አፍሪቃ አሜሪካውያን እና የአሜሪካ ምርጫ
ዓርብ፣ ሐምሌ 26 2016ዲያስፖራ አፍሪቃውያኑ ካማላ ሃሪስን ለመደገፍ ባካሄዱት ስብሰባ፣በአሜሪካ ኮንግረስ አባል የሆኑት የአፍሪቃ ተወላጆቹ ኢልሃን ኦማር እና ጋቢ አሞ ንግግር አድርገዋል። አፍሪቃ አሜሪካውያኗ የአሜሪካ ኮንግረስ አባል ኢልሃን ኦማር፣ ካማላ ሃሪስ እምነት የሚጣልባቸው መሪ መሆናቸውን ይናገራሉ።
እምነት የተጣልባቸው ካማላ ሃሪስ
«ካማላ ሃሪስ ቀጣዩ ፕሬዝደንታችን ለመሆን ብቁ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ አገራችን ልትመካባቸው የምትችልባቸው በጣም አስደናቂና እምነት የሚጣልባቸው መሪ ናቸው።» ሌላኛው አፍሪቃ አሜሪካዊ የኮንግረስ አባል ጋቢ አሞ በበኩላቸው፣ ካማላ ሃሪስን በተመለከተ ተከታዩን አስተያየት ስጥተዋል።
«በታሪካችን በጥንካሬ እና በልምዳቸው ብቁ ሆነው ለፕሬዚዳንትነት እጩ ለመሆን የተዘጋጁ ሰው ናቸው።» በዚሁ በበይነ መረብ በተካሄደው ስብሰባ ላይ፣ ሌሎች አፍሪቃ አሜሪካውያን ተመራጮችንና የማኀበረሰብ መሪዎች ተሳትፈዋል።
በአፍሪቃ አሜሪካውያኑ የተነሱ ሀሳቦች
በቤቶች፣ በምጣኔ ሃብት፣ በፖሊስ፣ በፍትሕ ማሻሻያ፣ በምግብ ደህንነት፣ በትምህርት መርኀ ግብሮች እንዲሁም በዓለም አቀፍ ግንኙነት በተለይም በአፍሮ ካሪቢያን አሜሪካ ግንኙነት ላይ መክረዋል። ከአራት ዓመት በፊት የነበረው የዶናልድ ትራምፕ የሥልጣን ዘመን በስደት አሜሪካ ለሚኖሩ አስቸጋሪ እንደነበር ያወሱት ተወያዮቹ፣ እርሳቸው ተመርጠው እንደገና ወደ ኋላ መመለስ አንፈልግም ብለዋል። በመሆኑም ካማላ ሃሪስ ተመርጠው ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ፣ የሚቻላቸውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
ካማላ ሃሪስና ዶናልድ ትራምፕ በአትላንታ
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ካማላ ሃሪስ የዲሞክራቲክ ፓርቲው ተጠባቂ ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ ከሆኑ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ፣ አትላንታ በሚገኘው የጆርጂያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው የምረጡኝ ቅስቀሳ አካሄደዋል።
ጆርጂያ የዘንድሮውን የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤት ከሚወስኑ ቁልፍ ግዛቶች ዋነኛዋ ስትሆን፣ ከወዲሁ ወደ ነጩ ቤተመንግሥት የሚወስደው መንገድ በጆርጂያ በኩል ነው እየተባለ ይገኛል።
በነገው ዕለት በተመሳሳይ፣ የሪፐብሊካኑ ዕጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ለምርጫ ዘመቻ ወደ አትላንታ እንደሄዱ ይጠበቃል።
ካማላ ሃሪስ በአትላንታ ባካሄዱት የምረጡኝ ቅስቀሳ፣ መካከለኛ ገቢ ያላቸው አሜሪካዊያንን የሚደግፍ ፖሊሲ እንዳላቸው ተናግረው፣ የትራምፕ ዕቅድ ግን መካከለኛውን መደብ እንደሚያዳክም ገልጸዋል። ከድንበር ጥበቃ ጋር በተገናኘ፣ ከሪፐብሊካኑ የሰላ ሂስ እየተሰነዘረባቸው የሚገኘው ካማላ ሃሪስ፣ በአሜሪካና በሜክሲኮ ድንበር ላይ የሁለትዮሽ ስምምነት ለማስገኘት ቃል ገብተዋል። የሪፐብሊካን ፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ፣ ጄዲ ቫንስ፣ ትናንት በአሜሪካና ሜክሲኮ ድንበር ላይ ባካሄዱት ጉብኝት፣ ለሀገሪቱ የኢሚግሬሽን ችግር በምክንያትነት ካማላ ሃሪስን ወቅሰዋል።
ታሪኩ ኃይሉ
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