1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያዉያን የሩጫ ባህል በኦሎምፒክ ሰሞን

ሐሙስ፣ ሐምሌ 18 2016

«የሩጫ ዉድድር ለኢትዮጵያዉያን ባህል ነዉ። ከሻንበል አበበ ቢቂላ የሮማ ኦሎምፒክ የማራቶን ድል ወዲህ በስፖርቱ መንደር የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ከፍ ብሎ እንዲዉለበለብ ያደረገ ነዉ። አትሌቲክስ የኢትዮጵያ መታወቅያ ነዉ።»

https://p.dw.com/p/4ih2Z
አበበ ቢቂላ በማራቶን ዉድድር በቼክ ሪፐብሊክ
አበበ ቢቂላ በማራቶን ዉድድር በቼክ ሪፐብሊክ ምስል Allsport Hulton/Archive/Getty Images

የኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ተሳትፎ እና የአትሌቶቹ ባህል

የኢትዮጵያዉያን አትሌቶች የኦሎምፒክ ተሳትፎ እና ቋሚ ባህላቸዉ

«የሩጫ ዉድድር ለኢትዮጵያዉያን ባህል ነዉ። ከሻንበል አበበ ቢቂላ የሮማ ኦሎምፒክ የማራቶን ድል ወዲህ በስፖርቱ መንደር የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ከፍ ብሎ እንዲዉለበለብ ያደረገ ነዉ። አትሌቲክስ የኢትዮጵያ መታወቅያ ነዉ።»

የአካል ማጎልመሻ መምህር እና የዓለም ክብረ ወሰንን የሰበሩ አትሌቶች አሰልጣኝ ስንታየሁ እሸቱ ከሰጡን አስተያየት የቀነጨብነዉ ነዉ ያደመጥነዉ። ጤና ይስጥልኝ አድማቾች እንደምን ሰነበታችሁ። አትሌቲክስ የኢትዮጵያ መታወቅያ ነዉ ያሉን፤ የሀገር ኩራት የሆኑ አትሌቶችን ለዓለም መድረክ ያበቁት አሰልጣኝ ስንታየሁ እሸቱ ናቸዉ። አሰልጣኝ ስንታየሁ እሸቱ፤ የአትሌቶች መፍለቂያ በሆነችዉ በትንሽዋ የኢትዮጵያ ከተማ በቆጂ ላይ ሆነዉ፤ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በዓለሙ የሩጫ ዉድድር መድረክ ከፍ አድርገዉ ያዉለበለቡ፤ ኢትዮጵያዉያንን ሁሉ በደስታ ያስተቃቀፉ አትሌቶችን አሰልጥነዋል።  

ስንታየሁ እሸቱ - የዓለም ክብረ ወሰንን የሰበሩ አትሌቶች አሰልጣኝ
ስንታየሁ እሸቱ - የዓለም ክብረ ወሰንን የሰበሩ አትሌቶች አሰልጣኝ ምስል Seyoum Getu/DW

ባለፉት አስርተ ዓመታት በዓለም እጅግ ፈጣን የሆኑ የርቀት ሯጮችንያፈራችዉ በአርሲ ዞን ዉስጥ የምትገኘዉ ትንሿ ከተማ በቆጂ ፤ ባፈለቀቻቸዉ አትሌቶች ምክንያት ለበርካታ ወጣቶች ብርታትን እና መነሳሳትን ፈጥራለች። ኢትዮጵያን ይዘዉ በአብዛናዉ ከኬንያዉያን አትሌቶች ጋር በዓለሙ የሩጫ ዉድድሮች መድረክ የሚፎካከሩት አትሌቶች፤ ነገ አርብ በሚጀመረዉ  በ 33ኛዉ የፓሪሱ የኦሎምፒክ ዉድድር ላይ ለመሳተፍ ወደ ፈረንሳይ ተመርቀዉ፤ በድምቀት ተሸኝተዋል። በፓሪሱ ኦሎምፒክ ላይ ከሚሳተፉት አትሌቶች መካከል አሰልጣኝ ስንታየሁ እሸቱ፤ በቆጂ ላይ  ሩጫን ያስጀመርዋቸዉ አትሌቶችም ተሳታፊዎች ናቸዉ። አሰልጣኝ ስንታየሁ እሸቱ ፤ የስልጠና ሞያዉን በ 1070 ዓም በአካል ብቃት አሰልጣኝነት ወይም የስፖርት አስተማሪ ሆነዉ በሃረር ከተማ ትምhreት ቤት መጀመራቸዉን ተናግረዋል።    

