በሰሜን ሸዋ ዞን በተፈጸመ የድሮን ጥቃት አስር ሰዎች መገደላቸውን የዐይን እማኞች ተናገሩ
ሐሙስ፣ ኅዳር 27 2016በአማራ ክልል በተለይ በሰሜን ሸዋ እና በወሎ አካባቢዎች የፋኖ ታጣቂዎችን ዒላማ አድርገው ሰሞኑን ተሰነዘሩ በተባሉ የድሮን ጥቃቶች ንጹሃን ዜጎች ጭምር መገደላቸው ተነገረ። ደቡብ ወሎ ዞን ከወገልጤና ከተማ ወጣ ባለ መንደር ውስጥ ታጣቂዎች ላይ ከተሰነዘረ ጥቃት በኋላ ቁስለኞችን ለማንሳት በተሰባሰቡ ንፁሃን የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ተጨማሪ የድሮን ጥቃት ተሰንዝሮ ብዙ ሰዎች መጎዳታቸውን ድርጊቱ ሲፈፀም መመልከታቸውን የገለፁ አንድ ሰው ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል በሰሜን ሸዋ ዞን ህዳር 25 ቀን መንዝ እና መርሃቤቴን በሚያገናኝ ሥፍራ ላይ ታጣቂዎችን ለማጥቃት የተሰነዘረ የድሮን ጥቃት የግጭቱ ተሳታፊ ያልነበሩን ጨምሮ አሥር ሠዎችን መግደሉን ያነጋገርናቸው ገልፀዋል።ስለ ጉዳዩ በአማራ ክልል የተደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲመረምር የተቋቋመው መርማሪ ቦርድም ይሁን መከላከያ ሠራዊት ያሉት ነገር የለም።
በአማራ ክልል ንፁሐን በድሮን ድብደባ ተገድለዋል - ኢሰመኮ
ኢሰመኮ ትናንት ባወጣው መግለጫ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና ኦሮሚያ ክልሎችን ጨምሮ በአማራ ክልል "በሲቪል ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለው ግድያ፣ አካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና መፈናቀል የፌዴራል መንግሥቱና የየክልሎቹ መንግሥታትን አፋጣኝ፣ ተጨባጭና ዘላቂ መፍትሔ የሚሻ ነው" ሲል ገልጿል።
የድሮን ጥቃቶች የት የት ተፈፀሙ?
በአማራ ክልል በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ መካከል ለወራት በቀጠለው የትጥቅ ግጭት ምክንያት ከሰሞኑ ታጣቂዎችን ብቻ ሳይሆን ንጹሃንን ጭምር እየጎዱ ያሉ የድሮን ጥቃቶች በተለይ በሰሜን ሸዋ እና ወሎ አካባቢዎች መሰንዘራቸው ተሰማ። በሰሜን ወሎ ዞን ተፈፀመ የተባለውን ሰሞንኛ የድሮን ጥቃት አደጋው የደረሰበት ሥፍራ ነዋሪ ነግረውናል።
ሌላኛው የአይን እማኝ እንደሚሉት ከሰሞኑ ባገረሸው ግጭት እና ያንን በተከተለ ጥቃት የሞቱት እንዳሉ ሆኖ የተጎዱ ሌሎች ሰዎች የህክምና እርዳታ ማግኘት አልቻሉም።በተመሳሳይ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ባለፈው ሳምንት በተቃጣ የድሮን ጥቃት አንድ ቦታ ላይ ሥር ሰዎች ሲሞቱ ፣ ምን ያህል እንደሆኑ በውል ያልታወቁ ሰዎች የተገደሉበት ሦስት የድሮን ጥቃት መሰንዘሩንም ያነጋገርናቸው ሰው ገልፀዋል።
የአማራ ክልል ጦርነት የፈጠረው ችግር
ምንም እንኳም መንግስት መግለጫውን ባይቀበለውም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከወር በፊት ድሮንን ጨምሮ በከባድ መሣሪያዎች በተሰነዘሩ ጥቃቶች በሲቪል ሰዎች ላይ ሞት እና የአካል ጉዳት መድረሱን አስታውቆ ነበር ።በክልሉ በሁለቱ አካላት መካከል ግልጽ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ የእንቅስቃሴ ጎደቦች ፣ የኢንተርኔት መቋረጥ እና ሌሎች እርምጃዎች ተወስደዋል። ከትጥቅ ግጭቱ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ሲቪል ሰዎች እና የሲቪል የንግድ እና የመሠረተ ልማት ተቋማት ላይ ዝርፊያ፣ የማሳ ላይ ሰብል ውድመት ጨምሮ በሲቪል ሰዎች፣ በሕዝብ እና በመሠረተ ልማት ላይ ጉዳት ደርሷል። በክልሉ የንግድ እና የማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ በፈጠረው ተጽዕኖ ነዋሪዎች ለአቅርቦት እጥረት እና ለዋጋ ንረት እንዲሁም ለተያያዥ ችግሮች መዳረጋቸውን የሚያሳዩ ዘገባዎች ወጥተዋል።
የድሮን ጥቃት በመቀሌ ከተማ
ኢሰመኮ ትናንት ባወጣው መግለጫ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና ኦሮሚያ ክልሎችን ጨምሮ በአማራ ክልል "በሲቪል ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለው ግድያ፣ አካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና መፈናቀል የፌዴራል መንግሥቱና የየክልሎቹ መግሥታትን አፋጣኝ፣ ተጨባጭና ዘላቂ መፍትሔ የሚሻ ነው" ሲል ገልጿል። ስለ ጉዳዩ በአማራ ክልል የተደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲመረምር የተቋቋመው መርማሪ ቦርድም ይሁን መከላከያ ሠራዊት ያሉት ነገር የለም።
ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