1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውስሽቪትዝ መታሰቢያ

ማክሰኞ፣ ጥር 12 2012

ስፍራው ሰዎች ለኢሰብዓዊ ባርነት የሚዳረጉበት የሚራቡበት በግቢው ጠባቂዎች በተደጋጋሚ የሚደበደቡበትና የጅምላ ጭፍጨፋም የሚፈጸምበት ቦታ ነው።ወደ አውስሽቪትዝ በከብት ማመላለሻ ባቡሮች ይጋዙ ከነበሩት ሰዎች  ወደ ካምፑ ሳይሆን በቀጥታ በጋዝ ታፍነው ወደ ሚገደሉበት አስከሬናቸውም ወደ ሚቃጠልበት እና አመዱ ወደሚነሰነስበት ስፍራ የሚወሰዱት ያመዝናሉ።

https://p.dw.com/p/3Wbrp
Auschwitz Soundgalerie Flash-Galerie
ምስል AP

የአውስሽቪትዝ መታሰቢያ 75 ተኛ ዓመት


በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የጀርመኑ የናዚ ሥርዓት ጀርመን ሰዎችን በጅምላ ይገድልና ያሰቃይ የነበረበት ፖላንድ የሚገኘው የአውስሽቪትዝ የሰዎች ማጎሪያ ካምፕ በሶቭየት ህብረት ወታደሮች ነጻ ከወጣ የፊታችን ሰኞ 75ኛ ዓመቱን ይደፍናል።ይህ ዕለት ጎርጎሮሳዊው ጥር 27፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በአውሮጳ ከጎርጎርያኑ 1941 እስከ 1945 ናዚ ጀርመን ይሁዲዎች ላይ የፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል መታሰቢያ ዕለትም ነው። በስፍራው ናዚዎች 1.1 ሚሊዮን ሰዎች በግፍ ጨፍጭፈዋል ተብሎ ይታመናል። ከተገደሉት አብዛኛዎቹም አይሁዶች ናቸው።የፊታችን ሰኞ የዓለም መሪዎች እና 200 ያህል ከዚያን ጊዜው ማጎሪያ በሕይወት የተረፉ ሰዎች በሚገኙበት በዚህ ስፍራ የመታሰቢያ ስነ ስርዓት ይካሄዳል። ደቡባዊ ፖላንድ ውስጥ የሚገኘው የአውስሽቪትዝ ማጎሪያ በጎርጎርያኑ 1947 ለጎብኚዎች ክፍት ከተደረገ ወዲህ ከ25 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ጎብኝተውታል። በየዓመቱም ከ2 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ስፍራውን ይጎበኛሉ። የዶቼቬለው ጁልያን በርነር በቅርቡ አውስሽቪትዝን ከጎበኙት መካከል አንዱ ነው።እርሱና ሌሎች ስፍራውን ለመጎብኘት የመጡ ሰዎች በጀርመንኛ «ስራ ነጻ ያወጣል»የሚል ጽሁፍ ከላይ በተቀረጸበት በር ነው ወደ ግቢው ዘልቀው የገቡት።