1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የረቡዕ ነሐሴ 29 ቀን፤ 2016 ዓ.ም የዓለም ዜና

ረቡዕ፣ ነሐሴ 29 2016

https://p.dw.com/p/4kHYU

አርዕስተ ዜና

*የኢትዮጵያ መንግስት ጦር ኃይልና የፋኖ ታጣቂዎች ኢትዮጵያን ከሱዳን ጋር በሚያዋስነዉ መተማ ዮሐንስ ከተማና አካባቢዉ የገጠሙት ዉጊያ ዛሬ ጋብ ብሎ ማርፈዱ ተነግሯል ። የፋኖ ታጣቂዎች ሽንፋ የተባለችዉን ከተማ ዛሬም እንደተቆጣጠሩ መሆኑ ተነግሯል ።

*በሁለት ዓመቱ የትግራይ ጦርነት ለተፈፀሙ ወንጀሎች ተጠያቂነት ይረጋገጥ ሲል በትግራይ ክልል ተቃዋሚ የሆነው «ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ ፓርቲ» ጥሪ አቀረበ ።

*የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ዋና ከተማ ኪንሻሳ ከሚገኝ ግዙፉ እስር ቤት ለማምለጥ ሞክረዋል በተባሉ እስረኞች ላይ በተከፈተ ተኩስ ቢያንስ 129 ሰዎች ተገደሉ ። የሟች እስረኞች ቤተሰቦች ግድያው ኢሰብአዊ ነው ሲሉ ኮንነዋል ። ምርመራ እንዲደረግም ጥሪ አስተላልፈዋል ።

*የቻይና እና የአፍሪቃ የመሪዎች ጉባኤ በቤጂንግ አቆጣጠር ዛሬ ማታ በይፋ ይጀመራል ። በጉባኤው ለመታደም በርካታ የአፍሪቃ ሃገራት መሪዎች የቻይና ዋና ከተማ ቤጂንግ ገብተዋል ።

ዜናው በዝርዝር

​መተማ ዮሐንስ፦ ዉጊያ ጋብ ብሏል፣ ዉጥረቱ ግን አልረገበም

የኢትዮጵያ መንግስት ጦር ኃይልና የፋኖ ታጣቂዎች ኢትዮጵያን ከሱዳን ጋር በሚያዋስነዉ መተማ ዮሐንስ ከተማና አካባቢዉ የገጠሙት ዉጊያ ዛሬ ጋብ ብሎ ማርፈዱ ተገለጠ ። የከተማዋ ነዋሪዎች እንዳሉት የመተማ ዮሐንስ ከተማን ለመያዝና ላለማስያዝ ትናንት በተደረገዉ ዉጊያ ቢያንስ ሁለት ሰዎች ተገድለዋል ። በመተማ ዮሐንስ ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴዎች እንደሌሉ  የዐይን እማኞች ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል ።

«ከትናንት በኋላ የተወሰኑ ሰዎች ተጎድተዋል ። ከሁለት ሰው በላይ በተኩሱ የሞተ አለ ። ከአራት ያላነሱ የአካል ጉዳት የደረሰባቸውም አሉ ። ከዚያ ውጭ ሁለት ሰው ቀብሬያለሁ ምንም አይነት እንቅስቃሴ የለም ። ሁሉም መሥሪያ ቤቶች ዝግ ናቸው ።»

በመተማ ወረዳ የሺንፋ ከተማን የፋኖ ታጣቂዎች ያለምንም ተኩስ ትናንት ማምሻውን እንደተቆጣጠሯት የዐይን እማኙ ተናግረዋል ። በከተማዪቱ ከባንክ አገልግሎት ውጪ ሌሎች እንቅስቃሴዎች በተለመደው መልኩ መቀጠላቸውን አስረድተዋል ። ሽንፋ ከምዕራብ ጎንደር ዞና ዋና ከተማ ገንዳ ዉኃ ወደ ቋራ በሚወስደዉ መንገድ ላይ የምትገኝ አነስተኛ ከተማ ናት ። የሱዳን ዜና ምንጮች እንደዘገቡት ደግሞ ዉጊያዉን የሸሹ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ድንበር አቋርጠዉ ሱዳን ገብተዋል ። ሱዳን መተማ ዮሐንስን ጋላባት ከሚባለዉ ከተማዋ ጋር የሚያገናኘዉን መንገድ መዝጋቷ ተዘግቧል ። በአካባቢዉ ጦር ማስፈሯም ተገልጧል ። በዜና መጽሄት ተጨማሪ ዘገባ ይኖረናል ።

