የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት የኢትዮጵያ ጉብኝት
ማክሰኞ፣ ኅዳር 30 2012የአፍሪቃ ህብረት መቀመጫ አዲስ አበባ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የመጀመሪያዋን ሴት የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት አስተናግዳ ሸኝታለች።ኮሚሽነር ኡርሱላ ፎን ዴር ላየን ሃላፊነታቸውን በይፋ በተረከቡ በሳምንቱ ነበር ወደ ኢትዮጵያ የሄዱት።በዚሁ ሃላፊነታቸው ፣የመጀመሪያቸው በሆነው የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ከኢትዮጵያ መንግሥት መሪዎች እና ከአፍሪቃ ህብረት ሃላፊ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተነጋግረዋል። ፎን ዴር ላየን ጋር ወደ አዲስ አበባ የተጓዘው የዶቼቬለ ዘጋቢ ቤርንት ሬግይርት እንዳለው የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው በአጠቃላይ 17 ሰዓታት ብቻ ነው የፈጀው።በአጭሩ ቆይታቸውም ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ ከኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና ከአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ጋራ የተወያዩት ፎን ዴር ላየን ይላል ቤርንት የመዝናኛም ይሁን ከተራ ዜጎች ጋር የመነጋገሪያ ፋታ አልነበራቸውም።ይህ የፎን ዴር ላየን የኢትዮጵያ ጉብኝት አጭርም ቢሆን ትኩረት ስቧል።በአዲሱ ሃላፊነታቸው ለምን የመጀመሪያ ጉብኝታቸውን በአፍሪቃ አደረጉ የሚል ጥያቄም ማስነሳቱ አልቀረም። ኮሚሽነሯ የመጀመሪያውን ጉብኝታቸውን በአፍሪቃ ያደረጉበትን ምክንያት አዲስ አበባ ውስጥ ከአፍሪቃ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ማህመት ፋኪ ጋር ከተነጋገሩ በኅላ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
«ከአውሮጳ ውጭ የመጀመሪያውን ጉብኝቴን በአፍሪቃ ማድረግን መርጫለሁ።በአፍሪቃ ህብረት መገኘቴ ጠንካራ ፖለቲካዊ መልዕክት ያስተላልፋል።ምክንያቱም የአፍሪቃ ክፍለ ዓለም እና የአፍሪቃ ህብረት ለአውሮጳ ህብረት እና ለህብረቱ ኮሚሽን አስፈላጊ ናቸውና።»
በክፍለ ዓለሙ እጅግ ፈጣን እድገት በማስመዝገብ ላይ ያሉ ኤኮኖሚዎች መኖራቸው እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ ሌሎችም የክፍለ ዓለሙ ከፍተኛ ተግዳሮቶች፣የመጀመሪያ የሥራ ጉብኝታቸውን በአፍሪቃ ያደረጉበት ተጨማሪ ምክንያት መሆኑንም አስረድተዋል።አውሮጳውያን እና አፍሪቃውያን ከጉርብትናም በላይ የጋራ እጣ ፈንታም አለንም ብለዋል ኮሚሽነሯ።የተጣበበ ጊዜ ይዘው ወደ አፍሪቃ ህብረት የሄዱት ፎን ዴር ላየን ለጋዜጠኞች ሲናገሩ ለአፍሪቃ ሰፊ እቅድ አዘጋጅተው ሳይሆን መጀመሪያ ለማዳመጥ እንደመጡ ነው ያስረዱት። የአውሮጳ ህብረት ታናሽ እህት ተደርጎ የሚቆጠረው የአፍሪቃ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ የእስካሁኑ የሁለቱ ህብረቶች ትብብር እንዲሻሻል ይፈልጋሉ።በዚህ ረገድ በተለይ ክፍለ ዓለሙን ያሳስባል የሚሉት አሸባሪነት ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ይላሉ።እናም በርሳቸው እምነት በዚህ ጉዳይ ላይ ከአውሮጳ ህብረት ጋር ይበልጥ ተቀራርቦ መስራት ያስፈልጋል።
