1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭትን ለመግታት የሚታገሉት የደሴ ከተማ ወጣቶች

ዓርብ፣ ጥቅምት 29 2017

ገና በታዳጊ ዕድሜዋ ለዚያዉም ምክንያቱን በውል በማታውቀው ሁኔታ ለቫይረሱ የተጋለጠችው ማክዳ ቀጣዩ የህይወቷ ምዕራፍ ፈታኝ ነበር ። በቫይረሱ መያዝ የሕይወት መጨረሻ ያህል ይሰማኝ ነበር የምትለው ወጣቷ ምንም እንኳ ስለበሽታው አንብባ መረዳት የምትችል ቢሆንም ከማህበረሰቡ ከሚገጥማት የአመለካከት ችግር ራሷን እስከማግለል አድርሷት ነበር።

https://p.dw.com/p/4mn84
Äthiopien | Verein Dessie Addis Tesfa
ምስል Brehanemeskel Sisay

ድጋፍ የሚሻው የደሴ ከተማ ወጣቶች የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭትን ለመግታት የሚያደርጉት ጥረት

ማክዳ ሞገስ ትባላለች ፤ የደሴ ከተማ ነዋሪ ናት ። 24 ዓመቷ ነው። የኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ በደሟ ውስጥ መኖሩን ያወቀችው ገና በለጋ ዕድሜዋ ነው ። ክፉ ደጉን ሳታውቅ ፤ የ8ኛ ክፍል ተማሪ ሳለች በቫይረሱ መያዟን የምትናገረው ማክዳ ቫይረሱ እንዴት እና በምን ምክንያት እንደያዛት አታውቀውም ። ማክዳ እንዳለችው በቫይረሱ መያዟን በምርመራ ያረጋገጡ የህክምና ባለሞያዎች  በቫይረሱ በተበከለ ደም ንክኪ የተጋለጠችበት ሁኔታ ሳይኖር እንዳልቀረ እንደነገረቻቸው ገልጻለች ። 
«ለቫይረስ የተጋለጥኩበት አጋጣሚ ከቤተሰብ አይደለም፤ ወላጆቼ ቫይረሱ የለባቸውም ፤ ታናሽ እህቴም ነጻ ናት ፤ በሆነ አጋጣሚ ነው ይላሉ ፤ ምናልባት ትምህርት ቤት ደም ነክተሽ ሊሆን ይችላል ፤ ይላሉ። ይሄ የኔ ብቻ ጉዳይ አይደለም ሌሎችም እንደኔ የሆኑ አሉ»
ገና በታዳጊ ዕድሜዋ ለዚያዉም ምክንያቱን በውል በማታውቀው ሁኔታ ለቫይረሱ የተጋለጠችው ማክዳ ቀጣዩ የህይወቷ ምዕራፍ ፈታኝ ነበር ። በቫይረሱ መያዝ የሕይወት መጨረሻ ያህል ይሰማኝ ነበር የምትለው ወጣቷ ምንም እንኳ ስለበሽታው አንብባ መረዳት የምትችል ቢሆንም ከማህበረሰቡ ከሚገጥማት የአመለካከት ችግር ራሷን ማግለል የመጀመሪያ ምርጫዋ ነበር ። 
«እውነት ለመናገር ከባድ ነበር ስምንተኛ ክፍል አካባቢ ነበር ፖዘቲቭ የሆንኩት ፤ ከዚያ በኋላ ቤተሰቦቼ ለኔ ለመናገር እጅግ ፈርተው ነበር ። እኔ አስረኛ ክፍል አካባቢ ነው ድንገት አሞኝ በጤና ባለሞያዎች የተነገረኝ»

ወጣት ማክዳ ሞገስ
ገና በታዳጊ ዕድሜዋ ለዚያዉም ምክንያቱን በውል በማታውቀው ሁኔታ ለቫይረሱ የተጋለጠችው ማክዳ ቀጣዩ የህይወቷ ምዕራፍ ፈታኝ ነበር ምስል Brehanemeskel Sisay