መቐለ፥ አረና ትግራይ የ ሕወሓት መከፋፈል ለትግራይ ክልል አደጋ ጋርጧል አለ

በሁለት ዓመቱ የትግራይ ጦርነት ለተፈፀሙ ወንጀሎች ተጠያቂነት ይረጋገጥ ሲል በትግራይ ክልል ተቃዋሚ የሆነው «ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ ፓርቲ» ጥሪ አቀረበ ። የያለፈው ጦርነት እና ጥፋት ተጠያቂነት ባለመረጋገጡ በጦርነቱ ተሳታፊ የነበሩ ኃይሎች ለሌላ ጥፋት እየተዘጋጁ ነው በማለትም ዓረና ከስሷል ። ወቅታዊ የትግራይ ክልል ፖለቲካዊ ሁኔታ እና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ መግለጫ የሰጠው «ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ» ፓርቲ ሕወሓት ውስጥ የተፈጠረው መከፋፈል ለትግራይ አደጋ ይዞ የሚመጣ ነው ብሎታል ። ዓረና ፓርቲ የሕወሓት አመራር ልዩነት የግል እና የቡድን ጥቅም ለማስከበር የሚደረግ ፍጥጫ የወለደው ነው ብሎ እንደሚያምን ገልጧል ። በዚህ የዓረና ክስ ዙርያ የመቐለ ወኪላችን ሚሊዮን ኃይለሥላሴ ከሕወሓት ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም ። በዜና መጽሄት ተጨማሪ ይኖረናል ።

አ.አ፥ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት በአቶ ታዬ ደንደዓ የዋስትና ጥያቄ ላይ ያስተላለፈው ብይን

የጦር መሣሪያን ያለፈቃድ ይዞ መገኘትን ጨምሮ በሦስት ተደራራቢ ክሶች ተከስሰው የነበሩት የቀድሞ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደዓ ለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረቡት የዋስትና መብት ጥያቄ ይግባኝ ዛሬ ውድቅ ተደረገባቸው ። አቶ ታዬ ለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ያሉት የዋስትና መብት ጥያቄያቸው ባለፈው ሐምሌ ወር መጨረሻ በስር ፍርድ ቤት ተቀባይነት በማጣቱ ነበር ። ሐምሌ 30 ቀን፣ 2016 ዓ.ም. አዲስ አበባ ውስጥ ያስቻለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሕገመንግስትና ሕገ-መንግስት ስርዓት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀል ጉዳዮች ችሎት አቶ ታዬ ከተከሰሱበት ሦስት ክሶች በሁለቱ ነጻ ሲላቸው፤ የጦር መሣሪያ ይዘው ተገኝተዋል በሚል የቀረበባቸውን 3ኛ ክስ ግን እንዲከላከሉ በይኖ እንደነበር ይታወሳል ። ያንኑን ተከትሎ በዋስ ወጥተው ቀሪው ጉዳያቸውን ከውጪ ለመከታተል ጥያቄ ያቀረቡት አቶ ታዬ፤ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት «ሁኔታዎች ገድበውኛል» ተከሳሹ ተመልሰው ፍርድ ቤት ላይቀርቡ ይችላሉ የሚል ጥርጣሬ አድሮብኛል በማለት ዋስትናውን ከልክሏል ። በውሳኔው ያልረኩት ተከሳሽ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤት ቢሉም ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ያስቻለው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ችሎት፤ «በስር ፍርድ ቤት የተሰጠው ብይን የሚነቀፍ አይደለም» በማለት ውሳኔውን አጽንቶባቸዋል ሲል ሥዩም ጌቱ ዘግቧል ።