 የበቆጂ  እንቁዎች

ኢትዮጵያ በዓለም ላይ እጅግ ፈጣን የሆኑ የርቀት ሯጮችን የማፍራት ባህሏን ይዛ መቀጠልዋን ባለፉት አስርት ዓመታት አትሌቶችዋ ባስመዘገቡት ድል አስመስክራለች። አርሲ ዞን ዉስጥ ከምትገኘዉ ትንሿ ከተማ በቆጂ ከአትሌት ደራርቱ ቱሉ እስከ ቀኒሳ በቀለ፤ ጥሩነሽ ዲባባ እና እህቶችዋ ብሎም ሌሎች አትሌቶች  በቁጥር የላቅ ስኬት ያስመዘገቡ  ከዚህች ትንሽ ከተማ የፈለቁ ናቸዉ። በአንድ ወቅት ዓለምን ያስደመሙ አትሌቶች ይፈልቁባት በቆጂ አሁን አሁን ስመ ጥር አትሌቶችን እንደ ቀድሞ ማፍለቅ የተሳናት ይመስላል የሚል ጥያቄም ተነስቶባት ነበር። በወቅቱ አትሌት ደራርቱ ቱሉ ያስገኘችዉ ድል የከተማዋን ወጣት በከፍተኛ ሁኔታ አነሳስቶ በሩጫዉ ዓለም ከፍተኛ መነቃቃትን ፈጥሮ እንደነበር፤ አሰልጣኝ ስንታየሁ እሸቱ ተናግረዋል።  

የሮማዉ የማራቶን ድል

የኦሎምፒክ ዉድድርን በጎርጎረሳዉያኑ 1956 ዓ.ም መሳተፍ የጀመረችዉ ኢትዮጵያ፤ በ 1960 ዓ.ም በቶክዮ ኦሎምፒክ፤ጀግናዉ አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ የማራቶን ዉድድርን ማሸነፉን ተከትሎ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የስፖርት መድረክ ከፍተኛ ዝናን አገኘች። ከዝያ ጊዜ ጀምሮ ላለፉት ስድስት አስርተ ዓመታት ኢትዮጵያ የሯጮች ሃገር የሚል ስያሜ ተስቷታል። በማራቶን ዉድድር በባዶ እግሩ ሮጦ የሃገሩን ስም ያስጠራዉ አትሌት አበበ ቢቂላን ለመዘከር ብሎም የኢትዮጵያን የሩጫ ታሪክ  ህያዉ ለማድረግ የጀግና እግር በሚል ስያሜ ፤ በዓለም የሩጫ ዉድድር ላይ በባዶ እግሩ የሚሮጠዉ፤ የታላቁ ርጫ የቀድሞ ስራ አስክያጅ ኤርምያስ አየለ ነዉ።

ኤርምያስ አየለ በባዶ እግር ሯጭ በጣልያን ሮም
ኤርምያስ አየለ በባዶ እግር ሯጭ በጣልያን ሮምምስል privat

ኤርምያስ፤ በጣልያን ሮም፤ በግሪክ አቴንስ እንዲሁም በደቡብ ኮርያ ሲዮል ላይ በባዶ እግርህ የሩጫ ዉድድርን በመካፈልህ ትታወቃለህ፤ ቀደም ብለህ እንደተናገርከዉ አትሌት ዋሚ ቢራቱ ፤ አንተን ጨምሮ ወደ ፓሪስ የሚሄዱትን አትሌቶች በስቴድየም አግኝተዉ መርቀዋል፤ በባዶ እግራቸዉም ከአትሌቶቹ ጋር አጭር ርቀት ሮጠዋል።

