የኢጋድ ጉባኤና የሱዳን ተቃውሞ
ሐሙስ፣ ጥር 9 2016የኢጋድ ጉባኤና የሱዳን ተቃውሞ
የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ዛሬ ኢንቴቤ ኡጋንዳ ውስጥ ልዩ ጉባኤ አካሂደ ። በዛሬው የኢጋድ ልዩ ጉባኤ ላይ ከተካፈሉት መካከል የኡጋንዳ ፣የኬንያ፣ የጅቡቲ ፣የሶማሊያና የደቡብ ሱዳን መሪዎች እንዲሁም ኢጋድ የጋበዛቸው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል አዛዥም እንደሚገኙበት ተዘግቧል። ሆኖም የፈጥኖ ደራሹን ኃይል አዛዥ ጀነራል መሐመድ ሀምዳን ዳጋሎን ፣ኢጋድ ሳያማክራት በጉባኤው እንዲሳተፉ መጋበዙን የተቃወመችው ሱዳን በዛሬው ጉባኤ ላይ አልተገኘችም። የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር «የሱዳንን ሉዓላዊነት የሚጥስ» ባለው የኢጋድ የዳጋሎ ግብዣ ምክንያት ከባለስልጣኑ ጋር ያለውን ግንኙነት ለጊዜው ማቋረጡን ከትናንት ወዲያ ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ዳጋሎ በዛሬው የኢጋድ ጉባኤ ላይ መካፈላቸው ላይ የተሰጡ አስተያየቶች
ኢጋድ ዳጋሎን መጋበዙ ተገቢ ነው አይደለም የሚሉ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው። «ለለውጥ የምስራቅ አፍሪቃ ተነሳሽነት» የተባለው በሰላም ግንባታና ድርድር ላይ የሚሰራው ድርጅት የፕሮግራም ሃላፊ አቶ ገረሱ ቱፋ ለዶቼቬለ በሰጡት አስተያየት ኢጋድ ዳጋሎን በጉባኤ ላይ መጋበዙ የተለመደ አሰራር አይደለም ብለዋል። ይህም በኢጋድ የሽምግልና ሚና ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያሳድር እንደሚችልም ጠቁመዋል።በዚህ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የአፍሪቃ ቀንድ የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ አቶ አብዱራህማን ሰዒድ ግን የዳጋሎን መጋበዝ ኢጋድ ሁለቱን ወገኖች በዚህ መድረክ በማገናኘት ሰላማዊ መፍትሄ ላይ ለመድረስ የያደረገው ሙከራ አድርገው እንደሚያዩት ለዶቼቬለ ተናግረዋል።
ሱዳን ከኢጋድ ጋር ግንኙነቷን የማቋረጧ ምክንያት
ሱዳን ከድርጅቱ ጋር ግንኙነቷን የማቋረጥ ውሳኔ ላይ ደረስኩ ስላለችበት ምክንያት የተጠየቁት አቶ አብዱራህማን ሱዳን ምክንያቱ የዳጋሎ በጉባኤው ላይ መጋበዝ ነው ብትልም በርሳቸው ምልከታ በኢጋድ ላይ ያላት ጥርጣሬም ጭምር ለዚህ ያበቃት ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።ታዲያ ሱዳን ከኢጋድ ጋር ለጊዜው ግንኙነቷን ለማቋረጥ የደረሰችበት ውሳኔ እየተባባሰ ለሄደው የሱዳን ውጊያ መፍትሄ ያመጣ ይሆን? አተ ገረሱ ይህ ውሳኔ መፍትሔ ያመጣል የሚል እምነት የላቸውም። ከዚያ ይልቅ ሁኔታውን ያወሳስበበዋል ነው የሚሉት።
የሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎችን ለማግባባት የሚደረገው የሽምግልና ጥረት
የሱዳንን ወታደራዊ መንግሥትና የፈጥኖ ደራሹ ኃይል ውጊያ እንዲያቆሙ በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ሀገራት የተካሄዱ የሽምግልና ጥረቶች አልተሳኩም። ምክንያቱ ሁለቱ ወገኖች አለመሸናነፋቸው ነው የሚሉ እንዳሉ ሁሉ ለችግሩ ሸምጋዮችን የሚወቅሱም አልጠፉም። አቶ አብዱራህማን እንደሚሉት ዋነኛዎቹ ምክንያቶች ሁለቱ ወገኖች ጦርነቱን ሲጀምሩ አንዳቸው ሌላኛቸውን ለማጥፋት መነሳታቸውና በስልጣን ክፍፍል ላይ አለመግባባታቸው ናቸው። አተ ገረሱ ደግሞ የአደራዳሪዎች ተጽእኖና ፍላጎት ለድርድሮቹ አለመሳካት ምክንያት መሆናቸው አልቀረም ይላሉ።
ኢትዮጵያና የኢጋድ ጉባኤ
የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ)የዛሬው የኡጋንዳ ጉባኤ አጀንዳ ከሱዳን ግጭት በተጨማሪ ሶማሊያ የተቃወመችው የኢትዮጵያና የሶማሌላንድ የባህር በር የመግባቢያ ሰነድም እንደሚሆን አስቀድሞ ተነግሯል። በዛሬው ጉባኤ ላይ የሶማሊያው መሪ ቢገኙም ኢትዮጵያ ግን በተደራረቢ የጊዜ ሰለዳዎች ምክንያት በጉባኤው ላይ መካፈል እንደማትችል አስቀድማ አሳውቃለች።
ኂሩት መለሰ
ታምራት ዲንሳ