«የእያንዳንዱ ሃገር የመረጋጋትእና የዓለም ሰላም አደጋ የሆነውን ይህን ስጋት ለመዋጋት፣ ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማንቀሳቀስ ከአውሮጳ ህብረት ጋር ይበልጥ ተቀራርቦ መሥራት ያስፈልጋል።ከአውሮጳ ጋር ያለን አጋርነት ብዙ ቅርጽ ያለው ሲሆን በጣም በሰፊውም አድጓል። በመጪው ዓመት በ2020 ተጨማሪ እርምጃዎችን መመውሰድ እንችላለን ብለን እናምናለን»
በጎርጎሮሳውያኑ የካቲት 2020 የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን እና የአፍሪቃ ህብረት ኮሚሽን አዲስ አበባ የጋራ ስብሰባ ይኖራቸዋል።በመጪው ዓመት ጥቅምት ደግሞ የአፍሪቃ እና የአውሮጳ ሃገራት መሪዎች ጉባኤ በብራሰልስ ይካሄዳል።የአውሮጳ ህብረትም ሆነ የአፍሪቃ ህብረት ኮሚሽን ለየክፍለ ዓለማቸው ጉዳዮች ሃላፊነት ይወስዳሉ።ሆኖም 8 የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ብቻ ያሉት የአፍሪቃ ህብረት ኮሚሽን ስልጣን አናሳ ሲሆን ሊያስተባብር የሚገባቸው ጉዳዮች ግን በርካታ ናቸው።የአፍሪቃ ህብረት እንደ አውሮጳ ህብረት የሕግ አውጭነት ሚና የለውም።ሃገራት ለሚስማሙባቸው ጉዳዮች ተገዥ እንዲሆኑ ማስገደድም አይችልም።ይሁን እና አውሮጳ ህብረት እንደሚያደረገው ፣55ቱ የአፍሪቃ ህብረት አባል ሃገራት ርዕሳነ ብሄራትና መራህያነ መንግሥትም ጉባኤዎች ያካሂዳሉ።ለዚህ ዓላማም 55 ርዕሳነ ብሄራትና የመንግሥታት መሪዎችን ማስተናገድ የሚችሉ ክፍሎች የሚኖሩት ቅንጡ ሆቴል አዲስ አበባ ውስጥ ይሰራል።ይህ ግዙፍ ግንባታ በሚካሄድበት ስፍራ ላይ ያሉ ምልክቶች እንደሚያሳዩት የቻይና ኩባንያዎች እና የፋይናንስ አቅራቢዎች በዋናነት ተሳታፊ ናቸው።ፎን ዴር ላየን ፣ቻይና ከኢትዮጵያ እና ከሌሎች የአፍሪቃ ሃገራት ጋር ባላት የኤኮኖሚ ትብብር እና በምትሰጠው ብድር ከባድ ተጽእኖ እንደምታደርግ ያውቃሉ።እናም በርሳቸው እምነት የአውሮጳ ህብረት ከእጁ ያመለጡትን እነዚህን የመሳሰሉ እድሎች መልሶ በእጁ ለማስገባት ብዙ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል።ሆኖም የአፍሪቃ ህብረት ዲፕሎማቶች በዚህ ጉዳይ ላይ በሚነሱ ውይይቶች በግልጽ እንደሚናገሩት አፍሪቃውያን ከማን ጋር እንደሚሰሩ እና ከማን ጋር እንደማይሰሩ የሚወስኑት ራሳቸው ናቸው።የቻይናም ይሁን የአውሮጳ ህብረት የልማት እና የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ምርጫም በሚያቀርቧቸው ሁኔታዎች ተሽሎ የተገኘውን እንደሚመርጡ ነው የሚናገሩት።
በፎን ዴር ላየን የአዲስ አበባ ቆይታ የአውሮጳ ህብረት ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት እና በግንቦት ለሚካሄደው ምርጫ የ170 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ እንደሚሰጥ አስታውቋል።ከዚህ ውስጥ 10 ሚሊዮኑ በዚህ ዓመት ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው ምርጫ ግልጽ እና ነጻ እንዲሆን ታስቦ የተለገሰ መሆኑ ተገልጿል።ፎን ዴር ላየንን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው ያነጋገሩት የዘንድሮው የኖቤል የሰላም ተሸላሚ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ግን ከፍተኛ ፍላጎት ስላለን ተጨማሪ ገንዘብ ያስፈልገናል ሲሉ ጠይቀዋል።