1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮሮና ተሐዋሲ ቁጥጥር ደንብ ለውጥ እና ስጋቱ በጀርመን

ማክሰኞ፣ መጋቢት 13 2014

ጀርመን ውስጥ በተለይ የመተላለፍ ፍጥነቱ ከፍተኛ መሆኑ የሚነገርለት ኦሚክሮን የተሰኘው ልውጥ የኮሮና ተሐዋሲ ከተከሰተ ወዲህ የበሽታው ስርጭት በጣም መጨመሩ ይታያል። ሆኖም በሀገሪቱ የወረርሽኙን መዛመት ለመከላከል ከዚህ ቀደም ተደንግገው የቆዩ ጥብቅ ደንቦች ለቀቅ ሊሉ ነው መባሉ በብዙዎች ዘንድ ስጋት መፍጠሩ እየተነገረ ነው።

https://p.dw.com/p/48qvm
Mosbach, Deutschland. Schild für Masken- und Abstandsregeln
ምስል Firn/Zoonar/picture alliance

የኮሮና ተሐዋሲ ስርጭት የተዘነጋ መስሏል

ከሁለት ዓመት በፊት የኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽኝ ዓለምን አደናግጦ የአየርም ሆነ የምድር እንቅስቃሴዎችን በገደበበት ወቅት ጀርመን ውስጥ የተወሰደው ጥብቅ የጥንቃቄ ርምጃ በሌሎች ሃገራት የታየው አይነት የሞት ድባብ አልታየም ነበር። በየዕለቱ የሚነገረው በተሐዋሲው የተያዙ ሰዎች ቁጥርም ያኔ ከሌሎች ጋር ሲነጻጸር እጅግም ነበር። ኦሚክሮን የተሰኘው ልውጡ የኮሮና ተሐዋሲ ጀርመን ውስጥ ከተገኘ ጀምሮ ግን የሚያዙት ሰዎች በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ መሆናቸው በየዕለቱ የሚወጣው ይፋዊ መረጃ ያመለክታል። የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምን ያስከትል ይኾን የሚለው ስጋት ያጠላበት የኮሮና ተሐዋሲ ዛሬም ከመቶ ሺህ በላይ ሰዎችን መያዙን፤ በርካታ ሃኪም ቤቶችም ታማሚዎችን ማስተናገዱ አቅማቸውን እየተፈታተነው መሆኑን የጀርመን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ነው። በዚህ መሀል ለጥንቃቄ የተደነገጉት ደንቦች በቅርቡ ይላላሉ እየተባለ ነው። 

አቶ ደጀኔ ካሣሁን ዶቼ ቬለ ለሚገኝባት ቦን ከተማ ቅርብ በሆነችው እና ከመላው ጀርመን በትልቅነቷ በአራተኛ ደረጃ ላይ በምትከኘው ኮሎኝ ከተማ የኢትዮጵያን ባህል የሚያስተዋውቀው ፋሲካ ምግብ ቤት ባለቤት ነው። የኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመቆጣጠር ሲደረጉ የቆዩ ጥንቃቄዎች ይላላሉ መባሉ በደንበኞቹ ዘንድ ስጋት ማስከተሉን አስተውሏል።

የጀርመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቡንደስታኽ ባሳለፍነው ሳምንት ለበርካታ ወራት በመላ ሀገሪቱ ተደንግጎ የቆየው የኮሮና ተሐዋሲ ስርጭንት ለመግታት የሚደረጉ የጥንቃቄ ርምጃዎችን ካሳለፍነው እሑድ ጀምሮ ለማላላት ሀሳብ ቀርቦ ጠንካራ ውይይት አካሂዷል። በጥንቃቄ ደንቦቹ ምክንያት ኅብረተሰቡ ተሰላችቷል የሚሉት ወገኖች ለቀቅ ይበል የሚለውን ደግፈው ቢናገሩም በአብዛኛው ግን በየዕለቱ የሚሰማው በተሐዋሲው የተያዙ ሰዎች ቁጥር በመቶ ሺህዎች እየተቆጠረ ደንቡን ለማላላት መወሰን አደገኛ መዘዝ ይኖረዋል በሚል ቸኮሎ ከመወሰን መቆጠብ ይገባል የሚለው በማመዘኑ ውሳኔውን ለየፌደራል ግዛቱ ለመተው ተገዷል። በባየርን ፌደራል ግዛት ስር የምትገኘው ኑረንበርግ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ሌላዋ የኢትዮጵያን ባህል የሚያስተዋውቀው ሉሲ ምግብ ቤት ባለቤት ወይዘሮ ገነት የማነ እሷ በምትኖርበት የጀርመን ፌደራል ግዛት ተደንግጎ የቆየው የጥንቃቄ ደንብ ለውጥ እንደሌለው ገልጻልናለች።

