የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብትና ተመድ፤ ያንዣበበው ረሐብ
ዓርብ፣ መስከረም 7 2014የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ትግራይ ክልል ውስጥ በሁሉም ተፋላሚ ወገኖች ከፍተኛ የመብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን መግለጡ የበርካቶች መነጋገሪያ ኾኗል። ድርጅቱ ከኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በጋራ ባካኼደው ምርመራ ያገኘውን ውጤት በሚመለከት ነበር መግለጫ የሰጠው። የኢትዮጵያ ውጩ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሰሞኑን የፀጥታው ምክር ቤት የታላቁ የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ላይ ሌላ መግለጫ አውጥቷል። ይህም ተጨማሪ የሳምንቱ የመነጋገሪያ ርእስ ነበር። በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተለይ በሕወሓት ቁጥጥር ስር በሚገኘው ሰሜን ወሎ ውስጥ ሰዎች ለብርቱ ረሐብ መጋለጣቸው እየተነገረ ነው። ትግራይ ክልል ውስጥም የረሐብ አደጋ መከሰቱ ቀደም ሲል ተነግሯል። በዚሁ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የጀርመን አፍሪቃ ሽልማት አሸናፊ መሆናቸው መነገሩም ትኩረት ስቧል።
በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተለይ በሕወሓት ቁጥጥር ስር በሚገኘው ሰሜን ወሎ ውስጥ ሰዎች ለብርቱ ረሐብ መጋለጣቸው እየተነገረ ነው። ወደ አካባቢው አንዳችም አይነት ርዳት ሳይገባ ለበርካታ ጊዜያት መቆየቱ የረሐብ እልቂት ሊያስከትል ይችላል ሲሉም በርካታ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎች ስጋታቸውን በመግለጥ እየወተወቱ ነው። የረሐብ አደጋ ከአማራ ክልል ባሻገር ትግራይ ክልል እና አፋር ክልል ውስጥም ስለመከሰቱ ቀደም ሲል አስተያየት ሲሰጥ ነበር።
ሩት ኦኬይ በሚል የትዊተር ስም ተጠቃሚ፦ «ስለ ወሎ ዝም አንበል፤ ሁላችንም ድምፅ እንሁን» ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል። ይህ ጉዳይ ሰብአዊነት የሚሰማውን ሰው በአጠቃላይ የሚመለከት መኾኑንም በእንግሊዝኛ ጽሑፍ አስፍረዋል። በአማርኛ «ወሎ» በሚል ተለቅ ባሉ ፊደላት ከተጻፈ ቃል ጋርም ሰውነታቸው እጅግ የገረጣ አንዲት አዛውንት እናት የደረቶቻቸው አጥንቶች እንዳገጠጡ በትካዜ አቀርቅረው የሚታዩበትን ፎቶግራፍም አያይዘዋል።
«ወሎ ወሎ ወሎ፤ ትኩረት እየተራቡ ላሉት ለሰሜን ወሎ ሕዝብ ቅድሚያ ለሰብአዊነት» የሚል ጽሑፍ በማስፈር ለዓለም የምግብ መርኃ ግብር እና ለተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) በትዊተር ጥሪ ያስተላለፉት ሁሴን ሞሐመድ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ ናቸው። አንሻ ሰዒድ በፌስቡክ ጽሑፋቸው፦ «አስቸካይ የስብአዊ ርዳታ ለወሎ» ብለዋል።