እውነታው ግን ሌላ ነው።ስፍራው ሥራ ነጻ የሚያወጣበት ሳይሆን ሰዎች ለኢሰብዓዊ ባርነት የሚዳረጉበት፣የሚራቡበት በግቢው ጠባቂዎች በተደጋጋሚ የሚደበደቡበት እና የጅምላ ጭፍጨፋም የሚፈጸምበት ቦታ ነው።ወደ አውስሽቪትዝ በከብት ማመላለሻ ባቡሮች ይጋዙ ከነበሩት ሰዎች ወደ ካምፑ ሳይሆን በቀጥታ በጋዝ ታፍነው ወደ ሚገደሉበት አስከሬናቸውም ወደ ሚቃጠልበት እና አመዱ ወደሚነሰነስበት ስፍራ የሚወሰዱት ያመዝናሉ።የጎብኚዎችን ስሜት ከሚፈታተኑት ክፍሎች መካከል የሰዎች አስከሬን የሚቃጠልበት ስፍራ አንዱ ነው።የሶቭየት ህብረት ጦር ስፍራውን ከመያዙ አስቀድሞ ናዚ ጀርመን አብዛኛዎቹን የግፍ መፈጸሚያ ቦታዎች ቢያቃጥልም ይህ ክፍል ግን ሳይወድም ቀርቷል።ስፍራውን ለመጎብኘት ከድሬስደን የመጣችው ወጣቷ አስተማሪ ካትሪና ወደ ጨለማው እና የታፈነው ክፍል ስትገባ የጠቆረው የአሰስከሬን ማቃጠያና ጭስ ማውጫውን ስታይ በእድሜዋ ደርሶባት የማያውቅ ሀዘን እንደተሰማት ተናግራለች።
«በጣም ስሜት የሚነካ ነበር።በተለይ የመጨረሻውን ሰዎች የሚገደሉበትን ስፍራ ስመለከት፤ሰዎች እንዴት ይገደሉ እንደነበረ ሳይ፣ የጠቆረውን ኮርኒስ ስመለከት እና ሰዎች የሚቃጠሉበት ስፍራ መሆኑን ይህን የፈጸሙትም አረመኔ የሚባሉት ብቻ ሳይሆኑ ተራው ሰው ጭምር ይህን ማድረጉን ስሰማ እና ሳውቅ በእውነት በእጅጉ ተሰምቶኛል።  እንደሚመስለኝ ይህ እንደገና ሊፈጸምም ይችላል።እናም ስለ አጠቃላዩ ጥፋት ማሰብ፣የታሪክ መጻህፍትን ማንበብ እና እዚህ ተገኝቶም የሆነውን ማየት እና ግንዛቤ መጨበጥ በጣም አስፈላጊ ነው።እንደ አስተማሪ በተለይ ስለዚህ ጉዳይ ለወጣቶችም ለአዋቂዎችም መናገር ያስፈልጋል።ሁሉም ገለልተኛ አይደለም።
በወቅቱ በተገደሉ አይሁዶች ጫማዎች የተሞላው ክፍል በስፍራው የተፈጸመውን ግድያ መጠን ለመገመት ይረዳል።በዚሁ የሕይወት መጸሐፍ በተባለው ክፍል ውስጥ የአውስሽቪትዝ ሰለባ አይሁዶች ስም ዝርዝር የሰፈረበት ባለ 16 ሺህ ገጽ ጥራዝ ይገኛል።በዚሁ ጥራዝ ላይ የሰዎቹ ስም ዝርዝር ሐገርና ከተሞቻቸው ጭምር ሰፍሯል።ከፖላንድ ከሶቭየት ህብረት ከጀርመን ከኦስትርያ ከሃንጋሪ ከቼኮዝሎቫክያ ከግሪክ ከዮጎዝላቪያ ከኢጣልያ ከቤልጂግ ከኔዘርላንድስ ፈረንሳይ እና ከኖርዌይ የተለያዩ ከተሞች የተጋዙ ይገኙበታል።