1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያና የጀርመን የጋራ ምርምር

ሐሙስ፣ ነሐሴ 19 2014

ምሁራኑ እንደሚሉት ከሆነ የሚያጠኑትን ናሙና ይዘዉ ወደ ጀርመን የሚመጡበት ዋና ምክንያት፤ በኢትዮጵያ ለምርምር የሚሆነ የረቀቀ ቴክኖሎጂ ቁሳቁስ ባለመኖሩ ብሎም፤ሃሳብና እዉቀትን ለመለዋወጥ ነዉ። የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በፍራንክፈርት ከሚገኘዉ ከጀርመኑ ዮሐን ቮልፍጋንግ ጎይተ ዩኒቨርሲቲ ለትብብር ስራ የመግባብያ ሰነድ ተፈራርሟል።

https://p.dw.com/p/4G3QC
Frankfurt | Die Forschungskooperation zwischen äthiopischen und deutschen Archäologen
ምስል privat

 

ጀርመኖቹ እኛ ሃገር መጥተዉ አብረን በጋራ ወደ ባሌ ተራራ ዋሻዎች በመሄድ ቂፋሮ አድርገን ነዉ እነዚህን ናሙናዎች የሰበሰብናቸዉ።»

በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የሥነ-ቁፋሮ ማለትም በአርኪኦሎጂ ሞያ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር አለምሰገድ ቤልዳዶስ የተናገሩትን ነበር ያደመጥነዉ። ኢትዮጵያዊዉ የአርኮሎጂ ባለሞያ  ዶ/ር አለምሰገድ ቤልዳዶስ፣ ወደ ሁለት ወር ገደማ ለምርምር ስራ ከኢትዮጵያዉያን ባልደረቦቻቸዉ ጋር ወደዚህ ወደ ጀርመን መጥተዉ ከጀርመናዉያን የሥነ ቁፋሮ እና ሥነ እፀዋት ባለሞያዎች ጋር ምርምር አድርገዉ ከቀናቶች በፊት ተመልሰዋል። ከአምስት ዓመታት ገደማ በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ  እና በፍራንክፈርት ጀርመን ከሚገኘዉ ዮሐን ቮልፍጋንግ ጎይተ ዩኒቨርሲቲ መካከል በተፈረመዉ የመግባብያ ሰነድ አማካኝነት ኢትዮጵያዉያን የሥነ-እፅዋት እና ሥነ ቁፋሮ ባለሞያዎች ለምርምር የትብብር ስራ በየዓመቱ ወደዚህ ወደ ጀርመን ይመጣሉ። ባለፈዉ ሰሞን ከጀርመን ምሁራን ጋር ያካሄዱትን ምርምር አጠናቀዉ የተመለሱት አራት ኢትዮጵያ የአርኮሎጂ እና የሥነ እፀዋት ተመራማሪዎች ዶ/ር አለምሰገድ ቤልዳዶስን ጨምሮ ፕሮፊሰር ሰብስቤ ደምሰዉ፤ ዶ/ር ኤርምያስ ልዑለቃል እና አቶ መላኩ ወንዲፍራዉ ይገኙበታል። ምሁራኑ እንደሚሉት ከሆነ የሚያጠኑትን ናሙና ይዘዉ ወደ ጀርመን የሚመጡበት ዋና ምክንያት፤ በኢትዮጵያ ለምርምር የሚሆነ የረቀቀ ቴክኖሎጂ ቁሳቁስ ባለመኖሩ ብሎም፤ ሃሳብና እዉቀትን ለመለዋወጥ ነዉ። የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በፍራንክፈርት ከሚገኘዉ ከጀርመኑ ዮሐን ቮልፍጋንግ ጎይተ ዩኒቨርሲቲ  ለትብብር ስራ የመግባብያ ሰነድ ከመፈራረሙ በፊትም ኢትዮጵያዉያን ምሁራን ወደ ጀርመን ለምርምር ይመጡ እንደነበር የሥነ ቅሪት ተመራማሪዉ  ዶ/ር አለምሰገድ ቤልዳዶስ ተናግረዋል። ይሁንና ባለፉት ሁለት ዓመታት በኮቪድ ምክንያት ለምርምር ጀርመናዉያኑም ወደ ኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያዉያኑም ወደ ጀርመን መምጣታ መሄዳችን ተቋርጦ ነበር ብለዋል። ተመራማሪዎቹ ወደ ጀርመን የሚያመጣቸዉ ዋንኛዉ ነገር በጀርመን ለምርምር ሥራ እጅግ ዘመናዊ መሳርያዎች ስለሚገኙ እንደሆነም ተናግረዋል።  

