የኢትዮጵያ መንግሥት መግለጫ እና የተመድ ማሳሰቢያ
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 8 2015የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ክልል የሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞን የሽረ ከተማን ከደቡባዊ ዞን ደግሞ የአላማጣ እና ኮረም ከተሞች መቆጣጠሩን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አረጋግጧል። ከትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቐለ በ278 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘውን የሽረ ከተማ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ኃይሎች ትላንት መያዟን የትግራይ ማዕከላዊ ኮማንድ በክልሉ መገናኛ ብዙኃን በተላለፈ መግለጫ አስታውቆ ነበር። በመግለጫው «ጥምር ኃይሎቹ በተለያዩ ግንባሮች መጠነ ሰፊ ጥቃት እንደከፈቱ» የገለጸው የትግራይ ማዕከላዊ ኮማንድ «በርካታ ሰላማዊ ሰዎች እንደተገደሉ እና ነዋሪዎች እንደተፈናቀሉ» አመልክቷል። የኢትዮጵያ መንግሥት ግን «የመከላከያ ሠራዊት በከተሞች ጦርነት እንዳይደረግ የተከተለው ጥብቅ ዲሲፕሊን በሲቪሎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ አድርጓል» በማለት ዛሬ ከሰዓት በኋላ ባወጣው መግለጫ ከትግራይ ማዕከላዊ ኮማንድ የቀረበውን ውንጀላ አጣጥሏል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ «ከልዩ ልዩ የእርዳታ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት መከላከያ በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች ርዳታ በተሣለጠ መንገድ እንዲደርስ ዝግጅት» እየተደረገ እንደሆነ አስታውቋል። ለዚህም የሽረ አውሮፕላን ማረፊያን እንደሚጠቀም የገለጸው መንግሥት በሰሜን ጎንደር በኩል ወደ ሽረ የሚወስደውን እና ከኮምቦልቻ ደሴ፣ ወልድያ፣ ቆቦ አላማጣ ያለውን መንገድ ለመክፈት ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ትላንት አመሻስሽ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ «በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ ነው» ሲሉ ተናግረዋል።
«በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ ነው። ኹከት እና ውድመት ከአሳሳቢ ደረጃ ደርሷል። ማህበራዊ ግንኙነት እየተሰነጣጠቀ ነው። በትግራይ ያለው ግጭት አሁኑኑ መቆም አለበት። ይኸ የኤርትራ ወታደሮች ጥቃት አቁመው ከኢትዮጵያ መውጣታቸውን ይጨምራል። የጦርነት መፍትሄ የለም። ንጹሐን ሰዎችን ዋጋ እየከፈሉ ነው። በመኖሪያ አካባቢዎች ጭምር በጅምላ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በየቀኑ በርካታ ንፁሀን እየተገደሉ፤ ቁልፍ መሠረተ ልማቶችን እያወደሙ እና አንገብጋቢ አገልግሎቶች የማግኘት ዕድል እየተገደቡ ነው። በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በነሐሴ ግጭት እንደገና ከተቀሰቀሰ ወዲህ ተፈናቅለዋል። አብዛኞቹ ለሁለተኛ ጊዜ የተፈናቀሉ ናቸው። በሴቶች፣ ሕፃናት እና ወንዶች ላይ ወሲባዊ ጥቃት እና ሌሎች ጭካኔዎች መፈጸማቸውን የሚገልጹ ረባሽ ምስክርነቶች እየሰማን ነው።"
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ፎልከር ቱርክ የውጊያው መባባስ እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል። ከሦስት ሣምንታት ገደማ በፊት በኮሚሽነርነት የተሾሙት የ57 ዓመቱ ፎልከር ሁሉም ወገኖች ግጭት አቁመው ለሰላማዊ እና ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል። የትግራይ ማዕከላዊ ኮማንድ ትናንት ሰኞ ባወጣው መግለጫ «በትግራይ ክልል እየተፈጸሙ ያሉ የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰቶችን» ዓለም አቀፉ ማኅበረብ ተረድቶ አፋጣኝ መፍትሄዎችን መስጠት አለበት ብሏል።
ማህሌት ፋሲል
ልደት አበበ
ኂሩት መለሰ