Symbolfoto Impstoff
ምስል Christoph Hardt/Geisler-Fotopres/picture alliance

የጀርመኑ የተላላፊ በሽታዎች ምርምር ተቋማ ሮበርት ኮኽ ዛሬ ይፋ ባደረገው መሠረት ባለፉት 24 ሰዓታት አዲስ በተሐዋሲው የተያዙት ሰዎች ቁጥር 222,080 ነው። ከአንድ ቀን በፊት ደግሞ 92,314 ሰዎች በኮሮና ተሐዋሲ ተይዘዋል። የተለያዩ የጀርመን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዛሬ ባቀረቧቸው የዜና ዘገባዎች የስርጭት ፍጥነቱ ከፍተኛ መሆኑ በሚነገርለት ኦሚክሮን ምክንያት ሀኪም ቤቶች በተሐዋሲው በተያዙ ታማሚዎች መጨናነቅ ጀምረዋል። በዚህ ምክንያትም በየሀኪም ቤቱ ህመምተኛም አስታማሚ ሀኪሞችም ለተሐዋሲው በመጋለጣቸው ጠንከር ያለው የቁጥጥር ደንብ መላላቱ በጤና አገልግሎቱ ዘርፍ ላይ የባሰ ችግር ሊያስከትል እንደሚችልም እያሳሰቡ ነው። እዚህ ጀርመን ሀገር የነርቭ ከፍተኛ ሀኪም የሆኑት ዶክተር ተሻገር ደመቀ ውሳኔው መታየት ያለበት በተያዙ ሰዎች መበራከት ሀኪም ቤቶች የሚጨናነቁ ከሆነ ፖለቲከኞች ጉዳዩን ዳግም ለማየት ይገደዳሉ ነው የሚሉት።

Deutschland | Coronavirus | Straßenszene in Köln
ምስል Martin Meissner/AP Photo/picture alliance

ሀኪም ቤቶች የኮሮና ተሐዋሲ ስርጭት ተባብሶ በነበረት ወቅት እንደታየው በተሐዋሲው በተያዙ ሰዎች ከተጨናነቁ ደግሞ ሌሎች ህክምና የሚያስፈልጋቸው ወገኖች ተገቢውን አገልግሎት ማግኘት እንደማይችሉም ነው ያመለከቱት። ዶክተር ተሻገር ከዚህም ሌላ የጥንቃቄ ደንቡን ለማላላት አሁን ያለው የኮሮና ልውጥ ተሐዋሲ ኦሚክሮን በአጭር ጊዜ ውስጥ የህመም ስሜት ማሳየቱ እና የመተላለፍ ፍጥነቱ ግምት ውስጥ መግባት እንዳለበትም ይገልጻሉ። ተሐዋሲው ካለው የመለዋወጥ ባህሪ የተነሳ በቀጣይ ወራት ምን ሊሆን እንደሚችል ለመገመት ስለሚከብድም ጊዜ ወስዶ መወሰኑ ይበጃል ባይ ናቸው።

ኦሚክሮን የተሰኘው ልውጡ የኮሮና ተሐዋሲ ከተከሰተ ወዲህ ኮቪድ 19 ወደ በርካቶች ጓዳ መግባቱ እየታየ ነው። ብዙዎች በሚችሉት አቅም ከፍተኛ ጥንቃቄዎችን ያለማዛነፍ እያደረጉም እነሱም ሆኑ ቤተሰባቸው ከተሐዋሲው ማምለጥ አለመቻሉን ሲናገሩ ማድመጡ የተለመደ ሆኗል። ዶክተር ተሻገርም እሳቸው በሚሠሩበት ሀኪም ቤት ተመሳሳይ ገጠመኝ እንዳለ ነው ያጫወቱን። የሚበጀው የአፍ አፍንጫ መሸፈኛን ሳያሰልሱ ማድረጉ፤ ርቀት መጠበቁም ሆነ በብዛት ሆኖ ከመሰባሰብ መራቁ ወሳኝነቱ ዛሬም ሊለወጥ እንደማይገባ ነው አጽንኦት የሰጡት።

Deutschland | Coronavirus |  Maskenpflicht in der Frankfurter Innenstadt
ምስል Florian Gaul/greatif/picture alliance

እሳቸው እንደገለጹትም ሆነ በግዛቶቹ የሚኖሩ ወገኖች እንደሚናገሩት በተለያዩ የጀርመን ፌደራል ግዛቶች የኮቪድ 19 ስርጭትን ለመከላከል የተደነገጉ የጥንቃቄ ደንቦች በአንዳንዳንዶቹ የመላላት አዝማሚያ ሲታይ በሌሎች ደግሞ ለውጥ ሳይደረግ ተጠናክሮ እየቀጠለ ነው።  በነገራችን ላይ አድማጮች እዚህ ጀርመን ውስጥ በአንድ የቤንዚን ማደያ ስፍራ ለመኪናው ነዳጅ ለመሙላት የገባ ተስተናጋጅ የአፍ አፍንጫ መሸፈኛ እንዲያደርግ ደጋግሞ ያሳሰበውን ወጣት የማደያ ሠራተኛ በሽጉጥ ተኩሶ በመግለደሉ ፍርድ ቤት ቀርቧል። ግለሰቡ ፍርድ ቤት ቀርቦ ኮሮና ተሐዋሲን ለመከላከል በሚደረጉ የጥንቃቄ ርምጃዎች መሰላቸቱን በምክንያት ከመግለጹ ውጪ ወንጀሉን አምኗል።

ኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ጀርመን ውስጥ 18.994.411 ሰዎች በተሐዋሲው መያዛቸው፤ 127 ሺህ ደግሞ ከተሐዋሲው ጋር በተገናኘ ሕይወታቸው ማለፉ ተመዝግቧል። ባለፈው ሁለት ሳምንት እስከ ትናንት ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ ደግሞ 2,745,011 ሰዎች በኮሮና ተሐዋሲ መያዛቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።

 ሸዋዬ ለገሠ 

አዜብ ታደሰ