ዳዊት ኤም በትዊተር ጽሑፋቸው፦ «በሕወሃት ወረራ ሰሜን ወሎ እና ዋግኅምራ ውስጥ የተከሰተው የምግብ ቀውስ እጅግ ሲበዛ አሳሳቢ ነው። ቀውሱ ተደፋፍኖ ሊቆይ የማይችል ኾኗል» ብለዋል። ዓለም አቀፍ ርዳታ ለጋሾች እና የመገናና አውታሮችም ትኩረት እንዲሰጡ አድራሻዎቻቸውን በማስፈር ጠይቀዋል። ተመሳሳይ ጥያቄ በአማራ ክልል መንግስት ትናንት ቀርቧል። የአማራ ክልል መንግስት ዓለም አቀፍ ረጂ ተቋማት ተግባራዊ የሰብአዊ ርዳታ እንዲያደርሱ ጥሪ አስተላልፏል። የክልሉ መንግሥት ለመቆጣጠር የማይቻል እልቂት ይከሰታል ሲል አስጠንቅቋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባሳለፍነው ሰኞ ጄኔቫ ከተማ ውስጥ 48ኛ ዓመታዊ ጉባኤውን ሲያካኺድ የኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍልም ዋነኛ አጀንዳው ነበር። ድርጅቱ ከኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በጋራ ባደረገው ምርመራ በሰሜን ኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ሰላማዊ ሰዎች እየተሰቃዩ መኾናቸውን ገልጧል። ትግራይ ክልል ውስጥ በሁሉም ተፋላሚ ወገኖች ከፍተኛ የመብት ጥሰቶች መፈጸማቸውንም ዐስታውቋል። ግጭቱ በኢትዮጵያ ሌሎች ክልሎችም መሻገሩን የድርጅቱ የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሼሌ ባሼሌት ገልጠዋል።
ትዊተር ላይ ከአንድ መቶ ዐሥር ሺህ በላይ ተከታዮች ያሏት ጋዜጠኛ ሰሚራ ሳውላኒ የኮሚሽኗ መግለጫን አያይዛ ቀጣዩን አጠር ያለ ጽሑፍ ከመግለጫው ነቅሳ አስፍራለች። «ግጭቱ ተባብሶ ቀጥሎ ወደ አፋር እና አማራ ክልሎችም ተሻግሯል። ሰላማዊ ዜጎች እየተሰቃዩ ነው፤ ከተጠያቂነት ነጻ መሆን መስፋፋቱ ቀጥሏል» ሲል ይነበባል።
ኮሚሽነር ሚሼሌ ባሼሌት በኢትዮጵያ የተከሰተው ግጭት፦ «ወደ አፍሪቃው ቀንድ»ም እንዳይሰራጭ የሚያሰጋ መኾኑን ባወጡት መግለጫ ዐሳውቀዋል። ኮሚሽነሯ ስጋት ያሉትን አስተያየት የተቃረነው የሸበር ደርሶ የተባለ የፌስቡክ አስተያየት ሰጪ፦ «ይሄ ቀውስ ከምስራቅ አፍሪካ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም» ብሏል። «ሱዳንንና ግብፅ እንዲትያርፉ ንገሩልን ሌላው የውስጥ ችግር ነው» ሲሉም አክለዋል። ትግራይ 21 ግንቦት የሚል የትዊትር ስም ያለው ተጠቃሚ፦ «ትግራይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ግጭት መፍትኄው ሊገኝ የሚችለው በፖለቲካ ውይይት እና ንግግር ብቻ ነው» የሚል ጽሑፍ በትምህርተ ጥቅስ አስፍረዋል። «ሁሉም ወገኖች በአፋጣኝ ያለምንም ቅድመ ኹኔታ ባላንጣነታቸውን አክትመው የተኩስ አቁም ለማድረግ እንዲደራደሩ ጥሪ አቀርባለሁ» የሚለውን የኮሚሽነሯ አስተያየትንም አካተዋል። በከድር ሰዒድ የተባሉ ሌላ የፌስቡክ አስተያየት ሰጪ ደግሞ ኮሚሽነሯ ግጭቱ ወደ አፍሪቃ ቀንድ እንዳይሻገር ያሰጋኛል ማለታቸውን በአጭሩ፦ «የምእራባዊያን ምኞት» ብለውታል። ሕይወት ከበደ ደግሞ፦ «በቃ አትተዉንም ማለት ነው» ሲሉ ጠይቀዋል። የተባበሩት መንግሥታት እና የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽኖች