የወረርሽኝ ስጋት በትግራይ
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 3 2014በትግራይ ወባ፣ አንትራክስ ወይ አባሰንጋ እና ራቢስ በሽታዎች በወረርሽኝ መልክ መቀስቀሱ ተገለፀ። በተለይም የወባ በሽታ በትግራይ በከፍተኛ መጠን እየተሰራጨ ሲሆን በበሽታው የሚለከፉ ሰዎች ቁጥር በየሳምንቱ በ130 ፐርሰንት እያሻቀበ ስለመሆኑ የትግራይ ጤና ቢሮ አስታውቋል። የትግራይ ጤና ቢሮ ምክትል ሐላፊ ዶክተር ሪኤ ኢሳያስ "ባለው ሁኔታ በትግራይ የወባ በሽታ ከቁጥጥራችን ውጭ ሆንዋል" ሲሉ ለዶቼቬለ ገልፀዋል። አንትራክስ ወይ አባሰንጋ የተባለው ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፍ በሽታ በትግራይ በወረርሽኝ መልክ የተከሰተ ሲሆን፥ በትግራይ ባለው ረሀብ ምክንያት ሰዎች የሞቱ እንስሳት ጭምር ስለሚመገቡ ለበሽታው መስፋፋት ምክንያት ስለመሆኑ ተነግሯል። ራቢስ ወይም የእብድ ውሻ በሽታም በትግራይ ወረርሺኝ ሆኖ ተቀስቅሶ እስካሁን ለ42 ሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑ የትግራይ ጤና ቢሮ ገልጿል።
በጦርነቱ ምክንያት በትግራይ የጤና ስርዓቱ መፍረሱ ተከትሎ የተለያዩ በሽታዎች በወረርሽኝ መልክ እየታዩ መሆኑ ይገለፃል። እንደ ትግራይ ጤና ቢሮ መረጃ በአሁኑ ወቅት በትግራይ ወባ፣ አንትራክስ ወይ አባሰንጋ እና ራቢስ ወይም የእብድ ውሻ በሽታዎች ወረርሺኝ ሆነው ይገኛሉ። በተለይም ወባ በሽታ በትግራይ 10 ወረዳዎች ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ያለ ሲሆን ለብዙሃን ሞት እና ሕመም ምክንያት እየሆነ እንዳለ የጤና ባለሙያዎች ይገልፃሉ። የትግራይ ጤና ቢሮ ምክትል ሐላፊ ዶክተር ሪኤ ኢሳያስ እንደነገሩን ወባ በትግራይ የዝርጋታው እና በበሽታው የሚለከፉ ሰዎች ቁጥር መጠን በየሳምንቱ በ130 ፐርሰንት እያደገ የከፋ የሕብረተሰብ ጤና ስጋት ሆንዋል። ላለፊት ሁለት ዓመታት ወባ ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራት ባለመከወናቸው፣ የኬሚካል ርጭት ባለመካሄዱ፣ የመድሃኒት ሌሎች የሕክምና ቁሳቁሶች አቅርቦት ባለመኖሩ የወባ በሽታ በትግራይ "ከቁጥጥር ውጭ" ሆኖ እንዲስፋፋ ምክንያት መሆኑ ዶክተር ሪኤ ኢሳያስ ያስረዳሉ።
ከዚህ ውጭ በትግራይ ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች እየተንሰራፋ ነው። ራቢስ ወይ የእብድ ውሻ በሽታ በትግራይ በወረርሽኝ መልክ እየታየ ሲሆን፣ በበሽተኛ ውሾች የተለከፉ ሰዎች የራቢስ ሕክምና በትግራይ ሆስፒታሎች ባለመኖሩ ወደ ባሕላዊ ሕክምና ለመሄድ ይገደዳሉ። እንደ የትግራይ ጤና ቢሮ መረጃ እስካሁን በትግራይ 384 ሰዎች በራቢስ ተለክፈዋል፣ 42 ሰዎች በበሽታው ምክንያት ሞተዋል።
ሌላው በትግራይ ወረርሺኝ ሆኖ ያለ በሽታ ደግሞ አንትራክስ ወይ አባሰንጋ የተባለው ብዙም ይስተዋል ያልነበረ በሽታ ነው። በዋነኝነት የሕመሙ የተለከፋ ወይ የሞቱ እንስሳት በመመገብ ከእንሰሳት ወደ ሰው የሚተላለፈው በሽታው፣ በትግራይ ባለው ረሀብ ምክንያት በተለይም በገጠሮች ሰዎች የሞቱ እንስሳት ጭምር ስለሚመገቡ ለአንትራክስ ወይ አባሰንጋ በሽታ እየተጋለጡ መሆኑ በጤና ባለሙያዎች ይገለፃል። እስካሁን 116 ሰዎች በበሽታው ተጠቅተው የተመዘገቡ ሲሆን 7 ሰዎች ደግሞ በአንትራክስ ወይ አባሰንጋ በሽታ ምክንያት መሞታቸው መረጋገጡ የትግራይ ጤና ቢሮ አስታውቋል።
በጦርነቱ ምክንያት 80 በመቶ በትግራይ የነበሩ ጤና ተቋማት በተለያየ ደረጃ የሚገለፅ ውድመት እንደደረሰባቸው የትግራይ ክልላዊ መንግስት እና ሌሎች ዓለምአቀፍ ተቋማት ይገልፃሉ።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