1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮሌራ ወረርሽኝ በኬንያ የዳዳብ መጠለያ ጣቢያ

ቅዳሜ፣ ሰኔ 3 2015

ከ300,000 በላይ የሶማሊያ እና የጎረቤት ሀገራት ስደተኞችን በሚያስጠልሉት በኬንያ የዳዳብ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች በርካታ ስደተኞች በኮሌራ ወረርሽኝ መጠቃታቸውን ድንበር የለሹ የሀኪሞች ቡድን አስታውቋል።አዳዲስ የሚመጡ ስደተኞች ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞም የጉዳቱ መጠን በፍጥነት ሊጨምር ይችላል ሲል የረድኤት ድርጅቱ አስጠንቅቋል።

https://p.dw.com/p/4SLWY
Flash-Galerie Hungerkatastrophe in Afrika
ምስል picture alliance/dpa

የኮሌራ በሽታ በዳዳብ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ

በኬንያ ዳዳብ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች  በርካታ ስደተኞች በኮሌራ ወረርሽኝ መጠቃታቸውን ድንበር የለሹ የሀኪሞች ቡድን አስታውቋል።አዳዲስ የሚመጡ ስደተኞች ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞም  የጉዳቱ መጠን በፍጥነት ሊጨምር ይችላል ሲል የረድኤት ድርጅቱ አስጠንቅቋል።

ከ300,000 በላይ የሶማሊያ እና የጎረቤት ሀገራት ስደተኞችን በሚያስጠልሉት በኬንያ የዳዳብ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች የከፋ የጤና ችግር ሊያጋጥም እንደሚችል ድንበር የለሹ የሀኪሞች ቡድን የምስራቅ አፍሪቃ ቅርንጫፍ አስጠንቅቋል።

የድንበር የለሹ የሀኪሞች ቡድን በፈረንሳይኛ ምህፃሩ/ MSF/ የኬንያ ዳይሬክተር ሀሰን ማይያኪ ለDW እንደተናገሩት ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ያልታየ የከፋ የኮሌራ እና ሌሎች ወረርሽኞች በመጠለያ ጣቢያዎቹ የመከሰቱ አጋጣሚ ከፍተኛ ነው።
የረድኤት ድርጅቱ እንዳስታወቀው በዳዳብ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ እስካሁን  2,786  ስደተኞች በወረረሽኑ ተጎድተዋል።

የንጽህና ጉድለት፣ የስደተኞች ፍልሰት መጨመር፣ የተዳከመ ሀብት እና የገንዘብ መጠን መቀነስ ሁኔታውን እያባባሱት መሆኑም ተገልጿል። 

Somalia Hungersnot Lager Flüchtlingslager Flash-Galerie
ምስል dapd

በዳዳብ የድንበር የለሹ የሀኪሞች ቡድን የጤና አስተባባሪ የሆኑት የህክምና ባለሙያዋ  ዶክተር  ካፒል ሻርማ  እንደገለፁት የኮሌራ ወረርሽኙ ከ7 ወራት በላይ ያስቆጠረበት ዋናው ምክንያት በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ ባለው የንፅህና ጉድለት ነው።

 «ሁላችንም እንደምናውቀው ለኮሌራ በሽታ ከሚዳርጉት ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል አንዱ የንፅህና ጉድለት ነው። የንፁህ መጠጥ ውሃ  እና የመጸዳጃ ቤት ተደራሽነት በጣም አስፈላጊ ነው።በመጠለያ ጣቢያው  ክፍት ቦታ ላይ መፀዳዳት አለ። መጸዳጃ ቤት ያለው ከ50% በታች የሚሆነው ነው።ስለዚህ እነዚህ ሁሉ ተደማምረው ለወረርሽኙ መጨመር  ምክንያት ሀነዋል።»
በአካባቢው ያሉ የህክምና ባለሙያዎች ሁኔታው እንዲስተካከል ከተፈለገ በውሃ፣ በፅዳት እና በንፅህና አጠባበቅ ዙሪያ አስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድም ጥሪ አቅርበዋል።