በጋራ ያከናወኑት የመጨረሻ የምርመራ ውጤት ጥቅምት 22 ቀን፣ 2014 ዓም ይፋ እንደሚያደርጉ ዐስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የወቅቱ ፕሬዚደንት የ«ታላቁ የሕዳሴ ግድብ»ን በተመለከተ ያወጣውን አጠር ያለ መግለጫ በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል። መሥሪያ ቤቱ በመግለጫውም፦ የፀጥታው ምክር ቤት ግድቡን በተመለከተ በግልጽ ከተወያየ ከዘጠኝ ሳምንታት በኋላ ያወጣው መግለጫ ከዚህ ቀደም «ታይቶ በማይታወቅ መልኩ» መሆኑን ጠቁሟል። የፀጥታው ምክርቤት አባላት ጉዳዩን ሦስቱ ሃገራት በአፍሪቃ ኅብረት ስር ይመልከቱ ማለታቸውን ኢትዮጵያ እንደምታደንቅም ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በጽሑፍ ጠቅሷል። ኾኖም ምክር ቤቱ ከተሰጠው ኃላፊነት ውጪ የልማት እና የውኃ መብት ላይ መግለጫ ማውጣቱን «የሚያሳዝን» ብሎታል። ቱኒዝያ በፀጥታው ምክር ቤት ተራዋ ደርሶ የአፍሪቃ መቀመጫ ላይ ስትቀመጥ ምክር ቤቱን ያሳለፈውን ውሳኔ በማሳነስ ኃላፊነቷን አለመወጣቷንም መግለጫው ጠቅሷል። የምክር ቤቱ የአሠራር ልዕልና ሲጣስ አባላቱ ያን በማረቁ ረገድ ሚናቸውን እንዲወጡም ኢትዮጵያ ማሳሰቧን ውጭ ጉዳይ ገልጧል። የፀጥታው ምክር ቤት የወቅቱ ፕሬዚደንት መግለጫን በተመለከተ ሊመጡ የሚችሉ ጥያቄዎችን ኢትዮጵያ ዕውቅና እንደማትሰጥም ከወዲሁ በመግለጫው አሳስባለች።
መግለጫውን በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። ቢንያም አክሎግ በትዊተር በሰጡት አስተያየት፦ «እንደ ቱኒዝያ ያለ አፍሪቃዊ ሀገር አፍሪቃ መር አመራር ላይ እምነት ማጣቱ ያሳዝናል። አፍሪቃዊ የመሆን የበታችነት ስሜት የመሆኑ አመላካች ነው» ብለዋል። መንግሥቱ ሳህ በበኩላቸው ቀጣዩን ሐሳብ በትዊተር አስፍረዋል። «ቱኒዝያን ምን ነካት? በአፍሪቃ መቀመጫ ተቀምጣ ከአፍሪቃ ጋር መጻረሯ?» ሲሉም ጠይቀዋል። አማኒ አማነ የተባሉ ቱኒዝያዊ የትዊተር አስተያየት ሰጪ ደግሞ ለቢንያም አክሎግ ቀጣዩን መልስ ሰጥተዋል። «ቱኒዝያ ብቸኛዋ የዓረብ ሃገራት ተወካይ ናት። ይህ በመሆኑም የግብጽ ድምፅ ናት። ቱኒዝያ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ሦስቱ ሃገራት አንድ ላይ እንዲቀመጡ እና ሁሉንም የማይጎረብጥ ስምምነት በመፈለጉ ረገድ ሰላማዊ መፍትኄን ትደግፋለች» የሚል አስተያየት በእንግሊዝኛ ቋንቋ አስፍረዋል። ኾኖም ኢትዮጵያ አስገዳጅ ነገሮችን ለማድረግ ትሞክራለች ሲሉም ከሰዋል።
ዶክተር ጥሩሰው አሰፋ እዛው ትዊተር ላይ በሰጡት አስተያየት የፀጥታው ምክርቤት ችግር ያሉትን መግለጫ ነቅሰው አውጥተዋል። ነቅሰው ያወጡት ጽሑፍ፦ «የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የውኃ አሞላል እና የሥራ አተገባበር ላይ በሁሉም ወገን ተቀባይነት ያለው አሳሪ ስምምነት በአፋጣኝ አጠናቁ» ሲል ይነበባል። ይህ በራሱ ችግር ያለው መሆኑን ዶክተር ጥሩሰው ገልጠዋል።
