1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ እና የእስራኤል ግንኙነት

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 7 2010

አፍሪቃ ለብዙ ጊዜ የፍልስጤማውያን አጋር ሆና ነበር የቆየችው። በአሁኑ ጊዜ ግን ብዙ አፍሪቃውያት ሀገራት ከእስራኤል ጋር የጠበቀ ግንኙነት የመፍጠር ፍላጎት ነው ያጎሉት። እስራኤልም በምትሰጠው የልማት ርዳታ፣ የጦር መሳሪያ እና የተራቀቀ ቴክኖሎጂ የአፍሪቃውያኑን ትኩረት ለመሳብ እየሞከረች ነው።

https://p.dw.com/p/2pSW0
Äthiopien Addis Ababa Benjamin Netanjahu Staatsbesuch
ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Ayene

እስራኤል/አፍሪቃ

የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በጎርጎሪዮሳዊው 2016  ዓም ወደ አፍሪቃ ያደረጉትን ጉዞ ታሪካዊ አድርገው ተመልክተውታል። ምክንያቱም አንድ የእስራኤል መሪ ከብዙ አሰርተ ዓመታት በኋላ አፍሪቃን ሲጎበኝ ኔታንያሁ የመጀመሪያ ናቸው። ኔታንያሁ በኬንያ ፣ ዩጋንዳ ፣ ኢትዮጵያ እና ርዋንዳ ባደረጉት ጉብኝታቸው ተደስተው መመለሳቸው ተገልጿል።

የኬንያ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ የቤንያሚን ኔታንያሁን ጉብኝት አስመልክተው በሰጡት አስተያየት፣ ከእስራኤል ጋር እንደገና በአዎንታዊ የትብብር መሰረት ላይ የተመረኮዘ ጠንካራ ግንኙነት መጀመር እንደሚገባ ገልጸዋል። ኔታንያሁ ሌሎቹ ሶስት የምሥራቅ አፍሪቃ ሀገራትም ያደረጉት ጉብኝት ጥሩ እና የተሳካ ነበር። የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ከምሥራቅ አፍሪቃው ጉዟቸው በኋላም ባለፈው ሰኔ ወር በአፍሪቃ ለሁለተኛ ጊዜ ጉብኝት አካሂደዋል። በዚሁ ወቅት በላይቤሪያ በተካሄደው የምዕራብ አፍሪቃ መንግሥታት የኤኮኖሚ ትብብር ድርጅት፣ በምህጻሩ የኤኮዋስ ጉባዔ ላይ ንግግር አድርገዋል።የአፍሪቃ እና የእስራኤል ግንኙነት አንዴ ሞቅ አንዴ ቀዝቀዝ ሲል መቆየቱን፣ በወቅቱም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ በደቡብ አፍሪቃ ፕሪቶርያ የሚገኘው በምህጻሩ አይ ኤስ ኤስ የተባለው ዓለም አቀፉ የፀጥታ ጥናት ተቋም ተንታኝ ስቲቭን ግሩዝድ ለዶይቸ ቬለ ገልጸዋል። « የእሥራኤል መንግሥት የተቋቋመው በጎርጎሪዮሳዊው 1948 ዓም ነው።  በ1950 ኛዎቹ እና 1960ኛዎቹ  ከአፍሪቃውያት ሀገራት ጋር የነበረው የእስራኤል ግንኙነት በጣም ጠንካራ ነበር። በአፍሪቃ በልማት ስራ ላይ የተሰማሩ ብዙ እስራኤላውያን ነበሩ፣ በእስራኤልም ብዙ አፍሪቃውያን ተማሪዎች ትምህርታቸውንት ይከታተሉ ነበር፣ ከ30 የሚበልጡ የአፍሪቃ ሀገራት ኤምባሲዎችም በእስራኤል ነበሩ። ፀረ ቅኝ አገዛዝ ስሜታቸው ሁለቱን ወገኖች አቀራርቦ ነበር። እስራኤላውያኑ የብሪታንያን ቅኝ አገዛዝ አብቅተዋል፣ አፍሪቃውያኑም ይህንኑ በማድረግ ላይ ነበሩ። በዚህም የተነሳ ግንኙነታቸው ጥብቅ ነበር።»

Kenia Besuch des israelischen Ministerpräsidenten Netanjahu
ምስል picture-alliance/AA/Kenyan Presidency

ይኸው በ1950 ኛዎቹ እና 1960ኛዎቹ በሁለቱ መካከል የታየው ግንኙነት በእስራኤል እና በጎረቤቶችዋ ዐረባውያት ሀገራት መካከል በቀጠለው ውዝግብ የተነሳ እክል አጋጥሞት ነበር። ዐረባውያት ሀገራት በ1967 ዓም በእስራኤል ላይ የጣሉትን ጥቃት ተከትሎ የእስራኤል ጦር  በስድስቱ ቀናት ጦርነት የግብፅን የሲናይ ልሳነ ምድር  መያዙ አይዘነጋም። ግብፅ እስራኤል የአፍሪቃን መሬት ይዛለች ስትል በተመድ ከሳለች።

