1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ዜና፣ ነሐሴ 22፣ 2016

ነጋሽ መሐመድ
ረቡዕ፣ ነሐሴ 22 2016

-የኢትዮጵያ መንግሥትን በነፍጥ የሚወጉ ኃይላት በሐገሪቱ ብሔራዊ የምክክር ሒደት እንዲካፈሉ ለተደረገላቸዉ ጥሪ መልስ አለመስጠታቸዉን የምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።ለታጣቂዎቹ ኃይላት ጥሪዉ የተደረገበትን መንገድና ጥሪዉ ሥለመድረስ አለመድረሱ ግን የኮሚሽኑ ባለሥልጣናት አልጠቀሱም።-----ግብፅ ለሶማሊያ የጦር መሳሪያ ማስታጠቅ ጀመረች።መሳሪያ የጫኑ ሁለት የግብፅ የጦር አዉሮፕላኖች ትናንት ሞቃዲሾ ማረፋቸዉን ዲፕላቶች አስታዉቀዋል።ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ወደብ ለመኮናተር ከተስማማች ወዲሕ የሞቃዲሾና የካይሮ ፍቅር ፀጥንቷል

https://p.dw.com/p/4k1ZK

ሞቃዲሾ-ግብፅ ለሶማሊያ የጦር መሳሪያ ማስታጠቅ ጀመረች

ግብፅ ለሶማሊያ የጦር መሣሪያ ማስታጠቅ ጀመረች። ዲፕሎማቶችና የሶማሊያ ባለስልጣናት ለሮይተርስ ዜና አገልግሎት እንደነገሩት የተለያዩ ጦር መሣሪያዎችና ጥይቶችን የጫኑ ሁለት የግብፅ የጦር አዉሮፕላኖች ትናንት ጠዋት ሞቃዲሾ አዉሮፕላን ማረፊያ አርፈዋል። ግብፅ ለሶማሊያ በቀጥታ ጦር መሣሪያ ስታስታጥቅ ከ40 ዓመት ወዲሕ የትናንቱ የመጀመሪያዉ ነዉ። ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የመንግስትነት ዕዉቅና ከሌላት ከሶማሊላንድ ወደብ ለመኮናተር የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረመች ወዲሕ የሞቃዲሾና የካይሮ ፍቅር ፀጥንቷል። ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ መገንባትዋን አጥብቃ የምትቃወመዉ ግብፅ፣ የሶማሊያና የኢትዮጵያን መቀያየም እንደ ጥሩ አጋጣሚ ተጠቅማበታለች። የግብፅና የሶማሊያ ባለሥልጣናት ከጥቂት ከሳምንታት በፊት የወታደራዊና የጋራ ፀጥታ ስምምነት ተፈራርመዋል። ታዛቢዎች እንዳሉት ስምምነቱ በተለይም ግብፅ ለሶማሊያ ጦር መሣሪያ ማስታጠቋ ኢትዮጵያን ማሳሰቡ አይቀርም። ሮይተር ዜና አገልግሎት ስማቸዉን ያልጠቀሰዉ አንድ ዲፕሎማት እንዳሉት ደግሞ «ሶማሊያ በእሳት እየተጫወተች ነዉ።»

 

ሐዋሳ-የምክክር ኮሚሽን ጥሪና የታጣቂዎች አቋም

ኢትዮጵያ ዉስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የሸመቁ ታጣቂ ቡድናት በሐገር አቀፍ ምክክር እንዲሳተፉ ላደረገላቸዉ ጥሪ መልስ አለማግኘቱን የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ኮሚሽኑ በሲዳማ ክልል አጀንዳ የማሰባሰብ መርሃግብሩን ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ሲያስጀምር እንደተገለጸው ታጣቂ ኃይላት በምክክር ሂደቱ እንዲሳተፉ በተደጋጋሚ ጠይቋል፡፡ጥያቄዉ ለየታጣቂ ቡድናቱ የቀረበበት መንገድ ግን አልተጠቀሰም። ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም ግን ታጣቂ ቡድናቱን ወደ ምክክር መድረኩ ሳይመጡ የምክክር  ሂደቱን በጥርጣሬ መመልክታቸው አግባብ አይደለም ብለዋል ፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት የተመሠረተዉ ኮሚሽን «መሠረታዊ አለመግባባቶችን» በምክክር ለመፍታትና  አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር እየጣረ መሆኑን አስታዉቋል፡፡ይሁና በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ የፖለቲካ ኃይሎችና አንዳንድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የኮሚሽኑን ገለልተኝነት በመጠራጠር በምክክሩ አይሳተፉም።

ኮሚሽኑ ከዚሕ ቀደም ከአዲስ አበባ ፣ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ፣ ከጋምቤላ ፣ ከሐረሪ ክልሎች እና ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የተሰበሰቡ አጀንዳዎች መረከቡን አስታውቋል ፡፡ በየአማራ ክልል አንዳድ አካባቢዎች በፀጥታ ችግር ምክንያት የተሳታፊዎች ልየታ ለማካሄድ ካጋጠመው ችግር በስተቀር የምክክር ሂደቱ በዕቅዱ መሠረት እየተከናወነ እንደሚገኝ ነው ኮሚሽነር መላኩ  የተናገሩት ፡፡