Flash-Galerie 60 Jahre Genfer Flüchtlingskonvention
ምስል picture alliance/dpa

የኬንያ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና ሌሎች ግብረሰናይ ድርጅቶች ከየካቲት ወር ጀምሮ በመጠለያ ጣቢያው የኮሌራ ክትባት  እና የጤና መረጃዎችን የመስጠት ስራዎችን ሰርተዋል። በአካባቢው ያሉ የህክምና ባለሙያዎች ግን በቂ እንዳልነበር እና ብዙ መሰራት እንዳለበት ዶክተር ካፒል ይናገራሉ። 
«ከውሃ ፣ከፅዳት እና ከንፅህና አጠባበቅ አንፃር ለዚህ ህዝብ የበለጠ መስራት ያስፈልጋል።በዚህ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ የንፅህና አጠባበቅ አገልግሎት ለሚሰጡ ድርጅቶችም ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ ያስፈልጋል።»

በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በተከሰተው የድርቅ የተነሳ  ወደ ዳዳብ ከሚገቡት መካከል አብዛኞቹ  የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያለባቸው ፣ የተዳከሙ እና  ለበሽታው የተጋለጡ መሆናቸውንም የጤና ባለሙያዎቹ ገልፀዋል።

በጎርጎሪያኑ 2022 ዓ/ም ብቻ ወደ 100,000 የሚጠጉ ስደተኞች ወደ  ኬንያ ገብተዋል።ከነዚህም ውስጥ 67,000 የሚሆኑት አዳዲስ ስደተኞች ወደ ዳዳብ የገቡ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ከ124,000 በላይ  ገና ያልተመዘገቡ ስደተኞች በዳዳብ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ይገኛሉ።ይህ ሁኔታም  የመጠለያ ጣቢያውን ከመጠን በላይ እንዲጨናነቅ አድርጎታል ሲሉ በኬንያ የድንበር የለሹ የሀኪሞች ቡድን የህክምና አስተባባሪ ዶክተር ኒቲያ ኡዳይራጅ ይገልፃሉ።

 «መጠለያ ጣቢያዎቹ ቀድሞውንም ከመጠን በላይ የተጨናነቁ ናቸው፣ እናም እዚያ ያለው ሰብዓዊ ሁኔታ ቀድሞውኑ ገደቡን አልፏል።»

Somalia Hungersnot Lager Flüchtlingslager
ምስል dapd

35,000 ሰዎችን የመያዝ አቅም ያለው የመጠለያ ጣቢያ በአሁኑ ወቅት ወደ 140,000 የሚጠጉ ስደተኞችን እያስተናገደ ሲሆን በሶማሊያ ባጋጠመው የከፋ ድርቅ እና እንደ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና ኢትዮጵያ ባሉ ጎረቤት ሀገራት በተከሰተው ዘርፈ ብዙ ቀውስ ሳቢያ  አሁንም ድረስ በርካታ ስደተኞች ወደ መጠለያ ጣቢያው እየጎረፉ ይገኛሉ።

ከዚህ በተጨማሪም ለመጠለያ ጣቢያው ችግር መባባስ የዓለም ኤኮኖሚ ቀውስም የራሱን ሚና ተጫውቷል።ሁኔታው የብዙ የእርዳታ ድርጅቶች ልገሳ  እና በመጠለያ ጣቢያው  ያሉ አንዳንድ መሰረታዊ አገልግሎቶችን እንዲዘገይ አድርጓል። 

ይህንን ተከትሎ የኬንያ መንግስት አዲስ የሚመጡ ስደተኞችን ለማስተናገድ እና በመጠለያ ጣቢያው ያለውን የሃብት ጫና ለማቃለል። አራተኛውን የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ለመክፈት ማቀዱን አስታውቋል ።

 

ፀሀይ ጫኔ 
ነጋሽ መሀመድ