የኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ችግር
ረቡዕ፣ ሐምሌ 20 2014
በኦሮሚያ ክልል ያለውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት ከኃይል እርምጃ ውጪ ሌላ አማራጭ የለም ብሎ እንደሚያምን የክልሉ መንግስት አመለከተ፡፡ የኦሮሚያ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከቱት “አሸባሪ” ባሉት በክልሉ በሚንቀሳቀሰው ሸማቂ ቡድን ላይ የሚወሰደው ወታደራዊ እርምጃ ውጤት እያመጣም ነው ብለዋል፡፡ክልሉ እየተገባደደ ባለው 2014 ዓ.ም. በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ቢታጀብም የተሻለ የልማት ስራዎች አፈጻጸም አሳይቷል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከሚገኙ 21 ዞኖች 8ቱ በከፊል በድርቅ ሲጠቁ 8ቱ ደግሞ የከፋ የፀጥታ ችግር ውስጥ ነው የከረሙት፡፡ ይሁንና የክልሉ መንግስት የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች በ2014 ዓ.ም. ያቀድኳቸውን የልማት ስራዎች ከግብ ከማድረስ አላገደኝም ብሏል፡፡ የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በዓመቱ የክልሉ ኢኮኖሚ 6.7% እምርታን አሳይቷል ነው ያሉት፡፡ በዓመቱ የፀጥታ ችግር ፈታኝ በሆነበት አፈጻጸሙ ከእቅዱ 100% የላቀ ከ52 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡንም አመላክተው፤ ለፀጥታ ችግሩ እልባት ለማስገኘት ታጣቂዎች ላይ የተቀናጀ ያሉት ወታደራዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊው አሁን ላይ የተሻለ የፀጥታ ሁኔታ በኦሮሚያ ውስጥ ተስተውሏልም ነው ያሉት፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ ብሔራዊ ምክክር ለማድረግ የተቋቋመው ኮሚሽን ውስጥ በኦሮሚያ ታጥቀው የሚንቀሳቀሰው መንግስት ሸነ ያለውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ቡድን የመሳተፍ እድሉ ምን ያህል ነው፤ የክልሉስ መንግስት ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ተደራድሮ የመፍታት ዝግጁነቱ አለው ወይ የተባሉት አቶ ኃይሉ፣ ችግሩን ለመፍታት ከወታደራዊ እርምጃ ውጭ የተቀመጠ አቅጣጫ የለም ብለዋል፡፡
በኦሮሚያ እየተገባደደ ባለው ዓመት በበጋ የስንዴ መስኖ ልማት ከ327 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ 14 ሚሊየን ኩንታል ምርት በማምረት ሊደርስ ነበረውን የከፋ የምግብ እጥረት በመጠኑም ቢሆን ለመቋቋም ማስቻሉም ተነግሯል፡፡ በዓመቱ ከ 3 ሺህ በላይ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውም ነው ተገለጸው፡፡ በቀጣይ 2015 ዓ.ም. የፀጥታ ችግሮችን መቅረፍ እና የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጠው ምርታማነት ላይ በትኩረት ለመስራት መታቀዱንም የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊው በመግለጫቸው አጽእኖት ሰጥተዋል፡፡
ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