በአማራ ክልል የኤች አይቪ ስርጭትና የመድኃኒት አቅርቦት ችግር
ፋኑኤል ፋንታሁንም ልክ እንደ ማክዳ ሁሉ የደሴ ከተማ ነዋሪ ወጣት እና የኤች አይቪ ኤድስ በደሙ ውስጥ የሚገኝ ወጣት ነው ። 23 ዓመቱ ነው። ፋኑኤል ለኤች አይ ቪ ኤድስ የተጋለጠው ገና ከውልደቱ ጀምሮ እንደሆነ ነው የሚናገረው።  ከቤተሰብ እንደተላለፈበት እና በተመሰቃቀለ ሁኔታ ውስጥ አልፎ እዚህ መድረሱንም ይገልጻል። 
«ቫይረሱ በደሜ እንዳለበት ያወቅኩት ገና የአምስት ዓመት ልጅ ሆኜ ነው። የስድስት ዓመት ልጅ እያለሁ አካባቢ ነው መድሃኒቱን መውሰድ የጀመርኩት ፤ እንደማንኛውም ሰው መድሃኒቱን ከመጀመራችን በፊት አስቸጋሪ ህይወት ነበረን ። ሙሉ ለሙሉ ጤነኛ አልነበርኩም። መድሃኒቱን መውሰድ ከጀመርኩ በኋላ ጤነኛ ነኝ ፤ ትምህርቴን እማራለሁ ፤ ስራም እሰራለሁ። »

በወጣቶች ከሚሰጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች አንዱ
የመገናኛ ብዙኃን ስለቫይረሱ ስርጭት እና ስለሚያስከትለው በሽታ የሚሰጡት ግንዛቤ የማስጨበጥ ተግባራትም እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም አልያም የሉም። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን በማህበረሰቡ ውስጥ ያለው የአመለካከት ችግር ዛሬም ድረስ አልተቀረፈም ። ምስል Brehanemeskel Sisay


ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በኋላም ቢሆን ግጭት ጦርነት ባልተለየበት የአማራ ክልልም ሆነ በመላው ሀገሪቱ የኤች አይ ቪ ስርጭት መልሶ እያንሰራራ ስለመሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ ። 
በእርግጥ ነው ስለ ኤች አይቪ ስርጭት እና ግንዛቤ ለመፍጠር የሚከናወኑ ተግባራት እና ይህንኑ ለማስፈጸም ይወሰዲ የነበሩ እርምጃዎች በእጅጉ መቃዛቀዙ ይታያል ። የመገናኛ ብዙኃን ስለቫይረሱ ስርጭት እና ስለሚያስከትለው በሽታ የሚሰጡት ግንዛቤ የማስጨበጥ ተግባራትም እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም ። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን በማህበረሰቡ ውስጥ ያለው የአመለካከት ችግር ዛሬም ድረስ አልተቀረፈም ። ይህንኑ ለመጋፈጥ ነዋሪነታቸውን በደሴ ከተማ ያደረጉ ወጣቶች ከስድስት ዓመታት በፊት በመሰረቱት አዲስ ተስፋ የኤች አይ ቪ ኤድስ በደማቸው ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ማህበር የአቅማቸውን እያበረከቱ ይገኛሉ። የማህበሩ መስራች እና ሊቀመንበር ወጣት ብርሃነ መስቀል ሲሳይ እንደሚለው ህጻናት እና ታዳጊ ወጣቶችን ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ የህብረተሰቡን ክፍል ለማንቃት እና ለማጠናከር  ነው።

የኤች አይ ቪ አሳሳቢ የጤና ችግር ሆኖ መቀጠል
«ማህበሩ የተመሰረተበት ዋነና ዓላማ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ አፍላ ወጣቶችን ማጠናከር እና ግንዛቤ እንዲኖራቸው እና ራሳቸውን እንዲያውቁ ነው።»
በብርቱ ፈተና ውስጥ እያለፉ ለሌሎች አርአያ ለመሆን በመጣር ላይ የሚገኙት ወጣቶቹ ከማህበረሰቡ የሚገጥማቸው ተግዳሮት ግን እንዲሁ በቀላሉ የሚታለፍ እንዳልሆነ ነው። 
«አወቅን የምንለው ተማርን የምንለው ሰዎች ራሱ የሚሰጡን ግብረ መልስ ከባድ ነው። ያገሉናል ለምሳሌ  የጓደኞቻችን ቤተሰቦች ያገሉናል፤ ከባድ ነው ፤ ሌላው ደግሞ የኛው ቤተሰብ ራሱ ለምሳሌ ወጣ ብዬ ሌሎችን ሳስተምር የሚሰጡት ምላሽ ከባድ ነው።»