Frankfurt | Die Forschungskooperation zwischen äthiopischen und deutschen Archäologen
ምስል privat
Frankfurt | Die Forschungskooperation zwischen äthiopischen und deutschen Archäologen
ምስል privat

ኢትዮጵያዉያኑ ሳይንቲስቶች እንደተናገሩት በጀርመን በአርኪዮሎጂ ጥናት የቤተ ሙከራ ማለትም የላብራቶሪ ቁሳቁስ እጅግ የረቀቀ በመሆኑ ወደዚህ በየዓመቱ ይመጣሉ። በአሁኑ የመጡበት የምርምር ስራ የተሳካ እንደነበርም ተናግረዋል።   

እኛ ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ከባዮሎጂ ዲፓርትመንት የሥነ-እፅዋት ጥናት ተቋም ነዉ የመጣነዉ ያሉን አቶ መላኩ ወንዲፍራዉ፤ በፍራንክፈርት ጀርመን የአንድ ወር ቆይታቸዉ ምርምር ጥናት እንዲሁም ስልጠናንን እንዳገኙ ተናግረዋል።  

Frankfurt | Die Forschungskooperation zwischen äthiopischen und deutschen Archäologen
ምስል privat

ኢትዮጵያዉያኑ ተመራማሪዎች እንደተናገሩት ከጀርመናዉያኑ ባልደረቦቻቸዉ ጋር ሆነዉ  በኢትዮጵያ ከምድር ገጽ በታች ለብዙ ሺህ ዓመታት የተቀበሩ የዕፅዋት ቅሪተ አካልን ለይቶ ማወቅና ስለዕፅዋቱ ይዘት ምርምር ማድረግ ላይ ያተኩራል ብለዋል። ዶ/ር አለምሰገድ ቤልዳዶስ በበኩላቸዉ የጥንታዊ ዕፅዋት ቅሪት አካሎቹ የተሰበሰቡት በባሌ ተራሮችና በዎላይታ ዋሻዎች ውስጥ ከጀርመናዉያኑ የምርምር ቡድን ጋር በጋራ ባካሄዱት የቁፋሮና አሰሳ ነው ሲሉ ነዉ ያከሉት። 

እንደ ዶ/ር አለምሰገድ ቤልዳዶስ፤ ከጀርመናዉያኑ ጋር በኢትዮጵያ ባሌ ተራሮች አካባቢ የተገኘዉ ጥንታዊ እፅዋት ቅሪትን ማጥናት በቀድሞ ጊዜ የሰው ልጅ የአመጋገብ ሁኔታን ለማወቅ ፤ ባለፉት ሃምሳ ሺህ ዓመታት (50,000 ዓመታት) የአካባቢው  የአየር ንብረት ሁኔታ ምን ይመስል እንደነበር ለማወቅ፤ እንዲሁም በአካባቢዉ ላይ ያለዉን ለዉጥ የሰው ልጅ የአኗኗር ስልቶችን እና ቀጣይነታቸዉን እንዴት እንደነበር ለማወቅ ይረዳል። 

Frankfurt | Die Forschungskooperation zwischen äthiopischen und deutschen Archäologen
ምስል privat

ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ለምርምር ፤ለጥናት ብሎም ለአንዳንድ ትምህርቶች እና እዉቀት ልዉዉጦች ለአንድና ሁለት ወራት ወደዚህ ወደ ጀርመን መጥተዉ የነበሩት ኢትዮጵያዉያኑ ሳይንቲስቶች ከቀናቶች በፊት ወደ ሃገራቸዉ ተመልሰዋል። የዛሬ ዓመት ወደ ፍራንክፈርት ስንመጣ ዶቼ ቬለ ሬድዮን እንጎበኛልን ሲሉ ነዉ ከቃለ ምልልሳችን በኋላ ቃል ገብተዋል። ዶቼ ቬለ ኢትዮጵያዉያኑ ምሁራን ለሰጡን ቃለ ምልልስ በማመስገን ስራቸዉን ይበል ሲል ተሰናብቷቸዋል።

ሙሉ ቅንብሩን ለማድመጥ የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ!

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