ረቡዕ መስከረም 5 ቀን፣ 2014 ዓ. ም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ያወጣው አጠር ያለ መግለጫ፦ ሦስቱ ሃገራት የሚፈልጉትን ታዛቢ እንዲጋብዙ ያበረታታል። እንደ መግለጫው ከኾነ ግብፅ ብትፈልግ አሜሪካን ልትጋብዝ ትችላለች ማለት ነው። ኢትዮጵያ፤ ግብጽ እና ሱዳን ውይይታቸውን በፍጥነት እንዲጀምሩ እና በስቸኳይ ስምምነት ላይ እንዲደርሱም መግለጫው ይጎተጉታል።
አፍሪቃን ወክላ የፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ የምትገኘው ቱኒዝያ አባልነቷ ሊያበቃ ሦስት ወራት ይቀሯታል። አጠር ያለው የፀጥታው ምክር ቤት የወጣው የፀጥታው ምክር ቤት የወቅቱ ፕሬዚደንት በኾነችው አየርላንድ ነው። አየርላንድም አባልነቷ እንደ ቱኒዝያ ሁሉ ከሦስት ወራት በኋላ ያከትማል። ከአየርላንድ የፕሬዚደንትነቱን ተራ በሚቀጥለው ወር የምትረከበው ኬንያ ናት። ከዚያም በወሩ ሜክሲኮ ትተካ እና ኒጀር የጎርጎሪዮሱ 2021 የመጨረሻዋ ፕሬዚደንት ትሆናለች። እንዲያ እያለም በየወሩ ይቀጥላል።
አብርሃም የተባሉ ሌላ አስተያየት ሰጪ የቱኒዝያ እና አየርላንድ የተቀናጀ እንቅስቃሴን በመገምገም ቀጣዩን ጽፈዋል። «የታላቁ የሕዳሴ ግድቡ ጉዳይ አንዴ ወደ አፍሪቃ ከተመለሰ በኋላ ለምንድን ነው የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ጣልቃ የሚገባው። የውኃ ክፍፍል ውዝግብ የሚባል ነገርም ሰምቼ ዐላውቅም» ብለዋል። «ግብጽ አስዋን ግድብን ሱዳንም የራሷን ግድብ ገድበዋል። ለምድን ነው ኢትዮጵያን ለማደናቀፍ የሚሞክሩት?» ሲሉም አጠይቀዋል። «አሳሪ የሚባል ስምምነትም የለም» ሲሉም አክለዋል።
በዚሁ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የጀርመን አፍሪቃ ሽልማት አሸናፊ መሆናቸው መነገሩም በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች የድጋፍ እና የተቃውሞ አስተያየቶች ተሰንዝረዋል። ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ለሽልማት የበቁት በሕይወት ዘመናቸው ለሰብአዊ መብቶች መከበር ላደረጉት አስተዋጽዖ መሆኑን የጀርመን የአፍሪቃ ሽልማት አዘጋጆች ባወጡት መግለጫ ዐሳውቀዋል። ሽልማቱን በተመለከተ፦ የጌታ ኤክጅ በሚል የፌስቡክ ስም ተጠቃሚ፦ «ጎበዝ ነህ ይገባሃል፣ በርታ» ሲሉ ድጋፋቸውን ገልጠዋል። አንጃክስ ጦሶ የተባሉ ሌላ አስተያየት ሰጪም በአጭሩ፦ «ይገበዋል» ብለዋል። ቴዎድሮስ ሲሳይ፦ «መጠቀሚያ ለማድረግ በሽልማት መደለለል ተጀመረ» ሲሉ ሽልማቱ ላይ ጥርጣሬያቸውን ገልጠዋል። ኅሉፍ ገብረ ሥላሴ የተባሉ አስተያየት ሰጪ፦ «ለየትኛው ኢትዮጵያዊ ነው የተካራከረለት» ሲሉ ጠይቀዋል። ኦሪያ ኢትዮጵያ ደግሞ፦ «አይገባውም» ሲሉ በእንግሊዝኛ ጽፈዋል። «ጀግና ነው ይገባዋል ለእውነት እና ለፍትኅ ብቻ የቆሞ እውነኛ ሰው ናቸው፤ በጣም ደስ ይላል» ያሉት ደግሞ
አዲስ አገኝሁ ተስፍው ብዙ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ናቸው። ድጋፍ እና አስተያየት መስጠቱ ቀጥሏል። ዶ/ር ዳንኤልም በመጪው ኅዳር ጀርመን ውስጥ በሚዘጋጅ ይፋዊ ደማቅ ስነ ስርዓት ሽልማቱን እንደሚቀበሉም ተገልጧል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