የእስራኤል ዐረቦች ወዝግብ ከዚያ በተከተሉት ዓመታትም እየተጠናከረ በመሄዱ ዐረባውያቱ ሀገራት አፍሪቃ ከእስራኤል ጋር ያለቸውን ግንኙነት እንዲያቋርጡ በአንድነት ጥረት አድርገዋል። ጥረታቸውም መሳካቱን ስቲቭን ግሩዝድ ያስታውሳሉ። በዚያን ጊዜ ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማቲክ ግንኙነት ከነበራቸው ሀገራት መካከል ግንኙነታቸውን የቀጠሉት አራቱ ብቻ ነበሩ። የአፍሪቃ ህብረትም የታዛቢነቱን አቋም ለፍልስጤማውያን እንጂ፣ ለእስራኤል አልነበረም የሰጠው። አሁን ግን በአፍሪቃ እና በእስራኤል ግንኙነት ላይ ለውጥ ተይቷል። አፍሪቃ በእስራኤል አኳያ ትከተለው የነበረው የማግለል አሰራር እየጠፋ የመጣ ይመስላል። የቀድሞው የሊቢያ መሪ ሞአመር ኧል ጋዳፊ ከስልጣን ከተወገዱ ከጎርጎሪዮሳዊው 20111 ዓም ወዲህ በአፍሪቃ ህብረት ፀረ እስራኤሉን ስሜት የሚያራምድ ወገን አይታይም።

Liberia Israelischer Ministerpräsident Benjamin Netanjahu bei ECOWAS
ምስል picture-alliance/AA/Israeli Prime Ministry Press Office

እንደ የዓለም አቀፉ የፀጥታ ጥናት ተቋም ተንታኝ ስቲቭን ግሩዝድ አስተያየት፣ የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ሳምንት ትህሳስ ስድስት፣ 2017 ዓም ኢየሩሳሌምን የእስራኤል ዋና ከተማ ናት ብለው እውቅና በሰጡበትም ጊዜ ከአፍሪቃ የጎላ የተቃውሞ ድምፅ አለመሰማቱ ይህንኑ ለውጥ የሚጠቁም ነው።
«እንደሚመስለኝ አፍሪቃውያን ፖለቲከኞች በተጨባጭ ሁኔታ ላይ ነው የሚያተኩሩት። ቀደም ባሉት ዓመታት ያደርጉት እንደነበረው ለርዕዮተ ዓለም ብዙም አይጨነቁም። ለፍልስጤማውያን ያላቸው ድጋፍም በፊት እንደነበረው ጠንካራ እና ሁለንተናዊ አይደለም።»

ከዚህ በተጨማሪ እስራኤል ለአፍሪቃውያኑ የምታቀርበው ርዳታም ሚና መያዙን የፖለቲካ ታዛቢዎች ይናገራሉ። ለምሳሌ፣ ይህ ሚና አፍሪቃ ሀገራት በሽብርተኝነት አንፃር በሚያደርጉት ትግል ላይ የሚታይ ነው።  የፅንፈኛ ቡድኖች  አዘውትሮ በሚያካሂዷቸው ጥቃት አሳሳቢ ስጋት በተደቀነባቸው ኬንያን በመሳሰሉ ሀገራት ይህ የእስራኤል ትብብር የያዘው ትርጓሜ ከፍ ያለ ነው። በመገናኛ ብዙኃን ዘገቦች መሰረት፣ በጎርጎሪዮሳዊው 2013 ዓም በኬንያ መዲና በዌስትጌት የገበያ አዳራሽ አሸባሪዎች የጣሉትን ጥቃት ተከትሎ የእስራኤል ጦር ኃይል ቡድኖች ኬንያውያኑን አቻዎቻቸውን ጋር በቅርብ ተባብረው መስራታቸው ተገልጿል። 

የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በ2016 ዓም የአፍሪቃ ጉዟቸውም ወቅት ለኬንያ ተጨማሪ ርዳታ ለመስጠት ቃል መግባታቸውን ዘገቦቹ አክለው አስታውቀዋል። ሀገራቸውም የሽብርተኞች ጥቃት ሰለባ መሆኗን የጠቀሱት እስራኤላዊው መሪ  ከአፍሪቃውያኑ ጋር ተባብሮ መስራቱ ሽብርተኝነትን ለማጥፋት የተጀመረው ትግል የተሳካ እንደሚያደርገው አመልክተዋል፣ በዚሁ ረገድም ዶይቸ ቬለ ያነጋገራቸው ኬንያዊው የፖለቲካ ተንታኝ ማርቲን ኦሎ እንደሚሉት፣ እስራኤል ለአፍሪቃ የምታደርገው ድጋፍ በጉልህ የሚታይ ነው።