ዛሬ ሐዋሳ የተጀመረው የሲዳማ ክልል አጀንዳ የማሰባሰብ መርሐ ግብር ለሰባት ቀናት ይቆያል።የሐዋሳዉ ወኪላችን ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ እንደዘገበዉ በመርሐ ግብሩ ከየወረዳዉ የተመረጡ 1 ሺህ 800 ሰዎች ይሳተፋሉ።

 

የሕዳሴ ግድብ ከ1500 ሜጋዋት በላይ ኃይል እያመነጨ ነዉ

ኢትዮጵያ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ የምታመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን ከእጥፍ በላይ ማሳደግዋን አስታወቀች።የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ መስሪያ ቤትን ጠቅሶ እንደዘገበው  በቅርቡ ሁለት ተጨማሪ መዘዉሮች (ተርባይኖች) አገልግሎት በመጀመራቸዉ ከግድቡ የሚመረተዉ የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን ወደ 1 ሺሕ 550 ሜጋዋት ከፍ ብሏል።ከዚሕ ቀደም ሥራ የጀመሩት ሁለት መዘዉሮች እያንዳዳቸዉ 375 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫሉ።ሰሞኑን የተመረቁት ሁለት ተጨማሪ መዘዉሮች ደግሞ እያንዳንዳቸዉ 400 ሜጋዋት ኃይል ያመነጫሉ። ኢትዮጵያ ከግብፅና ሱዳን ጋር የሚያወዛግባትን ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ በአባይ ወንዝ ላይ መገንባት የጀመረችዉ በ2003 አጋማሽ ነዉ። ግድቡ የመጀመሪያዉን ኃይል ማመንጨት የጀመረዉ ግን  ሐቻምና ነዉ። ብዙ ቢሊዮን ዶላር የፈሰሰበት ግድብ ከአፍሪቃ ትልቁ የኃይል ማመነጫ ነዉ። ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ከ5ሺሕ ሜጋዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል ተብሏል።

 

አዲስ አበባ-የአቶ ታዬ ደንደአ አቤቱታ ዛሬም አልተሰማም

በተለያዩ ወንጀሎች ጥርጣሬ ተከስሰዉ የታሰሩት የቀድሞ የኢትዮጵያ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደዓ በዋስ እንዲለቀቁ ያቀረቡት አቤቱታ ዛሬም ዉሳኔ አላገኘም።ባለፈዉ ሐምሌ 30፣ 2016 አዲስ አበባ ያስቻለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሕገ መንግስትና ሕገ-መንግስት ስርዓት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀል ጉዳዮች ችሎት አቶ ታዬ ላይ ከተመሠረተባቸዉ ሶስት ክሶች ከሁለቱ በነጻ አሰናብቷቸዉ ነበር።ይሁንና ፍቃድ ሳይኖራቸው  የጦር መሳሪያ ይዘው ተገኝተዋል በሚል የቀረበባቸውን 3ኛ ክስ ግን እንዲከላከሉ ፍርድ ቤቱ በይኖ ነበር፡፡የአቶ ታዬ ባለቤት ወይዘሮ ስንታየሁ ዓለማየሁ እንደሚሉት አቶ ታዬ   ሶስተኛዉን ክስ በዋስ ተለቅቀዉ እንዲከራከሩ ያቀረቡትን ጥያቄ ፍርድ ቤት ዉድቅ አድርጎባቸዋል።በዚሕም ምክንያት ተከሳሹ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ይግባኝ ጠይቀዉ ፍርድ ቤቱ ለዛሬ ቀጠሮ ሰጥቷቸዉ ነበር።ወይዘሮ ስንታየሁ እንዳሉት ፍርድ ቤቱ አቤቱታን ዛሬ ማየት አልቻለም።

አቶ ታዬ ደንደዓ የተመሰረተባቸዉን ክስ ያለጠበቃ በራሳቸዉ እየተከራከሩ ነዉ።የአዲስ አበባዉ ወኪላችን ስዩም ጌቱ እንደዘገበዉ አቶ ታዬ የጥብቅና መብት ለመከልከላቸው መንግስትን ተጠያቂ አድርገው፣የብሔራዊ መረጃ ደህንነት ያሉትን ተቋም መክሰሳቸው አይዘነጋም፡፡አቶ ታዬ የገዢዉ የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ ባለሥልጣን፣ የኦሮሚያ ምክር ቤት አባልና ሚንስትር ደ ኤታ ነበሩ።

 

