1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ኢትዮጵያ ልማት ማህበር በጀርመን

ረቡዕ፣ ኅዳር 28 2015

የደቡብ ኢትዮጵያ ልማት ማህበር በጀርመን ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች ያሰባሰባቸውን ከ 15 ሚልዮን ዩሮ በላይ የሚገመቱ ልዩ ልዩ የህክምና እና የትምህርት ቁሳቁሶችን በኢትዮጵያ ለሚገኙ ሆስፒታሎችና ዩኒቨርሲቲዎች በእርዳታ መለገሱን ገለጸ::

https://p.dw.com/p/4KSRP
Deutschland Frankfurt a.M. | Treffen Southern Ethiopia Region Development Community
የደቡብ ኢትዮጵያ ልማት ማህበር በጀርመን የዕውቅናና ምስጋና መርሃ-ግብርምስል Endalkachew Fekade/DW

የደቡብ ኢትዮጵያ ልማት ማህበር በጀርመን የዕውቅናና ምስጋና መርሃ-ግብር

የደቡብ ኢትዮጵያ ልማት ማህበር በጀርመን ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች ያሰባሰባቸውን ከ 15 ሚልዮን ዩሮ በላይ የሚገመቱ ልዩ ልዩ የህክምና እና የትምህርት ቁሳቁሶችን በኢትዮጵያ ለሚገኙ ሆስፒታሎችና ዩኒቨርሲቲዎች በእርዳታ መለገሱን ገለጸ:: የማህበሩ10ኛ ዓመት ዓመታዊ ስብሰባ በዛሬው ዕለት ፍራንክፈርት ከተማ በሚገኘው ሂልተን ሆቴል በተከናወነበት ወቅት ማህበሩ ላለፉት ዓመታት ሲያደርግ በነበረው እንቅስቃሴ ከፍተኛ ድጋፍ ላበረከቱ አባላቱና የተለያዩ ግለሰቦች የዕውቅናና የምስጋና ሽልማት አበርክቷል:: የመርሃ ግብሩ ተጋባዥ እንግዳ በጀርመን የኢትዮያያ ኤምባሲ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን ማህበሩ እስካሁን በኢትዮጵያ ያከናወናቸውን ከፍተኛ የእርዳታ እንቅስቃሴዎች አድንቀው በመላው ዓለም የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያንም ሀገር እና ወገናቸውን በተመሳሳይ መልኩ እንዲረዱ ጥሪያቸውን አቅርበዋል::  

Deutschland Frankfurt a.M. | Treffen Southern Ethiopia Region Development Community
የደቡብ ኢትዮጵያ ልማት ማህበር በጀርመን የዕውቅናና ምስጋና መርሃ-ግብርምስል Endalkachew Fekade/DW

 በኢትዮጵያ ለሕጻናት ለጤናና ለትምህርት ተቋማት የተለያየ የሰብዓዊ ድጋፍ አገልግሎት ለማበርከት እንደ ጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር በ 2012 ዓ.ም ጀርመን ነዋሪ በሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ ወዳጆችና የውጭ ሃገራት ዜጎች የተመሰረተው የደቡብ ኢትዮጵያ ልማት ማህበር በጀርመን በዛሬው ዕለት ፍራንክፈርት ከተማ በሚገኘው ሒልተን ሆቴል ባዘጋጀው ዓመታዊ ስብሰባ እስከዛሬ ማህበሩ ባከናወናቸው እንቅስቃሴዎች ልዩ ልዩ ድጋፍ ሲያበረክቱለት ለቆዩ አባላቱና ግለሰቦች የዕውቅናና የምስጋና ሽልማት አበርክቷል::