በስፍራው በግፍ ከተገደሉት 1.1ሚሊዮን ሰዎች ውስጥ 90 በመቶው አይሁዶች ናቸው። በዚህ ስፍራ የሚገኘው ሌላው ክፍል በተለይ በአውሮጳ ሮማ ሲንቲ ወይም ጂፕሲ ተብለው በሚጠሩት የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የተፈጸመውን ግፍ ያሳያል።ቁጥራቸው 21 ሺህ እንደሚደርስ የተገመተ ጂፕሲዎች በዚህ ቦታ በጋዝ ታፍነው ተገድለዋል።ሌሎች 75 ሺህ የፖላንድ ዜጎች፣ ከማዕከላዊ እስያ የመጡ ሙስሊሞችን ጨምሮ 15 ሺህ የሶቭየት ህብረት የጦር ምርኮኞችም በዚህ ስፍራ ህይወታቸው አልፏል።ባለፉት ዓመታት አውስሽቪትዝን ከጎበኙት 2 ሚሊዮን ሰዎች መካከል ወጣት አሜሪካውያኑ ጥንዶች ሜሪና ብራድ መጀመሪያ የጎበኙት አውስሽቪትዝ አንድ የተባለውንና በቀድሞ ወታደራዊ ጦር ሰፈሮች ታስረው የነበሩ አብዛኛዎቹ የፖላንድ እስረኞች የሚገኙበትን ስፍራ ነበር።ቀጥለው የጎበኙት ከዚህ ስፍራ በሦስት ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ቢርከናው በተባለ ስፍራ በ17o ሄክታር ላይ የተሰራ ከኤሌክትሪክ ጋር የተገናኘ የሽቦ አጥር እና የጥበቃ ማማ ያለው በጋዝ አፍኖ መግደያ እና አስከሬን ማቃጠያ ያለበትን ስፍራ ነበር።ጥንዶቹ ሜሪና ብራድ እንደተናገሩት ይህ ስፍራ ከሌሎቹ የማጎሪያ ማዕከላት ይለያል።
«ይህ ካምፕ በፊት ካየነው በጣም ይለያል። በሌላኛው ካምፕ ህንጻዎቹ ከነሙሉ መረጃዎቻቸው ሁሉም ወደ ቤተ መዘክርነት ተቀይረዋል።ይህኛው ግን ቀድሞም እንደነበረ ነው።አልተነካም።የኖሩባቸው የጦር ሰፈሮች በሙሉ እንዳሉ ናቸው።በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በየቀኑ ይመጡባቸው የነበሩ ተሽከርካሪዎችም አሉ ።በጣም ተደምሜያለሁ።በጣም የተለየ ነበር።በትምሕርት ቤት በተደጋጋሚ የተማርኩትን በአካል ማየት መቻል በተለይም ድርጊቱ ብዙም ሩቅ በማይባል ጊዜ መፈጸሙን ማወቅ መንፈስን ይረብሻል።»
የቤተ መዘክሩ አንዱ ክፍል ትኩረት የናዚ ርዕዮተ ዓለም ነው።ይኽም የናዚ ባለሥልጣናትን ፀብ አጫሪ ቀስቃሽ ፀረ ሴማዊነት ንግግሮችን እንዲሁም የአይሁዶች ጥያቄ ብለው ለሚያነሱት ጉዳይ የመጨረሻ መፍትሄ ለመስጠት የሚያቀርቡትን ጥሪ አካቷል። ፓውል ሳቪኪ የአውስሽቪትዝ ቤተ መዘክር የህዝብ ግንኙነት መኮንን ናቸው።ጎብኒዎች ከናዚ ጀርመን ታሪክ ፣በተለይ ርዕዮተ ዓለሞች በጥንቃቄ መያዝ እንዳለባቸው ትምሕርት መወስድ አለባቸው ይላሉ። 

