የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት አንድምታ
እሑድ፣ ነሐሴ 21 2015
ብራዚል ፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካን ባካተተው እና በእንግሊዥናው ምህፃሩ BRICS የሚባለው የአምስቱ ሀገራት ጥምረት 15ኛው ጉባኤውን በዚህ ሳምንት ማለትም ከጎርጎሪያኑ ከነሀሴ 22 እስከ 24/2023 በደቡብ አፍሪቃ ጅዋንስበርግ አካሂዷል። በዚህ ጉባኤ ስድስት አዳዲስ አባል ሀገራት ወደ ጉባኤው መቀላቀላቸው ተሰምቷል። ከነዚህ መካከል ያለፈው ያለፈው ሰኔ መጨረሻ 2015 ዓ/ም ለጉባኤው ጥያቄ ያቀረበችው ኢትዮጵያ አንዷ ነች። ሀገሪቱ የአምስቱን ሀገራት የኢኮኖሚ እና የንግድ ትብብር መቀላቀሏን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ትናንት በይፋዊ የቲዩተር ገፃቸው አስታውቀዋል።ጠቅላይ ሚኒስትሩዝርዝር ማብራሪያ ባይሰጡበትም ይህ ለኢትዮጵያ "ታሪካዊ ሁነት" ነው ብለዋል።ለመሆኑ ኢትዮጵያ የዚህ ጉባኤ አባል መሆኗ ምን ፋይዳ አለው? በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የፋይናንስ እና የመዋዕለንዋይ ፍሰት ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ሰዋለ አባተ ጠቀሜታውን በሶስት ከፍለው ያዩታል።«የዚህ ብሎክ አባል መሆን ሊያስገኝ የሚችለው አንዱ ጥቅም አንደኛው የኢኮኖሚ ትብብር ነው።በዚህ የኢኮኖሚ ትብብር ኢንቨስትመንትን እና ንግድን ከማበረታት ጋር ተያይዞ በተለይ በአባል ሀገራት ዙሪያ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ሪሶርስ እና ገበያ አለ ተብሎ ስለሚታሰብ እርስ በእርሳቸው በሚያደርጉት የንግድ ልውውጥ እና የኢንቨስትመንት ስራ ኢትዮጵያ ትልቅ የኢንበስትመንት መዳረሻ ትሆናለች ተብሎ ይታሰባል።»በማለት ገልፀዋል።ባለፉት አምስት እና ስድስት አመታት እንደ ሩሲያ እና ቻይና ያሉ አባል ሀገራት የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገባቸውን የጠቀሱት ባለሙያው ኢትዮጵያም አባል ሀገር መሆኗ የዚህ ትሩፋት ተቋዳሽ ዳንድትሆን ያደርጋታል ብለዋል። በሁለተኛ ደረጃ ለመሰረተ ልማት ግንባታ የሚውል ብድር እና እርዳታ ማግኘት ነው።«ሁለተኛው እነዚህ ብሎኮች አንዱ የሚሰሩበት ለመሰረተ ልማት ግንባታ ሊውል የሚችል የፋይናንስ ድጋፍ እና ብድር ለአባል ሀገራት መስጠት ነው።ስለዚህ ኢትዮጵያም የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ጅምር ከመሆናቸው የተነሳ ወደ ፊት ከፍተኛ የሆነ ሪሶርስ ይፈልጋል እና ለዚህ ግብዓት የሚሆን ድጋፍ እና ብድር ከእነዚህ ሀገራት ይገኛል ተብሎ ይታሰባል።በዋናነት ይህንን ለማገዝ ይህ ብሎክ በቅርቡ ተግባራዊ ያደረገው «ኒው ዲቨሎጵመንት ባንክ» የሚባል ተቋም አለ።በዚህ ተቋም አማካንነት እንደ ለመንገድ እና ተዛማጅ መሰረተልማቶች ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ታገኛለች ተብሎ ይታሰባል።»በማለት ሁለተኛውን የአባልነት ጥቅም አብራርተዋል።
ዶክተር ሰዋለ እንደሚሉት ኢትዮጵያ ከዚህ ቡድን የምታገኘው ሶስተኛው ዋነኛው ጥቅም በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተፅዕኖ መፍጠር ነው።
ያም ሆኖ የምዕራቡን ዓለም ጎራ ይቀናቀናል በሚባለው በዚህ ቡድን ኢትዮጵያ አባል መሆኗ በሀገሪቱ ላይ ጫና ሊያመጣ ጥቅሟንም ሊያሳጣት ይችላል የሚሉ አሉ።የኢትዮጵያ የአባልነት ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ትናንት በሰጡት መግለጫ ግን አባልነቱ «አንዱን ጎራ ትቶ አንዱን የመያዝ »እንዳልሆነ ገልፀዋል።ኢትዮጵያዊ ዲፕሎማሲዋ የሚታወቀው በገምቢ ገለልተኛነት እና በአለም አቀፍ መድረኮች በሁለትዮሽ ብቻ ሳይሆን የባለ ብዙ ወገን መድረኮች አራማጅ ናት። ብለዋል። እሳቸው ይህን ይበሉ እንጅ ዶክተር ሰዋለ ግን የምዕራቡ ጎራ ተፅዕኖ አይቀሬ ነው ይላሉ።«የተነሱበት ዋናው ዓላማ የ«ዌስተርን»ን ብሎክ ለመገዳደር እና የ«ኢመርጅንግ» ኢኮኖሚ ሀገራትን ጥቅም እያስከበረ አይደለም። የሚል ሀሳብ ይዘው ነው የተነሱት።ስለዚህ ከእነዚህ «ዌስተርን» ሀገራት ጋር ተገዳዳሪ ቡድን ነው።ያን ያህል «ፎርማል» የሆነ ተቋም ባይሆንም እስካሁን ድረስ ተገዳዳሪ ነው።ከዚህ አንፃር ወደዚህ ጎራ የሚሰለፉ ወይም የሚሳተፉ ሀገራት ተፅዕኖ ይደርስባቸዋል።»ካሉ በኋላ። እንደሩሲያ ብራዚል እና ህንድ ያሉ- ሀገራት ተፅዕኖውን በኢኮኖሚ አቅም ሲመክቱ መቆየታቸውን ገልፀዋል።እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ደካማ ኢኮኖሚ ያላቸው ሀገራት ግን ብድር እና እርዳታ የሚያገኙት ከምዕራቡ ዓለም በመሆኑ እና በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሀገራቱ በፖለቲካው ያላቸው ተፅዕኖ ቀላል ባለመሆኑ ነገሮች በነበረው ሁኔታ ሊቀጥሉ እንደማይችል አብራርተዋል። ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ከፍተኛ ተፅዕኖ ይጠብቃታል ብለዋል። ከዚህ አንፃር ተግዳሮቱን ለመቋቋም የሚያስችል አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።
ሰሙኑን ብሪክስ በደቡብ አፍሪቃ ባካሄደው አመታዊ ጉባኤ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ኢራን፣ ሳውዲ አረቢያ ፣የተባበሩት አረብ ኢመሬቶች፣ ግብፅ እና አርጀንቲናንም አባልነታቸው ተቀባይነት አግኝቷል።
የእነዚህ ሀገራት በቡድኑ መካተት፣የብሪክስን አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ከዓለም አቀፉ የሀገር ውስጥ ምርት ውስጥ 36 በመቶ ድርሻ ይይዛል። ከዓለም አጠቃላይ ህዝብም 47 በመቶውን ይወክላል።
ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ፀሀይ ጫኔ
ማንተጋፍቶት ስለሺ