በዲያስፖራ ከተመሰረቱ ማህበራት መካከል የጎላ እንቅስቃሴ ማከናወኑ የሚነገርለት ሴዳ ባለፉት አስር ዓመታት ከ 15 ሚልዮን ዩሮ በላይ ዋጋቸው የሚተመን ልዩ ልዩ የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶችን ለህክምና ተማሪዎች እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ወድና አዳዲስ የህክምና ትምህርት መማሪያ መጻህፍትን በኢትዮጵያ የደቡብ ክልል ሆስፒታሎችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የለገሰ ሲሆን ዓለም የደረሰበት የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር በኢትዮጵያ እንዲጠናከር እና የሃገሪቱን የባህልና የቱሪስት መስህቦችም ለውጭ ዜጎች በማስተዋወቅ ታላላቅ ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝ የማህበሩ ዋና ሰብሳቢ ወይዘሮ ዘመናይ ማትኒያክ ለዶይቼ ቨለ "DW" ገልጸዋል:: በ 2014 ዓ.ም በዴንማርክ ኮፐንሃገን ዩኒቨርሲቲ የህክምና ተማሪ ከነበሩ ኢትዮጵያዊ የተገኙ ዋጋቸው ከ 50 ሺህ ዩሮ በላይ የሚገመቱ በርካታ ለህክምና ትምህርት ተማሪዎች መማሪያ የሚውሉ አዳዲስና ውድ መጽሃፍትን ለሶስት ዩኒቨርሲቲዎች በመለገስ እንቅስቃሴውን የጀመረው ሴዳ "ሃኪሞች ለኢትዮጵያ" ከተባለ ቡድን በዕርዳታ ያገኘውን 150 ሺህ ዮሮ ግምት የሚያወጡ የሆስፒታል አልጋዎችን የላብራቶሪ መሳሪያዎችን የልብስ ማጠቢያና ማድረቂያ ማሽኖችን የህሙማን መመርመሪያ መሳሪያዎችን እና የአልትራ ሳውንድ ማሽኖችን ሌሎችንም የህክምና ቁሳቁሶች ለይርጋዓለም ሆስፒታል በ 2015 ዓ.ም ማበርከቱም ተገልጿል:: ሌላው ማህበሩ ካከናወናቸው ታላላቅ ፕሮጀክቶች መካከል ጎልቶ የሚጠቀሰው በ 2017 ዓ.ም በህክምና መስጫ መሳሪያዎች እጥረት ሳቢያ ግንባታው ተጠናቆ የስራ እንቅስቃሴ ላልጀመረው የወልቂጤ ሆስፒታል ከ 15 ሚልዮን ዩሮ በላይ የሚገመት በርካታ የህክምና መስጫ መሳሪያዎች የተደረገው ድጋፍ መሆኑን አመራሮቹ ይገልጻሉ:: ሆስፒታሉ ከ 75 በመቶ በላይ የሚገመተውን ቁሳቁስ ማህበሩ ካሟላለት በኋላ እንቅስቃሴውን ጀምሯል:: በጌድዖ እና ጉጂ ማህበረሰብ መካከል በተከሰተው የእርስ በእርስ ግጭት ለተፈናቀሉ ወገኖችና ለሀገር መከላከያ ሰራዊቱም ማህበሩ የአቅሙን ድጋፍ ማበርከቱን ወይዘሮ ዘመናይ አስረድተዋል::

Deutschland Frankfurt a.M. | Treffen Southern Ethiopia Region Development Community
የደቡብ ኢትዮጵያ ልማት ማህበር በጀርመን የዕውቅናና ምስጋና መርሃ-ግብርምስል Endalkachew Fekade/DW

ማህበሩ ከጀርመን የተለያዩ ተቋማት የሚለገሰውን እና የሚገዛቸውን የህክምና መሳሪያዎችና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች ሃገርቤት ከላከ በኋላ የወደብ ነጻ የጉምሩክና ሌሎችም የቢሮ ፎርማሊቲዎች በፍጥነት በመጨረስ ለህክምና ተቋማት ለተረጂዎች እና ለድርጅቶች ተደራሽ እንዲሆኑ ለማስቻል አዋሳ ከሚገኘው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ልማት ማህበር ጋር በቅርበትና በትብብር መስራቱም ስራውን አቀላጥፎልናል ብለዋል ወይዘሮ ዘመናይ:: ዛሬ በሂልተን ሆቴል በተዘጋጀው ዓመታዊ የምስጋናና ዕውቅና መርሃግብር ላይ የተካፈሉ ልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አደረጃጀቶች አባላት እና የማህበሩ ድጋፍ ሰጪ የውጭ ዜጎችም ሲዳ የሚያስመሰግን እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን መስክረዋል:: ጀርመናዊው ቴዲ ማርትኒያክ አንዱ ናቸው::

"ባለፉት 10 ዓመታት ማህበሩ ከዴንማርክ ኮፐንሃገን ዩኒቨርሲቲ የተገኙ የህክምና መማሪያ መጻህፍትን ለግሷል:: ለይርጋዓለም እና ሌሎችም ሆስፒታሎች አያሌ የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶችን ከፍተኛ ዲሲፒሊን በተሞላበት ሁኔታ ወደ ኢትዮጵያ እንዲጓጓዝ ተደርጓል::በእኔ በኩል ከውጭ ተቋማትና ድርጅቶች ጋር የምናደርገው የስራ እና የእርዳታ ግንኙነት የተሳለጠ እንዲሆን የበኩሌን እገዛ እያበረከትኩ እገኛለሁ"

