የኬንያና የኢትዮጵያ ቀጣይ ግንኙነት
ዓርብ፣ መስከረም 6 2015የኬንያው አዲሱ ፕሬዝዳንት ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ ቃለ-መሃላ ሲፈጽሙ ባደረጉት ንግግር ውስጥ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ አንስተው የቀድመው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የጀመሩትን የሰላም ሂደት እንዲገፉበት መስማማታቸውን አንስተው ነበር፡፡ ኬንያ እና ኢትዮጵያ በቃጣናው መልካም የሆነ እና ከአንከንም የራቀ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው አገራት ይባልላቸዋል፡፡
ኬንያ በቀጣይ በአዲሱ ተመራጭ ፕሬዝዳንት ስር ምንያህል የዲፕሎማሲ ሁኔታ ከኢትዮጵያ ጋር ትከተላለች? በኢትዮጵያ ውስጥ ላለው የአለመረጋጋት ሁኔታስ ሚናዋ ምን ያህል ይሆን?
አዲሱ የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሳሞይ ሩቶ በባዓለ ስመት ንግግራቸው የቀድሞ አለቃቸው ዑሁሩ ኬንያታ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ የጀመሩትን ተፋላሚዎችን የማደራደር እና የሰላም ጥረት የመቀጠል ሃላፊነትን እንዲያስቀጥሉ በመግለጽ ለጎረቤታቸው ኢትዮጵያ የሰጡትን ትኩረት በጉልህ አሳይተዋል፡፡
የሁለቱ አገራት ግንኙነት የጦርነት ታሪክ የሌሌውና ለዘመናት በመንግስታት መካከል በበጎ ሁኔታ የቀጠለ በሚል በተንታኞች ይገለጻል፡፡
መሰረቱን ኔዘርላንድ ባደረገው በሰላምና ህገመንግስት ግንባታ ላይ የሚሰራ ኢንተርናሽናል አይዲያ በተባለ ድርጅት ውስጥ የሚሰሩት የምስራቅ አፍሪካን ፖለቲካ በመተንተን የሚታወቁት ዶ/ር አደም ካሴ አበበ፤ ይህ የኬንያ ተግባር “የኢትዮጵያን አሁናዊ ችግር ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ የመፍታት ፍላጎቷን የሚያሳይ ነው” ይላሉ፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስትን የሚወጋው ህዝባዊ ወያኔ ኃርነት ትግራይ (ህወሓት)ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ መንግስት ለጦርነቱ መቋጫ ይሆናል ብሎ ያስቀመጠውን በአፍሪካ ህብረት ስር የመደራደር መርህን ወደ ጎን በማለት የኬንያውን ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታን ለአደራዳሪነት መምረጣቸው ይታወቃል፡፡ በእርግጥ ህወሓት ይህን አቋሙን በሰሞነኛው መግለጫው አሻሽሎ በአፍሪካ ህብረት ስር በሚካሄደው የሰላም ጥትረት ለመደራደር መዘጋጀቱን አሳውቋል፡፡ ዶ/ር አደም ካሴ በማብራሪያቸው የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት በድርድሩ የመሳተፍ ጥረት እውን መሆን ከአፍሪካ ህብረቱ መርህ ጋር አይጋጭም ይላሉ፡፡
ዶ/ር አበበ ካሴ “በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ለሚስተዋለው የሰላም እጦትና የግጭት ችግር ዋነኛ መፍትሄው የሚመነጨው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ተፋላሚ ኃይላት ሙሉ ፈቃደኝነት ሲታከለበት ብቻ ነው” ይላል፡፡ “የአደራዳሪዎች መብዛትና ጫና ለኢትዮጵያው ችግር ዘለቄታዊ እልባት አያመጣም” በማለትም ሃሳባቸውን ይደመድማሉ፡፡
እንደ ተንታኙ አስተያየት “ሰፋ ያለ ዲፕሎማሲያዊ ግኙንነት ያላቸው ኬንያ እና ኢትዮጵያ በአዲሱ ተመራጭ ፕሬዝዳንትም ስር በኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ እና ፀጥታ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩበት ቢሆን እንጂ አሉታዊ ግንኙነት አይጠበቅም፡፡” በኢትዮጵያ የተጀመሩ የኬንያ ኢንቨስትመንቶችና የጋራ ደህንነት ስራዎች እንደሚጠናከሩም እምነታቸውን አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የማክሰኞው የኬንያ ፕሬዝዳንት በዓለ ስመት ላይ ከታደሙ የአገራት መሪዎች ተጠቃሽ መሆናቸው ይታወሳል፡፡
ሥዩም ጌቱ
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