«እስራኤል የጦር ድጋፍ፣ ስልጠና እና መሰል ርዳታ ለመስጠት ሁሌም ዝግጁ ነው። እንዲያውም፣ በአፍሪቃ በከፍተኛ ቦታ ላይ የሚገኙ ግለሰቦችን የሚጠብቁት አዘውትሮ እንደሚታየው በእስራኤል የሰለጠኑ ናቸው። ስለዚህ እስራኤል ለአፍሪቃ የምትሰጠው በጣም ብዙ ስልታዊ፣ ወታደራዊ እና የፀጥታ ጥበቃ ድጋፍ አሁንም ቀጥሏል።» 

እስራኤል ለአፍሪቃ ከምትሰጠው የጦር ድጋፍ ጎንም የልማቱን ርዳታም አጠናክራለች።አሁን ከተያዘው ታህሳስ ወር መጀመሪያ ገደማ ወዲህ እስራኤል እስከ ጎርጎሪዮሳዊው 2030 ዓም ድረስ ለ 66 ሚልዮን አፍሪቃውያን ኮሬንቲ የማቅረብ ዓላማ ባለው  ፓወር አፍሪቃ በተሰኘው የዩኤስ አሜሪካ ፕሮዤ ውስጥ መሳተፍ ጀምራለች፣ አፍሪቃ ከተራቀቀው በተለይም፣ በግብርናው ዘርፍ ካለው የእስራኤል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የምትሆንበትም እድል ይጠቀሳል።

Nairobi Kenia Terroranschlag Al-Shabaab Einkaufszentrum Westgate Mall
ምስል picture-alliance/AP Photo

ይሁን እንጂ፣ እስራኤል ከአፍሪቃ ጋር ትብብሯን ለማሳደግ የምታደርገው ጥረት የራሷን ጥቅም የማስጠበቅ ዓላማ እንዳለው ተንታኞች ይናገራሉ። ኔታንያሁ በአፍሪቃ ጉዟቸው ወቅት ሀገራቸው በአፍሪቃ ህብረት ውስጥ የታዛቢነት አቋም እንዲሰጣት ያላቸውን ፍላጎት  ደጋግመው ሲናገሩ ተደምጠዋል። እስራኤል ይህን የታዛቢነት አቋም የማግኘት ፍላጎትዋ 54 አባል ሀገራት ያሉትን የአፍሪቃ ህብረት ሙሉ ድጋፍ  የማግኘት ዓላማ ሲኖረው፣ ይህ  በተመድ እና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ ወደፊት በእስራኤል አንጻር የብዙኃን ተቃውሞ እንዳይነሳ ለማከላከል እንደሚረዳ ጠቅላይ ሚንስትር መናገራቸውን  ታይምስ ኦፍ ኢዝራኤል የተባለው የሀገራቸው ዕለታዊ ጋዜጣ አስታውቋል። 

ይሁን እንጂ፣ እንደ ፖለቲካ ተንታኞች አስተያየት፣ ይህ እስራኤል ከአፍሪቃ ጋር  እያጠናከረችው ያለው ትብብር ኔታንያሁ ያሰቡትን ዓላማ በርግጠንነት ያሳካል ለማለት አይቻልም። በብዛት ሙስሊም ዜጎች ያሏቸው ሞሮኮ፣ ሴኔጋል፣ ሞሪታንያ ወይም ሱዳንን የመሳሰሉ ሀገራት እስራኤልን በጥርጣሬ ነው የሚመለከቱዋት። ሱዳን ለምሳሌ የእስራኤል ዜጎች ወደ ሀገሯ እንዲገቡ አትፈቅድም። ሞሪታንያም እስራኤል እአአ በ2010 ዓም የጋዛ ሰርጥን በደበደበችበት ጊዜ ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማቲክ ግንኙነቷን አቋርጣለች።  

ደቡብ አፍሪቃ ደግሞ አአአ እስከ 1994 ዓም ድረስ ከውሁዳኑ የነጮች መንግሥት ጋር የጠበቀ ግንኙነት በነበራት እስራኤል አኳያ ቁጥብነት የታከለበት ግንኙነት ነው ያላት። በእስራኤል እና በአፍሪቃ መካከል በቶጎ ጉባዔ ለማድረግ እቅድ ቢኖርም፣ እቅዱ እስከዛሬ በእቅድ ደረጃ ብቻ እንደሚገኝ እና መቼ እንደሚደረግም የሚታወቅ ጉዳይ እንደሌለ ተገልጿል።

አርያም ተክሌ/ዳንየል ፔልስ

እሸቴ በቀለ