ወጣት ብርሃነ መስቀል ሲሳይ ፤ የአዲስ ተስፋ ማህበር ጸሐፊ
በብርቱ ፈተና ውስጥ እያለፉ ለሌሎች አርአያ ለመሆን በመጣር ላይ የሚገኙት ወጣቶቹ ከማህበረሰቡ የሚገጥማቸው ተግዳሮት ግን እንዲሁ በቀላሉ የሚታለፍ እንዳልሆነ ነው።ምስል Brehanemeskel Sisay


ኢትዮጵያ ባለፈው የጎርጎርሳዉያኑ 2023 ከ 1 .7 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የኤች አይ ቪ ኤድስ በደማቸው ውስጥ እንደሚገኝ በምርመራ መረጋገጡን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሃገራትን የኤዝ አይቪ ኤድስ ጉዳይ መረጃ ያመለክታል። በተናጥል በአማራ ክልል ብቻ ያለውን ከተመለከትን 165 ሺ ገደማ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ሰዎች እንዳሉ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያወጣው ጥናት ያሳያል። ይህ በምርመራ የተረጋገጠውን መረጃ ሲያመለክት በአንጻሩ እንደቀደመው ጊዜ የተቀናጀ ምርመራ ባለመኖሩ አኃዙ ከዚህም ሊያሻቅብ  እንደሚችል ይገመታል።

 ቀጣዩ ክትባት የኤች አይ ቪ ኤድስ ይሆን?
ይህን ቀላል ቁጥር የማይሰጠው የህብረተሰብ ክፍል ግንዛቤውን ማሳደግን ጨምሮ ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በደሴ እና ዙሪያዋ እየተንቀሳቀሱ ያሉት ወጣቶች ሁሉንም የህብረተሰብ በዚሁ መርሃ ግብር ማቀፋቸውን የማህበሩ መስራቅ ወጣት ብርሃነ መስቀል ይናገራል።
«እንደ ማህበር አጠ,ቃላይ አሁን ከ250 በላይ አባላት ይዘን እየተንቀሳቀስን እንገኛለን። ከነዚህ ውስጥ ከ65 እስከ 70 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው ። ወንዶች የተወሰኑ አሉ ፤ አካል ጉዳተኞችም አሉ። »

የአዲስ ተስፋ ማህበር አባላት በግንዛቤ ማስጨበጥ ውይይት ላይ
ወጣቶቹ ሁሉንም የህብረተሰብ በዚሁ መርሃ ግብር ማቀፋቸውን የማህበሩ መስራቅ ወጣት ብርሃነ መስቀል ይናገራል።ምስል Brehanemeskel Sisay


ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ልቅ በሆነ የግብረ ስጋ ግንኙነትም ሆነ በሌሎች ቫይረሱን ሊያስተላልፉ በሚችሉ ምክንያቶች ተጋልጠው ፤ በምርመራ ራሳቸውን አውቀው እና ከህብረተሰቡ ተገልለው የሚኖሩ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች  እንዳሉ የሚናገሩት ወጣቶቹ ፤ አርአያነት ያለው ስራቸውን ተቀብለው ለማገዝ ይሁንታቸውን የሚሰጡ ሰዎች እንዳሉ ይገልጻሉ ። 
«ሰው ስለራሱ ራሱ ነው የሚያውቀው። ራሱን ደብቆ እኛን ተወቃሽ ያደርጋል። በተቃራኒው ደግሞ በጣም መልካም ሰዎች አሉ ። ስልካችንን ተቀብለው እኛም ቤት እንዲህ አይነት ልጅ አለች እባክሽ እንዳንቺ አድርጊልን የሚሉም አሉ።»
ከ150 በላይ አባላት ያሉት የደሴ የአዲስ ተስፋ ማህበር በበጎ ፈቃደኞች ተመስርቶ የአቅሙን እያበረከተ ቢሆንም ተገቢው  ድጋፍ እንዳልተደረገለት የማህበሩ መስራች ወጣት ብርሃነ መስቀል ይናገራል። 

