1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የፈረሙት ስምምነት፡ የኦነግ ማሳሰቢያ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 30 2016

በአከባቢው ሁሉም አካላት ውጥረቱን በሰከነ አካሄድ እንዲፈቱት በጠየቀበት በዚሁ መግለጫ፤ ኦነግ በተለይም ለስደተኞች እና ሰላማዊ ዜጎች ጥበቃ ሊደረግ እንደሚገባ ነው ያሳሰበው፡፡ከዚህ በፊትም የሁለቱ አገራት መንግስታት በፈጠሩት እሰጣገባ ሶማሊያ ውስጥ በተጠለሉ የኦሮሞ ስደተኞች ላይ በታሪክ አጋጣሚ ተደጋጋ ጥቃት መሰንዘሩን አስታውሷልም፡፡

https://p.dw.com/p/4b1sz
ኦነግ ዉጥረቱ በሰላማዊ ሰዎች በተለይም በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ጠይቋል
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አርማ።ኦነግ የኢትዮ-ሶማሊላንድ ስምምነት የቀሰቀሰዉ ዉጥረት እንዳይባባስ አሳስቧልምስል Seyoum Getu/DW

የኢትዮ-ሶማሊላንድ ስምምነትና ኦነግ

 

የኢትዮጵያ መንግስት በለፈው ሳምንት መጀመሪያ ራስዋን የሶማሊላንድ ሪብሊክ ብላ ከምትጠራዉ ግዛት ጋር የመግባቢያ ሰነድ በመፈረሙ ሰበብ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል ዉጥረት መቀስቀሱ እንዳሳሰበው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አስታወቀ፡፡ኦነግ ባወጣዉ መግለጫ እንደሚለዉ ስምምነቱ  «የሚመለከታቸው» ያላቸዉን ወገኖች ማካተት ነበረበት። የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ መንግስታቸው ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገዉ ስምምነት ዲፕሎማሲያዊ ቀውስ እንዳያስከትል እንደሚጥር ባለፈዉ ሳምንት አስታዉቀዉ ነበር። 
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የኢትዮጵያ መንግስት እና የሶማሊላንድ ራስ-ገዝ አስተዳደር የፈረሙትን ይህን የመግባቢ ሰነድ በቃጣናው የውጥረት መንገስ ምክኒያት እንዳይሆን ያሰጋል ብሎታል፡፡ በአከባቢው ሁሉም አካላት ውጥረቱን በሰከነ አካሄድ እንዲፈቱት በጠየቀበት በዚሁ መግለጫ፤ ኦነግ በተለይም ለስደተኞች እና ሰላማዊ ዜጎች ጥበቃ ሊደረግ እንደሚገባ ነው ያሳሰበው፡፡ ፓርቲው በመግለጫው ከዚህ በፊትም የሁለቱ አገራት መንግስታት በፈጠሩት እሰጣገባ በሰላማዊ ዜጎች ላይ በተለይም ሶማሊያ ውስጥ በተጠለሉ የኦሮሞ ስደተኞች ላይ በታሪክ አጋጣሚ ተደጋጋ ጥቃት መሰንዘሩን አስታውሷልም፡፡
የኦሮሞ ህዝብ ከጎረቤት የሶማሊያ ህዝብ ጋር ለዘመናት ባህል፣ ወግ፣ ሃይማኖት እና ድንበር ተጋርቶ በሰላም መኖሩን ያወሳው ኦነግ በገዢዎች ተደጋግሞ በሚቀሰቀስ ግጭት ግን የሰው ህይወት እና ሃብት ስወድም መቆየቱን አመልክቷልም፡፡ ፓርቲው በመግለጫው ኦነግ እና ወንድም ህዝብ ባለው የሶማሊያ ህዝብ መካከል ለፍትህ እና ሰብኣዊ መብት መከበር ያደላ አዎንታዊ ግንኙነት መኖሩንም ገልጾ የጋራ ሰብኣዊ እሴት ያለው ይህ ግንኙነት እንዳይበላሽ የሶማሊያ ፖለቲከኞች፣ ምሁራን፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች እና ህዝብ አንቂዎች ጥሪ እንዲያሰሙም ጠይቋል፡፡

የኦነግ የፖለቲካ ኦፊሰር ፖለቲከኛ በቴ ዑርጌሳ በዚህ ላይ በሰጡን ተጨማሪ ማብራሪያም ፓርቲያቸውን ያሳሰበው አብይ ጉዳይ አስረድተዋል፡፡ “የኦሮሞ ማህበረሰብ ከሶማሊያም ሆነ ሶማሊላንድ ጋር አጎራባች ህዝብ እንደመሆኑ በበዛት ወደዚያ በመሄድ ህይወቱን የሚመሩ የብሔሩ ተወላጆች አሉ፡፡ ከዚህ በፊት ከታሪክ አጋጣሚ እንደምንረዳው አገራቱ መካከል ችግር ስኖሩ ሰላማዊ ዜጎች ስለሚጠቁ ያ እንዳይሆን ነው ጥሪውን ያሰማነው” ብለዋል፡፡