Polen, Ausschwitz: KZ Gedenkstätte Auschwitz-Birkenau
ምስል picture-alliance/A. Widak
Polen KZ Trzebinia
ምስል picture-alliance/akg-images
Eingangstor und Schienen zum Vernichtungslager Auschwitz-Birkenau
ምስል Alex Pantcykov/dpa/Sputnik/picture-alliance

«በዓለማችን በብዙ ቦታዎች የጥላቻ አስተሳሰቦች ውጤቶችን ማየት እንችላለን።በብዙ ቦታዎች ሰዎች ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ይፈጸሙባቸዋል፤ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች እየጨመሩ ነው።የዘር ማጥፋት ወንጀሎች በግድያዎች አይደለም የሚጀምሩት።ሁሌም ከርዕዮተ ዓለም ነው የሚነሱት።ለእነዚህ ዛሬ ለሚፈጸሙ አስፈሪ እና እኩይ ተግባራት  በ40 ዓመታት ውስጥ ሌላ መታሰቢያ ሊኖር ይችላል።ያኔም ስለ ዛሬ ስለሆነው ጥያቄ የሚያነሳ ጎብኚ ይኖራል።»
ሰዎች ጭካኔ በተሞላበት መንገድ በግፍ ሲገደሉ እና ሲሰቃዩ የነበረበትን ይህን ቦታ ለመጪው ትውልድ ጠብቆ ለማቆየት ሃላፊዎቹ የበኩላቸውን እየጣሩ መሆኑን ይናገራሉ።ሆኖም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ከ75 ዓመት እድሜ በላይ ያስቆጠረው የዚህ ስፍራ ይዞታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ ሄዷል።ችግሩን ለማስወገድም አንድ የጋራ ዓለም አቀፍ ጥረት ከተጀመረ አሥር ዓመት ተቆጥሯል ይላሉ ከአውስሽቪትዝ የትምሕርት ማዕከል  ሉካስ ሊፒንስኪ 
«ግለሰብ ጎብኚዎች በራሳቸው ያለ ክፍያ ሊጎበኙ ይቻላሉ።በሚከፈላቸው አስጎብኚዎች አማካይነትም መጎብኘት ይቻላል።የመንግሥት ተቋም እንደመሆናችን ገንዘብ የሚገኘው ከመንግሥት ነው።ከግለሰቦች ከተቋማት እና ፎልክስ ቫገንን ከመሳሰሉ ኩባንያዎችም እገዛ እናገኛለን።በጎርጎሮሳዊው 2009 ቦታውን እንዳለ ለማቆየት የሚያስችል ገንዘብ የሚያሰባስብ አውስሽቪትዝ ቢርከናው የተባለ ድርጅት ተመስርቷል።በቅርቡ ስፍራውን የጎበኙት የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ለድርጅቱ ተጨማሪ 60 ሚሊዮን ዩሮ እንደሚለግሱ ተናግረዋል።ይህ ከጀርመን መንግሥት የሚሰጥ የመጀመሪያ እርዳታ አይደለም።በቤተመዘክሩ ውስጥ የሚያገለግሉ በርካታ በበጎ ፈቃደኞችም አሉ።»
አውስሽቪትዝን የጎበኙ ሁሉም ቦታውን ማየት አለበት ይላሉ።በነርሱ አስተያየት ከአውስሽቪትዝ በሕይወት የተረፉት አድሜ አሁን ከ90 ዓመት በላይ መሆኑ ታሪኩን የማስተላለፍ ድርሻ የቀጣዩ ትውልድ ነው።ኤርና ደ ፍሪስ ከአውስሽቪትቭ ተርፈው አሁንም በሕይወት ካሉ ጥቂት ሰዎች አንዷናቸው።እኚህ የ95 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ እናታቸው አይሁድ ፤አባታቸው ደግሞ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ነበሩ።ደ ፍሪስ ከእናታቸው ጋር በ1943 ነበር ወደ አውስሽቪትዝ የተጋዙት።እዚያም ሲደርሱ ከእናታቸው ለዩዋቸው።ያኔ በሕይወት እንደማላገኛት አወቅኩ ብለዋል።
«እናቴን መሰናበት በካምፑ ቆይታዬ ከገጠመኝ አስቸጋሪ ሁኔታ ከባዱ ነበር።ከአውስሽቪትዝ ተመልሳ እንደማትወጣ አውቅ ነበር።»
የደ ፍየሪስ እናት አውስሽቪትዝ እንደሞቱ ይገመታል።አሁን በቅጡ መናገርም ሆነ መስማት የሚያዳግታቸው ደ ፍየርስ አውስሽቪትዝ ወጣትነቴን ቀምቶኛል ይላሉ።
«የኔ ወጣትነት ተሰርቋል። ሁሌም በብሔራዊ ሶሻሊዝም ናዚ ተጽእኖ ስር ነበር።ብዙ ጥላቻ የተንሰራፈበት ነበር።በተለይ እንደህጻን ተገልዬ መቆየቴ በጣም መጥፎ ነበር።»ይላሉ ደ ፍሪስ 

Polen, Ausschwitz: KZ Gedenkstätte Auschwitz-Birkenau
ምስል picture-alliance/dpa/A. Weigel

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