ሰነዓ-ሰሜን የመን ዉስጥ ጎርፍና ናዳ 33 ሰዉ ገደለ

አል ማሕዊት የተባለዉ የሰሜናዊ የመንን ወረዳ ያጥለቀለቀዉ ጎርፍና የድንጋይ ናዳ 33 ሰዎች ገደለ።28 መኖሪያ ቤቶችን አፈረሰ።የአል ማሕዊት ባለሥልጣናት ዛሬ እንዳስታወቁት ባለፉት ጥቂት ቀናት በተከታታይ የጣለዉ ከባድ ዝናብ አካባቢዉን በጎርፍ አጥለቅልቆ፣ በየተራራና ጉብታዉ ላይ የነበሩ ድንጋዮችን እየፈነቃቀል ቤቶችና መጠለያዎች ላይ ወርዉሯቸዋል።አለቅጥ የሞሉ ሶስት ግድቦችም ገደባቸዉን ጥሰዉ አካባቢዉን አጥለቅልቀዉታል። በአደጋዉ መሞታቸዉ ከተረጋገጠዉ 33 ሰዎች በተጨማሪ በ10 የሚቆጠሩ ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም።እስካለፈዉ ሳምንት ድረስ በተለያዩ የየመን ግዛቶች የደረሰ ጎርፍ 60 ሰዎች መግደሉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታዉቋል። የየመን ቀይ ጨረቃ ማሕበረሰብ እንዳስታወቀዉ ካለፈዉ ወር ጀምሮ በመላዉ የመን የጣለዉ ዝናብ ከ340 ሺሕ የሚበልጡ ሰዎችን አንድም አፈናቅሏል፣ አለያም ሥራና እንቅስቃሴያቸዉን አዉኳል።

 

 

ዋጋዱጉ-ቡርኪና ፋሶ የምዕራባዉያን መገናኛ ዘዴዎችን አገደች

የቡርኪና ፋሶ ወታደራዊ መንግስት የተለያዩ የምዕራባዉያን ሐገራት መገናኛ ዘዴዎች ከሐገሩ እንዳይዘግቡ አገደ።የብሩኪና ፋሶ መንግስት እርምጃዉን የወሰደዉ መገናኛ ዘዴዎቹ የሐገሪቱ ጦር ሐይል ሰላማዊ ሰዎችን ገድሏል የሚል ዜና በማሰራጨታቸዉ ነዉ።የቡርኪና ፋሶ ጦር ኃይል ባለፈዉ የካቲት 223 ሰዎችን ገድሏል በማለት የአሜሪካዉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሑማን ራይትስ ዋች ያሰራጨዉን መረጃ የተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች ዘግበዉ ነበር።አዣንዝ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበዉ የቡርኪና ፋሶ ዉስጥ እንዳይሰሩ ከታገዱት መካከል የፈረንሳዩ ላ ሞንድ፣የብሪታንያዉ ዘ-ጋርዲያን ጋዜጦች፣ የጀርመኑ ማሰራጪያ ጣቢያ ዶቼ ቬለ፣ TV5 የተባለዉ የፈረንሳይ ቴሌቪዥን ጣቢያ ይገኙበታል።የአዉሮጳ ሕብረትና የየመገናኛ ዘዴዎቹ ኃላፊዎች ርምጃዉን ተቃዉመዉታል

 

በርሊን-«ብሪታንያ ከአዉሮጳ ሕብረት ጋር መቀራረብ ትሻለች» ስታርመር

የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ኪር ስታርመር በሐገራቸዉና በአዉሮጳ ሕብረት መካከል ያለዉን ልዩነት ለማጥበብ እንደሚጥሩ አስታወቁ።ዛሬ ከጀርመኑ መራሔ መንግስት ኦላፍ ሾልስ ጋር በርሊን ዉስጥ የተነጋገሩት ስታርመር እንዳሉት በብሪግዚት ምክንያት የተበላሸዉን የለንደንና የብራስልስን ግንኙነት ለማደስ ሁነኛ እርምጃ ይወስዳሉ።የብሪታንያ ወግ አጥባቂ ፓርቲ ሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ብሪታንያ ከአዉሮጳ ሕብረት አባልነት ወጥታለች።ለዘብተኛዉን የሠራተኛ ወይም ሌበር ፓርቲን የሚመሩት  ስታርመርና የጀርመኑ መራሔ መንግስት ኦላፍ ሾልስ ሐገሮቻቸዉ የመከላከያ፣ የቴክኖሎጂና የንግድ ግንኙነታቸዉን ለማጠናከር ተስማምተዋል። እስከ መጪዉ ጥር ይጠናቀቃል የተባለዉ ስምምነት ብሪታንያ ከአዉሮጳ ሕብረት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማደስ የምታደርገዉ ጥረት አካል ነዉ። የብሪታንያዉን  ጠቅላይ ሚንስትር ፍላጎትና እርምጃን መራሔ መንግስት ኦላፍ ሾልስ ደግፈዉታል። ስታርመር ፓሪስን ለመጎብኘት አቅደዋልም።

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።