ሁለቱ መሪዎች የተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ የሶማሊያ መንግስትን አስቆጥቷል
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አሕመድና የሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሒ አብዲ ስምምነቱን ከመፈረማቸዉ በፊትምስል TIKSA NEGERI/REUTERS

 

ኦነግ በመግለጨው እንዳብራራው የፖለቲካ ውጥረቱ በተንሰራፋበት በዚህ አሳሳቢ ወቅት ሶማሊያ ውስጥ ለሚገኙ ለኦሮሞ እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ጥበቃ እንዲደረግ ነው ለተለያዩ የሶማሊያ ማህበረሰብ አካላት ባስተላለፈው በዚህ ጥሪ የጠየቀው፡፡ኦነግ አክሎም ውጥረቱን የቀሰቀሰውን ጉዳይ እንደምገነዝብ አሳውቆ በሂደቱ ሊፈጠር የሚችለውን የሰላማዊ ዜጎች በተለይም የስደተኞች ጉዳት እንዳያስከትል ግን እንዳሳሰበውም አስረድቷል፡፡ ፓርቲው በመግለቻው ከኦሮሚያም ይሁን ከመላው ኢትዮጵያ የተሰደዱ ስደተኞች ለሶማሊያ የተጣመመ አመለካከት እንደሌላቸው ግንዛቤ ውስጥ ሊገባ ይገባልም ነው ያለው፡፡ ስደተኞችም ሆኑ ሌሎች ሰላማዊ ዜጎች በንግድ እና ሌሎች መስተጋብሮች በሰላም ተሳስረው የመኖር ፍላጎታቸው እንዲጠብም ተጠይቋል፡፡

በመሆኑም በዚህ ፈታኝ ጊዜ የጋራ መስተጋብሮች በተለይም የሰላማዊ ዜጎች ደህንነትና ህይወትን ለመጠበቅ እንዲውሉ ሲል ነው ኦነግ የጠየቀው፡፡ ለመላው ሶማሌያውያን ብሎ ባስተላለፈውም ጥሪ ሰላማዊ ዜጎችን መጠበቅ የሞራል ግዴታ ሊሆን ይገባል ብሏል፡፡
ስለስምምነቱ ኦነግ ያለው ድጋፍ ወይም ተቃውሞ ላይም በዶይቼ ቬሌ የተጠየቁት ፖለቲከኛ ቤቴ ዑርጌሳ “መንግስት ስለጉዳዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ለአገር ውስጥ ባለድርሻ አካላት የሰጠው ማብራሪያ በቂ ባለመሆኑ ሂደቱን ለመደገፍም ሆነ ለመቃወም እንደምቸገሩ” አስረድተዋል፡፡ ፓርቲያቸው ትልቅ የህዝብ ቁጥር ያላት ኢትዮጵያ ወደብ እንደሚያስፈልጋት እንደሚያምንና ለመፍትሄውም ዓለማቀፍ ህግ ባልተቃረነና ሰላማዊ በሆነ መነግገድ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡  
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ለመላው ዓለማቀፍ ማህበረሰብ በተለይም ለተባበሩት መንግስታት፣ ለአፍሪካ ህብረት፣ ለአውሮፓ ህብረት እና ጎረቤት አገራት ብሎ ባስተላለፈው ጥሪ ግፊት ተደርጎ ሊከሰት የሚችለው አውዳሚ ያለው ግጭት እንዲቀርም ጠይቋል፡፡

የሶማሊላንድን ወደብ ለመጠቀም ከዚሕ ቀደም የተለያዩ ሐገራት ጥያቄ አቅርበዉ ነበር
አፍሪቃ ቀንድ ጫፍ ላይ የምትገኘዉ ሶማሊላንድ የአደን ባሕረ ሰላጤን የሚዋሰኑ በርካታ ወደቦች አሏት

 

ከኦነግ በተጨማሪም በዚህ ጉዳይ ላይ መግለጫ ያወጣው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትም (ኦነሰ) ጦርነት ቀስቃሽ ያለውን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስተዳደር ከሰሞኑ የወሰደው እርምጃ ነቅፎታል፡፡ የኦነሰ ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ በቀድሞ ትዊተር በአሁኑ ኤክ እንዳመለከቱት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር እርምጃ በቃጣናው ሰላምን የሚያውክ ብለውታል፡፡ አክለውም ነባር ያሉት የኦሮሞ እና ሶማሊ ህዝብ ትብብር እንዳይላላ የኦነሰ ቃል አቀባዩ በመልእክቱ ጠይቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ መንግስት እና ራስገዟ ሶማሊላንድ መካከል የትብብር የተባለው የጋራ ሰነድ መፈረሙን ተከትሎ በተነሳው ውዝግ ላይ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ የመንግስታቸው ዓላማ በጋራ መልማት ላይ የሚያተኩር መሆኑን አስረድተው፤ ሊፈጠሩ የሚችሉ ዲፕሎማሲያዊ ጫናን በማስረዳት እንደሚፈቱ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ስምምነቱን ተከትሎ ሉዓላዊነቴ ተደፍሯል ያለችው ሶማሊያ ተቃውሞዋን በማሰማት ለተለያዩ ዓለማቀፍ ማህበረሰብ ጥሪ ማቅረቧም አይዘነጋም፡፡

ሥዩም ጌቱ

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