አሳሳቢዉ የኤድስ ስርጭት በኢትዮጵያ
« የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግ አካል የለም ። በቁሳቁስም እንዲሁ ድጋፍ የሚያደርግ የለም። የከተማው ጤና ቢሮን ጨምሮ መንግስት ትኩረት የመስጠት ችግር አለ። ሚዲያውም በተመሳሳይ እንደ ድሮው ስለ ኤች አይቪ ቅስቀሳ የማድረግ ድክመት አለ።»
ወጣቶቹ በተነሳሽነታቸው ልክ ተገቢው ድጋፍ ሊደረግላቸው በተገባ ነበር ። በወጣቶቹ የስራ እንቅስቃሴ እና በክልሉ ስላለው አጠቃላይ የቫይረሱ ስርጭት ለመጠየቅ ወደ ክልሉ ጤና ቢሮ የሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎችጋ ስልክ ብንደውልም ስልክ ባለመነሳቱ መረጃ ልናገኝ አልቻልንም ።  ነገር ግን የጉዳዩ አሳሳቢነት አሁም እንዳለ ነውና የሚመለከታቸው ሁሉ ወጣቶቹን መደገፍ ቢችሉ ለተቀረው የሀገሪቱ ክፍል የሚተርፍ አርአያነት ያለው ተግባር ማከናወን እንደሚችሉ ማሳያ ሊሆን ይችላል። 

የአዲስ ተስፋ ማህበር አባላት የግንዛቤ ማስጨበጥ መርኃ ግብር ላይ
ወጣቶቹ በተነሳሽነታቸው ልክ ተገቢው ድጋፍ ሊደረግላቸው በተገባ ነበር ። ግን ያ ሲሆን ብዙም አይታይምምስል Brehanemeskel Sisay


ወጣቶቹ ማህበር መስርተው በኤች አይ ቪ ኤድስ መያዝ በእኛ ይብቃ ሲሉ ከግብ እንዲደርስላቸው የሚፈልጉ በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም ፤ የቫይረሱን ስርጭት መግታት ግን ቀዳሚ ጉዳያቸው ነው ። 
«እኔ ቢሳካልን ብዬ ተስፋ የማደርጋቸው ሁለት ነገሮች ናቸው ።  ዋነናው ጉዳይ የኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ ስርጭት በመላው ዓለም ብሎም ከኢትዮጵያ እንዲቀንስ  ነው ። ሁለተኛው ደግሞ ልክ የኛን ዕድል ያላገኙ የእኛን ዕድል እንዲያገኙ ነው»
«እንደ ሃገር ታሪክ ተናጋሪዎች ብቻ መሆን የለብንም ። ከእኔ ምን ይጠበቃል ፤ ምንድነው ማድረግ ያለብኝ ፤ የሚለውን ነገር ሁላችንም ብናስብ ጥሩ ነው። ነጻ የሆነ ትውልድ ለነገ መፍጠር አለብን። »

ኤች አይቪ ተዘንግቷል?
መልዕክቱ ለሁሉም ነው ። ኤች አይ ቪ ኤድስ ጊዜ እንዳለፈበት በሽታ የሚቆጥሩ ይኖሩ ይሆናል ፤ ነገር ግን ዛሬም አለ ፤ ህጻን ፣ አዋቂ ፣ ወንድ ሴት ሳይል ሁሉንም ያጠቃል፤ ይገድላል። ለደሴ የአዲስ ተስፋ ማህበር ምስጋናችን ይድረሳችሁ 

ታምራት ዲንሳ

ነጋሽ መሐመድ