1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወባ ወረርሽኝ ኢትዮጵያ ውስጥ ተስፋፍቷል

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 26 2017

ኢትዮጵያ ውስጥ የወባ ወረርሽኝ መባባሱ እየተነገረ ነው። በተለይ ካለፈው ዓመት ጥር እስከዘንድሮው ጥቅምት ወር ድረስ ከሰባት ሚሊየን በላይ ሕዝብ በወባ መያዙን የዓለም የጤና ድርጅት ባለፈው ሳምንት ይፋ ያደረገው መረጃ ያመለክታል። ለምን?

https://p.dw.com/p/4men7
የወባ ትንኝ
የወባ ትንኝ በመከላከያ አጎበር ላይ ፎቶ ከማኅደርምስል Jonathan Nackstrand/AFP

የወባ ወረርሽኝ ኢትዮጵያ ውስጥ ተስፋፍቷል

ወቅታዊው የወባ ወረርሽኝ ይዞታ

ኢትዮጵያ ውስጥ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የወባ ወረርሽኝ እየተባባሰ የብርካቶችንም ሕይወት እየቀጠፈ እንደሚገኝ ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚደርሱን ዘገባዎች ያመለክታሉ። ባሳለፍነው ሳምንት ሐሙስ ዕለት የዓለም የጤና ድርጅት ይፋ ባደረገው ዘገባም ሀገሪቱ ባለፉት ሰባት ዓመታት ከከፋ የወባ ወረርሽኝ ጋር እየታገለች መሆኗን አመልክቷል። የድርጅቱ መረጃ እንደሚያመለክተው ካለፈው ዓመት ጥር ወር አንስቶ እስከያዝነው ጥቅምት 10 ቀን ድረስ በወባ በሽታ ከ7,3 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ተይዟል። 1157ቱ ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል። በአሁኑ ጊዜ 75 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ግዛት በወባ ወረርሽኝ የተመቻቸ መሆኑንም በጤናው ረገድ ከፍተኛ ተግዳሮት እንዳስከተለም ተገልጿል። በእነዚህ አካባቢም 65 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ለወባ የተጋለጠ ሲሆን በተለይ ሕጻናት ለከፋ ጉዳት እየተዳረጉ መሆኑንም የዓለም የጤና ድርጅት አመልክቷል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ሳይንስ ኮሌጅ የውስጥ ደዌ እና ተላላፊ በሽታዎች ተመራማሪ እና ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ወንድወሰን አሞኘየወባ በሽታ የዝናብ ወቅት ሲያበቃ እንደሚመከሰት በማመልከት አሁን ወቅቱ እንደሆነ ነው ያስታወሱት።

የወባ ወረርሽኝ የተባባሰበት ምክንያት

የዓለም የጤና ድርጅት አሁን ለሚታየው የወባ ወረርሽኝ መባባስ አኖፖሊስ ስቴፋኒስ የተሰኘች አዲስ የወባ ትንኝ መስፋፋትን፤ ድርቅን፤ የምግብ ዋስትና አለመኖርን፤ የአየር ንብረት ለውጥን፤ እንዲሁም በሀገሪቱ የቀጠለውን ግጭት ጦርነት በምክንያትነት ገልጿል። ዶክተር ወንድወሰንም ይህን ይጋራሉ።

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ የወባ በሽታን ስርጭት ለመቆጣጠር ትርጉም ያላቸው ተግባርት እየተከናወኑ ውጤት እየታዩባቸው ዓመታት የቅርብ ጊዜ ትዝታዎች ናቸው። ባደረጉት ጥረት ስኬት ያስመዘገቡ አካባቢዎችም በአርአያነት ይነገርላቸው ነበር። አሁን ግን በተለይ በኦሮሚያ ክልል፤ በአማራ ክልል፤ በምዕራብ፣ በደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ስርጭቱ በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን፤ በወባ የሚያዙ ብቻ ሳይሆን የሚሞቱትም ቁጥር ከፍ እያለ መሆዱ እየተነገረ ነው። ከዚህ ቀደም ወባን ስለማጥፋት ይነገር የነበረው ዛሬ ወደኋላ ተመልሶ ካሉት ተደራራቢ ችግሮች ጎን ለጎን ወባ ዋነኛ የጤና ስጋት ሆናለች።

 ፕላስሞዲየም ፋልሲፋረም ተሐዋሲ
የወባ ትንኝ የምታዛምተው በሽታውን የሚያስከትለው ፕላስሞዲየም ፋልሲፋረም ተሐዋሲ ፎቶ ከማኅደርምስል picture alliance/BSIP

ያሉ ተግዳሮቶች

የዓለም የጤና ድርጅት በዘገባው እንዳመለከተው የወባ በሽታን ለመከላከል የሚያስችል የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት መኖሩን፤ በተለይ ደግሞ ግጭት ጦርነት በጠናባቸው አካባቢዎች የጤና ተቋማት በመጎዳታቸው ተገቢው የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ፈተና ሆኗል። የውስጥ ደዌ እና ተላላፊ በሽታዎች ተመራማሪ እና ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ወንድወሰንም እንዲሁ አንድም ለመከላከል የሚሠሩ ሥራዎች እንደቀድሞው መሠራት ያልተቻለበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል፤ የወባ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል የሚያስፈልጉ ግብአቶች በበቂ ሁኔታ አልቀረቡ ከሆነ፤ አዲስ የወባ ዝርያ መምጣቱና መድኃኒት መቋቋም መቻሉና የመሳሰሉት ምክንያቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ አመላክተዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ በሳይንሳዊ አጠራሩ ፋልሲፈረም እና ቫይቫክስ የተሰኙት ናቸው የወባ አይነቶቹ። ፋልሲፈረም በብዛት የሰዎችን ሕይወት የምትቀጥፈው ስትሆን በብዛት የምትከሰተው ደግሞ ቫይቫክስ የተሰኘችው መሆኗን ነው ባለሙያው የገለጹልን። ሆኖም ፋልሲፈረም በፈጣን የደም ምርመራው ሂደት ወዲያው ይገኝ የነበረውን ምልክት አጠፋች። ሆኖም ግን መስተካከሉና የምትደብቀውን የሚያጋልጥ የመመርመሪያ ስልት መኖሩን እና ያንንም ለማዳረስ መሞከሩንም አስረድተዋል።

በነገራችን ላይ አድማጮች ከጤና ሚኒስቴር የሚመለከታቸውን ኃላፊዎች ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት ስልካቸው ባለመነሳቱ እንዳልተሳካልን መግለጽ እንወዳለን። ለሰጡን ሙያዊ ማብራሪያ ዶክተር ወንደወሰንን ከልብ እናመሰግናለን።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