የኢትዮጵያ፣የጀርመንና የፈረንሳይ ሚኒስትሮች የጋራ መግለጫ
ዓርብ፣ ጥር 5 2015የኢትዮጵያ ፣ የጀርመን እና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ትናንት ማምሻውን በአዲስ አበባ ሸራተን አዲስ ሆቴል በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
የሁለቱ ሀገሮች ሚኒስትሮች በኢትዮጵያ ያደረጉት ጣምራ ጉብኝት ሀገራቱ ለኢትዮጵያ ያላቸውን አጋርነት የሚያሳይ ነው ሲሊ ምክትል እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናግረዋል።
ከሁለቱም ሀገሮች ጋር ታሪካዊ እና የቅርብ ወዳጅነት አለን፣ በወቅታዊ ፣ ሀገራዊ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች በዝርዝር መክረናል ያሉት ደመቀ መኮንን ሌሎች የጋራ ጉዳዮችንም በዝርዝር አስረድተናቸዋል ብለዋል። "በፕሪቶሪያ የተፈረመው የሰላም ስምምነት ወደ አፈፃፀም ገብቶ በጥሩ ሁኔታ እየቀጠለ እንደሆነ እና ይህም በቁርጠኝነት እንደሚተገበር አረጋግጠንላቸዋል። ተጠያቂነትን ለማረጋገጥና ለዚህም ሲባል የሽግግር ወቅት ረቂቅ ማእቀፍ ለሕዝብ ውይይት አቅርበን እየተንቀሳቀስን መሆኑን አቅርበናል" ብለዋል።
የጀርመን የፌደራል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ ከፈረንሳይ አቻቸው ጋር ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የተጀመረው የሰላም ስምምነት ገቢራዊነቱ እንዲጠናከር ለማገዝ፣ በተፈጥሮ አደጋ እና በጦርነትና ግጭት ምክንያት ለጉዳት ለተዳረጉ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸው የሚያደርገውን የሰብዓዊ ድጋፍ ለማየትና ለማጠናከር ብሎም በጦርነት ውስጥ ለደረሰ ጉዳት አጥፊዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማበረታታት መሆኑን ገልፀዋል። ጉብኝታቸው ትግራይ ክልልን ያካትት እንደሆን ለቀረበላቸው ጥያቄም ምላሽ ሰጥተዋል።
"በአመቱ መጨረሻ ጉብኝታችንን ለማድረግ እቅድ ስንይዝ የሰላም ስምምነት ሂደቱ ተጀምሮ ነበር። ሁለተኛ ጉዳይ የሆነው የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ተሻሽሎ እንዲሁም ተጠያቂነትን ማስፈን የሚለው ቅድመ ሁኔታ የነበሩ ጉዳዮች ሰሚ አግኝተዋል። ያለን ጊዜ ሁለት ቀናት ብቻ ናቸው። ስለዚህ በቂ ጊዜ የለንም" በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
በተመሳሳይ የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካትሪን ኮሎንና ጀርመንና ፈረንሳይ ባጠቃላዩም የአውሮጳ ሕብረት በሌሎች ዘርፎች ማለትም በግብርና ፣ በትምህርት እና በልማት ሥራዎች ከኢትዮጵያ ይሁን ከአፍሪካ በጋር እንደሚሰሩ እና የሚያደርጉትን ሁሉን አቀፍ ድጋፍም አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልፀዋል።
"በዚህ አመት ከኢትዮጵያ ጋር ያለን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመርንበትን 125 ኛ አመት እናከብራለን። ይህ ያለን ግንኙነት ምን ያህል ጠንካራ መሆኑን የሚያሳይ ነው" ብለዋል።
ከሰብዓዊ ድጋፍ ባሻገር በፖለቲካ ዘርፍ ያደረጋችሁት ድጋፍ ምንድን ነው ተብለው ተጠይቀውም " እዚህ ነን። ድጋፍ ለማድረግ እዚህ ነው ያለነው። ከዚህ በላይ ግን የሰብዓዊ ድጋፍ እያደረግን ነው። ባለፉት ሁለት ቀናት የአለም ምግብ ፕሮግራም ድርጅቶችን ጎብኝተናል። " ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ምክትል እና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን ፈረንሳይ ፣ ጀርመን እና አውሮፓ ኅብረት ለኢትዮጵያ የሚያደርጉትን የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
ተጠያቂነትን በተመለከተ የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላነሱት ሀሳብም ቀጥተኛ ምላሽ ሰጥተዋል።
"የተጠያቂነትን ጉዳይ በተመለከተ ሥጋትዎን እንገነዘባለን። ይሁንና ከዚህ በላይ የሚያሳስበው የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ነው። ቃል በገባንላችሁ መሰረት እዚህ ደረጃ ለመድረስና ቀውሱን በሰላም ለመፍታት የምንችለውን ሁሉ አድርገናል። አሁንም ይህንን ተፈፃሚ ለማድረግ ቁርጠኞች ነን። ስምምነቱ እየተተገበረ ነው። የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦቱ እየተሻሻለ ነው። የመሰረታዊ አገልግሎቶች ዳግም መጀመርም ተስፋ ሰጪ ሆኖ ቀጥሏል። የተጠያቂነት ጉዳይም በተመሳሳይ።
ለሕዝባችንና ለዜጎቻችን ኃላፊነት አለብን። በዚህ ጉዳይ እንደ መንግሥት ግልጽ የሆነ ምላሽ ለመስጠት ቁርጠኛ ነን። ከተባበሩት መንግሥታት እና ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጣምራ የምርመራ ውጤት በኋላ ወዲያውኑ ምክረ ሀሳቦችን ለመተግበር የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚቴ አቋቁመናል አሁንም ደከመኝ ሳይል ተጠያቂነት እንዲሰፍን እየሠራ ይገኛል። ይህ የእኛ ኃላፊነትና ተግባር ነው። በተጨማሪም አሁን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር በመሆን መርማሪ ባለሙያዎችን እንዲያስገባ ጋብዘናል። ስለዚህ ከዚህ ኮሚሽን ጋር በጣምራ በመሥራት መሬት ላይ ያለውን ሂደት መገምገም በጣም ጠቃሚ ነው። እናም እኛ ዜጎቻችንን የተመለከቱ ማንኛውንም ጉዳዮች ለመፍታት ግልጽ እና ክፍት ነን"
የጀርመን እና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተመሳዳይ ይዘት ያለው መግለጫ የሰጡ ሲሆን የተጀመረው የሰላም ስምምነት እንዲጠናከር ፍላጎታቸው መሆኑን እና ለአተገባበሩም ድጋፍ እንደሚያደርጉ፣ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት በተጠናከረ ሁኔታ እንዲቀጥል እና በደረሱ ጥፋቶች ላይ ተሳትፎ ያላቸው ሁሉ ተጠያቂ እንዲሆኑ የሚለውን በአፅንኦት ጠይቀዋል። ሚኒስትሮቹ ዛሬ ከአፍሪካ ሕብረት ባለሥልጣናት ጋር በልዩ ልዩ ጉዳዮች መምከራቸው ታውቋል።
ሰሎሞን ሙጬ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
አዜብ ታደሰ