በባዶ እግር ሯጭ

አትሌቲክስ ዉስጥ ብዙ ኖርያለሁ፤ በኢትዮጵያ የታላቁ ሩጫ ስራ ሥራ አስኪያጅ ነበርኩ ያለን ኤርምያስ አየለ፤ በባዶ እግሩ በዓለም የሩጫ ዉድድር መድረክ የሚሳተፈዉ ኢትዮጵያን የማስተዋወቅ ዓላማን ይዞም እንደሆን አጫዉቶናል። ኤርምያስ አየለ እነደ ሌሎቹ የሩጫ ዉድድር ተሳታፊዎች ሁሉ በ33ኛዉ የፓሪሱ የኦሎምፒክ ዉድድር ላይ በባዶ እግሩ በማራቶን ዉድድር ላይ ይሳተፋል። 

የበቆጂ እንቁዎች: ታላቁ ሩጫ በበቆጂ
የበቆጂ እንቁዎች: ታላቁ ሩጫ በበቆጂምስል Omna Tadel

በጎርጎረሳዉያኑ 1956 ዓ.ም ሜልበርን አውስትራሊያ፤ የኦሎምፒክ ዉድድርን የተቀላቀለችው ኢትዮጵያ በቀጣይ፤ በሮም፣ ቶኪዮ፤ ሜክሲኮ ሲቲ በማራቶን ዉድድር አሸንፋ፤ በጀግኖቹ ሻምበል አበበ ቢቂላና ማሞ ወልዴ ኢትዮጵያ በታሪክ ማህደር ስሟ በደማቅ ተጽፏል። በጎርጎረሳዉያኑ 1980 በሞስኮ ኦሎምፒክ፤ ማርሽ ቀያሪዉ በሚል ስያሜዉ የሚታወቀዉ በአትሌት ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር በ5ሺህ እና በ10ሺህ ሜትር ለሃገሩ የመጀመሪያዉን የወርቅ ሜዳልያ ያስገኘ፤ ብሎም በሩጫዉ ዘርፍ ቀጣዩን የኢትዮጵያ ትዉልድ ያበረታታ እና ደማቅ ታሪክን የፃፈ አትሌት ነዉ። በተለያዩ ምክንያቶች ኢትዮጵያ በኦሎምፒኩ መድረክ በተከታታይ ባትሳተፍም፤ አትሌቶችዋ በተሳተፉበት ሁሉ የወርቅ፤ የብርና የነሐስ ሜዳልያን አስገኝተዉ የኢትዮጵያ የሩጫ ባህል ታሪክ በኦሎምፒክ ማህደር ደምቆ እንዲቀጥል አድርገዋል።

የኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ሜዳልያ

ሻለቃ ደራርቱ ቱሉ፤  አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ፤ በዓለም የሩጫ ዉድድር መድረኮች የሃገራቸዉን ሰንደቅ ከፍ ብሎ እንዲዉለበለብ ያበቁ ሩጫንም የኢትዮጵያ ባህል እንዲሆን ያደረጉ አትሌቶች ናቸዉ።  በኢትዮጵያ የመጀመርያ የኦሎምፒክ ተሳትፎ ታሪክ ከጎርጎረሳዉያኑ 1956 ዓ.ም ከሜልበርኑ ኦሎምፒክ ዉድድር ጀምሮ እስካሁን ድረስ በተሳተፈችባቸዉ የኦሎምፒክ ጨዋታዎች፤ በአትሌቲክስ 22 የወርቅ፤ 11 የብር፤ እና 21 የነሐስ ሜዳሊያዎች በድምሩ 54 ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ፤ በአፍሪቃ ከኬንያ እና ከደቡብ አፍሪቃ ለጥቆ በሜዳልያዎች ብዛት በሦስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ኤርምያስ አየለ በባዶ እግር ሯጭ በጣልያን ሮም
ኤርምያስ አየለ በባዶ እግር ሯጭ በጣልያን ሮምምስል privat

ዶቼ ቬሌ በ 33 ኛዉ የፓሪስ ዉድድር ላይ ለሚሳተፉ አትሌቶች ሁሉ መልካሙን ይመኛል። ለቃለ-ምልልስ የቀረቡትን በዶቼ ቬለ ስም በማመስገን፤ ሙሉዉን ጥንቅር እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