገ የአፍሪቃ ጉብኝታ,ውን የሚያበቁት ሾልዝ ሾልዝ በበኩላቸው በዩክሬኑ ጦርነት የደቡብ አፍሪቃ አቋም ላይ ለመነጋገር እድሉን በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸው ሆኖም ሩስያ በጦርነቱ ዓለም አቀፍ ድንበሮችን በኃይል ለመጣስ ያደረገችው ሙከራ ተቀባይነት የለውም ብለዋል። ሾልዝ የጎበኙዋቸው  የወቅቱ የአፍሪቃ ኅብረት ሊቀ መንበር ሴኔጋል እና ደቡብ አፍሪቃ ሰኔ መጨረሻ ጀርመን በሚካሄደው የቡድን ሰባት ጉባኤ ላይ ይካፈላሉ።

Tillia, Niger | Kanzler Scholz besucht den Niger
ምስል Michael Kappeler/dpa/picture alliance

ኂሩት መለሰ 

ሸዋዬ ለገሠ