ዐቢይ አህመድ ሥልጣን እንደያዙ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ሰላም ለማውረድ ባደረጉት ጥረት የተሸለሙትን የሠላም ኖቤል ዛሬ ተረክበዋል። ባለፈዉ ቅዳሜ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ጋር የተነጋገሩት ፎን ዴር ላየን ዐቢይ ኖቤል በመሸለማቸዉ ደስታቸውን ገልፀውላቸዋል።
በአውሮጳ ህብረት አስተያየት አሁን በአስቸኳይ መፍትሄ ከሚያሻቸው የአፍሪቃ ጉዳዮች መካከል የአየር ንብረት ለውጥ፣ትምሕርት እና ለወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር እንዲሁም ስደት ዋነኛዎቹ ናቸው።ለነዚህ ሁሉ ተግዳሮቶች ግን አሁን መልስ የለኝም ነው ያሉት ፎን ዴር ላየን ከአፍሪቃ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህመት ፋኪ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ።
«እውነት ለመናገር ለነዚህ ሁሉ ተግዳሮቶች መልስ የለኝም።ሆኖም በጋራ መልስ መፈለግ እንችላለን ብዬ አምናለሁ።በህብረት ለአውሮጳም ለአፍሪቃም የሚሰራ ጥሩ መፍትሄ ማግኘት እንችላለን።በውይይታችን እንደተገነዘበው በአውሮጳና በአፍሪቃ መካከል የበለጠ የትብብር ሥራ ማካሄድ የሚያስችል ቦታ አለ።
በአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት በፎን ዴር ላየን ምኞት የሁለቱ ህብረቶች አጋርነት ተጨባጭ ውጤቶች እና የሚታዩ ለውጦችን ማምጣት አለበት።ከአፍሪቃ ህብረት ጋር የሚከናወነው ሥራም እየተሻሻለ ሊሄድ ይችላል።ይህን በተመለከተ በሁለቱ ህብረቶች መካከል ባለው የጋራ ትብብር የተገኙት ተጨባጭ ለውጦች ምን እንደሆኑ ዶቼቬለ የጠየቃቸው ፎን ዴር ላየን ሲመልሱ
«ለውጦች አሉ ግን ግን በምንፈልገው ፍጥነት እየሄደ አይደለም።ለኔ ዋናው ነገር ከፕሮጀክቶቹ የትኛዎቹ ሰሩ የትኛዎቹ አልሰሩም ብለን የምንከታተልበት መንገድ ነው።በተጨባጭ ያስገኘውን ስኬት እና በወረቀት ላይ የሰፈረውን መለየት መቻል አለብን።»
ፎን ዴር ላየን በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ጋርም ተነጋግረዋል።ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በአሁኑ ጊዜ በአፍሪቃ ብቸኛዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲሆኑ ፎን ዴር ላየን ደግሞ የመጀመሪያዋ ሴት የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ናቸው።በውይይታቸው ካተኮሩባቸው ጉዳዮች መካከል በአፍሪቃ የጾታዊ ተዋጽኦ ጉዳይ ይገኝበታል።በአፍሪቃ ልጃገረዶች እና ወጣት ሴቶች እንዴት የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ማድረግ ይቻላል የሚለው ሁለቱ ከተነጋገሩባቸው ጉዳዮች ውስጥ ናቸው።ኢትዮጵያ በካቢኔዋ ጾታዊ ተዋጽኦን በማመጣጠን ከዓለም ልዩ ቦታ ትይዛለች። ኡርዙላ ፎን ዴር ላየን ግን በኮሚሽናቸው ይህን ሊያሳኩ አልቻሉም። አንድ የአፍሪቃ ዲፕሎማት ከርሳቸው ጋር ለተጓዘው የዶቼቬለ ዘጋቢ ቤርንት ሪግይርት «እዚህም ከኢትዮጵያ መማር ይቻላል ሲሉ ነግረውታል።
ቤርንት ሬግየርት
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