ማህበሩ በዋናነት የሃገር ተረካቢ በሆኑ ሕጻናት ጉዳይ እንዲሁም በጤናና በትምህርት ዘርፎች በዲያስፖራ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ምሳሌ እና አርዓያ የሚሆኑ ተጨባጭ የድጋፍ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱ ሊበረታታና ሊደገፍ ይገባዋል ያሉንም ነበሩ::

"ማህበሩ ደቡብ ኢትዮጵያ የሚል ስያሜ ቢኖረውም ብሄርና ሃይማኖት እና ፖለቲካ ሳይገድበው በመላው ኢትዮጵያ በሚደረጉ ሁለንተናዊ የግብረሰናይ እንቅስቃሴዎች በዓይን የሚታዩ አመርቂ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል:: በጣም ጥቂት ሆነን ለሚልዮኖች ተደራሽ የሚሆን አኩሪ ስራዎችንም ሰርተናል:: በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም የእኛን ፈለግ ቢከተሉ ሃገራችንን ማበልጸግ ብዙ ተዓምራዊ ለውጦችን እና እድገቶችንም ማምጣት እንችላለን:: የነገ ሃገር ተረካቢ በሆኑ ሕጻናት በጤናና በትምህርት ዘርፎች ሰፊ አዳዲስ ስራዎችን በቀጣይ በተጠናከረ መልኩ ለማከናወንም አቅደናል:: በመሆኑም ሁሉም ከጎናችን ተሰልፎ እንዲደግፈን ጥሪ ማስተላለፍ እፈልጋለሁ" ብለዋል ሌላው የማህበሩ አባል አቶ ፋሲል አሰፋ::

Deutschland Frankfurt a.M. | Treffen Southern Ethiopia Region Development Community
የደቡብ ኢትዮጵያ ልማት ማህበር በጀርመን 10ኛ ዓመት ዓመታዊ ስብሰባ ምስል Endalkachew Fekade/DW

የደቡብ ኢትዮጵያ ልማት ማህበር በጀርመን እስካሁን ከህክምና ቀሳቁሶች ልገሳ ለሃገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ከማበርከት እና በእርስ በእርስ ግጭት ለተፈናቀሉ ወገኖችም ሰብዓዊ ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር "ሃኪሞች ለኢትዮጵያ" የተሰኘው ቡድን በይርጋዓለም ሆስፒታል የጀመረው ዓይነት የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር በኢትዮጵያ እንዲጠናከር እንዲሁም የሃገሪቱን የባህልና የታሪክ መስህቦች ለውጭ ዜጎች በማስተዋወቅ ጭምር በቀጣይ በስፋት እንደሚሰራ ተገልጿል:: ለዚህም እንዲረዳው ማህበሩ በአዳዲስ አባላት ይበልጥ ተጠናክሮ በኢትዮጵያ የልማት እና የሰብዓዊ አገልግሎቱን ለማስፋት ተዘጋጅቷል ነው ያሉት የማህበሩ ዋና ሰብሳቢ ወይዘሮ ዘመናይ ማርትኒያክ:: የመርሃ ግብሩ ተጋባዥ እንግዳ በጀርመን የኢትዮያያ ኤምባሲ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሙሉ ሰለሞንም ማህበሩ እስካሁን በኢትዮጵያ ያከናወናቸውን ከፍተኛ የእርዳታ እንቅስቃሴዎች አድንቀው በመላው ዓለም የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያንም አገር እና ወገናቸውን በተመሳሳይ መልኩ እንዲረዱ ጥሪያቸውን አቅርበዋል:: አምባሳደሯ በተለይም ሰላም በማስከበሩ ሂደት በመላው ዓለም የሚገኘው ዲያስፖራው ዳር እስከዳር ላደረገው ከፍተኛ ድጋፍ ልባዊ ምስጋናዬን ማቅረብ እፈልጋለሁ ያሉ ሲሆን ይህ ለሀገር የተደረገ ድጋፍ አሁንም የማህበረሰቡን ሁለንተናዊ ኑሮ ለመለወጥና እድገት ለማምጣት በሚደረገው ጥረትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል:: በተጓዳኝ በተደረገላቸው የሽኝት የሽልማት እና የምስጋና መርሃግብርም ማህበሩን እና ታዳሚዎችን አመስግነዋል::

እንዳልካቸው ፈቃደ

አዜብ ታደሰ