ኪንሻሳ፥ ከእስር ቤት ለማምለጥ በተባለ ሙከራ በርካቶች ተገደሉ

የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ዋና ከተማ ኪንሻሳ ከሚገኝ ግዙፉ እስር ቤት ለማምለጥ ሞክረዋል በተባሉ እስረኞች ላይ በተከፈተ ተኩስ ቢያንስ 129 ሰዎች ተገደሉ ። ማካላ በተባለው እስር ቤት ከግድያው ባሻገር ሴቶች በግዳጅ መደፈራቸውንም የኮንጎ ሀገር ውስጥ ሚንስቴር ማሳወቁን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል ። የዐይን ምስክሮች ለዜና ምንጩ እንደተናገሩት ከሆነ ሰኞ ከሌሊቱ ስምንት ሰአት ላይ ይሰማ የነበረው ተኩስ ለበርካታ ሰአታት ቀጥሎ ነበር ። የሀገር ውስጥ ሚንስትሩ ጃክዌማን ሻባኒ በተንቀሳቃሽ ምስል ባስተላለፉት መልእክት፦ ከተገደሉት መካከል «24ቱ የተተኮሰባቸው ማስጠንቀቂያ ከተሰጠ በኋላ» መሆኑን ተናግረዋል ። በሕይወትና ንብረት ላይ ብርቱ ጉዳት መድረሱንም አክለዋል ።

«ሰኞ ሌሊት ስምንት ሰአት አካባቢ ከማካላላ መዓከላዊ እስር ቤት በብዛት ለማምለጥ የነበረው ሙከራ ከፍተኛ የሆነ የሰው ሕይወት እና የንብረት ላውድመት አስከትሏል ። »

ሌሎች ቢያንስ 59 ሰዎች የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸው ህክምና እንደተደረገላቸውም ተናግረዋል ። የሟች እስረኞች ቤተሰቦች ግድያው ኢሰብአዊ ነው ሲሉ ኮንነዋል ። ምርመራ እንዲደረግም ጥሪ አስተላልፈዋል ። ማክሰኞ ማለዳ ላይ በእስር ቤቱ አጎራባች ሥፍራዎች የተኩስ ድምፅ ይሰማ እንደነበር የዐይን እማኞች ተናግረዋል ።

ቤጂንግ፥ የቻይናና የአፍሪቃ ሐገራት ትብብር ጉባኤ

በቻይና እና አፍሪቃ ትብብር ጉባኤ ለመታደም በርካታ የአፍሪቃ ሃገራት መሪዎች ቤጂንግ ገብተዋል ። የሚኒስትሮቹ ጉባኤ ከትናንት በስትያ ጀምሮ በመካሔድ ላይ ነዉ ። በቻይና ዋና ከተማ ቤጂንግ ዛሬ በይፋ የሚከፈተው ጉባኤ እስከ ዓርብ ድረስ ይቆያል ተብሏል ። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ የመሩት መልዕክተኞች ጓድ ቤጂንግ ገብቷል ። ጠቅላይ ሚንስትሩ ዛሬ በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጻቸዉ ባሰራጩት መልዕክት፦ «ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ላደረጉልን ደማቅ አቀባበል እና ላካሄድነው ጠቃሚ ውይይት አመሰግናለሁ ። ኢትዮጵያ የቻይናን ያልተቋረጠ ዘርፈብዙ ድጋፍ በእጅጉ ታደንቃለች» ብለዋል ። የቻይናዉ ፕሬዝደንት ሺ ቺንፒንግ የአፍሪቃ እንግዶቻቸዉን ዛሬ ማታ እራት ይጋብዛሉ ።  በምጣኔ ሐብት ከዓለም የሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ቻይና የአፍሪቃ ሃገራት ዋነኛ የንግድ ሸሪክ ናት በዓለማችን ኤኮኖሚ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ቻይና ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከአፍሪቃ ጋ ያላት የንግድ ልውውጥ ከ167.8 ቢሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን ሮይተርስ ቻይናን ጠቅሶ ዘግቧል ።

ኪዬቭ፥ሩስያ በሰው አልባ ጢያራና ሚሳይሎች የዩክሬን ከተሞችን ደበደበች

የዩክሬን ዋና ከተማ ኪዬቭ እና ልቪቭ በሩስያ ሰው አልባ ጢያራ እና ሚሳይሎች መደብደባቸውን የዩክሬን መከላከያ ዐሳወቀ ።  ልቪቭ ከተማ ውስጥ በጥቃቱ ቢያንስ ሰባት ሰዎች መገደላቸውን የከተማዪቱ ከንቲባ ተናግረዋል ። ከጦር ግንባር በመቶ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በሚገኝ ከተማ ከሩስያ በኩል ድብደባ የተለመደ አይደለም ተብሏል ። ምዕራባዊ ዩክሬን ልቪቭ ከተማ ላይ በሩስያ ተፈጸመ በተባለው ድብደባ ከሟቾቹ ባሻገር ታሪካዊ ሕንጻዎች ጉዳት እንደደረሰባቸውም ተዘግቧል ።

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።