የአማራና የትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች ውዝግብ ወዴት እየሄደ ነው?
ሰኞ፣ ሚያዝያ 7 2016“ከትግራይ ክልል ተሻግረው የመጡ” ያሏቸው ታጣቂዎች ጥቃት እንዳደረሱባቸው የራያ አላማጣ ወረዳ ባለስልጣናትና ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬሌ ተናገሩ። ጉዳዩን አስመልክቶን ከትግራይ ክልል የመንግስት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃአስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡
አማራና ትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱባቸው አካባቢዎች የኢትዮጵያ መንግስትና የትግራይ ባለስልጣናት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሰረት ይፈታል የሚል ሀሳብ ቢኖርም አወዛጋቢ አካባቢዎች ግን እስካሁን እልባት ሳያገኙ እንዴያውም ወደ ግጭት የሚያመሩ ሁኔታዎች እየታዩ ነው፡፡ የፕሪቶሪያው ስምምነት እንደሚያመለክተው ሁለቱ ክልሎች አወዛጋቢ ቦታዎችን በህገመንግስቱ መሰረት እንደሚፈቱ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ያትታል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተለይም በራያ አላማጣ አካባቢ ትንኮሳዎችና ግጭቶች እየታዩ እንደሆነ ነው ነዋሪዎችና የአካባቢ ባለስልጠናት የሚናገሩት ፡፡ የወሎ አማራ የወሰንና ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አባልና የአላማጣ ከተማ አስተዳደር ሲቪል ሰርቪስ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መንገሻ ቸሩ ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በራያ አላማጣ ወረዳ አንዳንድ አካባቢዎች የትግራይ ኃይሎች በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት ከፍተዋል ብለዋል፡፡ “... በጋርጃሌ፣ ወደላይ በኩል ጉቤ በተባለ አካባቢ፣ ኡላ ኡላ ጋውርሻንቶ ሚባሉ ጎጦች (መንደሮች) ትናንትና እዛ ነው ግጭት የነበረው፣ ትናንትና እስከ ቀኑ 10 ሰዓት አካባቢ በድሽቃ፣ በሞርተር ሲተኩሱብን ነው የዋሉት፣ በእርቀት ከተራራ ላይ ሆነው ነው በእኛ ሚሊሺያዎች ላይ የሚተኩሱት፤ ወደ ኮረም መውጫ አካባቢ በዚያ በኩልም ውጊያ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ ነው፡፡” ብለዋል፡፡
ትንኮሳው ካለበት አካባቢ እንዳሉ የገለፁልን አንድ ነዋሪ ዛሬም ጥቃቱ መቀጠሉንና ሁለት የአካባቢው ሰዎች መገደላቸውን ነግረውናል፡፡ “በአሁኑ ሰዓት (ዛሬ ቀን 5 ሰዓት አካባቢ) ከባድ ውጊያ ነው ያለው፣ ውጊያው ጋርጃሌ በላይ “አስታምባ” የሚባል ቦታ አለ፣ በዚያ ቆርጠው አላማጣን ለመቆጣጠር ነው ያሰቡት፣ እስካሁን ሁለት ሰዎች ሞተዋል፣ የቆሰሉም አሉ፣ እኔ አሁን እዛው ጋርጃሌ ከተባለው አካባቢ ነው ያለሁ ተኩሱ ይሰማኛል፡፡በስናይፐርና ዲሽቃ ነው የሚተኩሱት፡፡”
መሆኒ በተባለ የትግራይ ክልል አካባቢ ተፈናቃዮች ወደ ቀያችን እንመለስ የሚል ሰላማዊ ሰልፍ ባለፈው ቅዳሜ መደረጉን የአላማጣ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኃይሉ አበራ መስማታቸውን ገልፀው፣ ግን ሰልፉን ሽንፋን በማድረግ ወደ ራያ አላማጣ ከተማ ለመግባት ጥረት በተደረገው እንቅስቃሴ ግጭቱ መፈጠሩን አመልክተዋል፡፡ እንደ አቶ ኃይሉ ተፈናቃዮች እንዲመለሱ ፈቃደኛ እንደሆኑ ጠቅሰው በጉልበትና በኃይል የሚሆን ነገር ግን እንደማይኖር አስጠንቅቀዋል፡፡
“የፕሪቶሪያው ስምምነት እንዲፈፀም እንፈልጋለን፣ ተፈናቃዮችም እንዲመለሱ ሽማግሌዎች ጭምር ልከናል፣ ምርጫ እንኳ ቢኖር ይምጡና ህዝቡ እነሱን ከመረጠ እናስረክባለን ብለናል፣ ሁሉን ነገር በኃይል ተቆጣጥርን ፍላጎታችን እናስፈፅማለን ካሉም ከዚህ በኋላ በኃይል የሚወሰድ ህዝብ የለም፣ ከራያ ህዝብ ፍላጎት በጭራስ ወደ ትግራይ የሚካለልበት እድል የለም” ነው ያሉት አቶ ኃይሉ፡፡ባለፈው ቅዳሜና ትናንትና በራያ አላማጣ ወረዳ አዲስ ብርሀን ቀበሌን በሙሉ፣ ጨማሮ፣ ቀልቃላና ሌሎችንም መንደሮች የትግራይ ኃይሎች የተቆጣጠሯቸው መሆናቸውን ከንቲባው ጠቁመው፣ ጦርነት እንደተከፈተባቸውና ህብረተሰቡንም ክብር ነስተውታል ነው ያሉት፡፡
ተፈናቃዮች እንዲመለሱ የራያ አላማጣ ነዋሪ ፍላጎት መሆኑን የገለፁት ሌላ የአላማጣ ከተማ ነዋረ፣ መሆኒ ላይ በተደረገው ሰልፍ ግን ሲነገር የነበረው ተገቢነት የሌለውና የራያ አላማጣን ህዝብ ያስቆጣ ነው ብለዋል፡፡ “ሰልፍ አድርገው ነበር፣ ተፈናቃይ ይግባ ነው የሚሉት፣ የእኛ ህዝብ ደግሞ ተፈናቃይ አይግባ ያለው ነገር የለም፣ ሲገድል፣ ሲያፍን ሰውን ወደ ጦርነት ሲልክ የነበረ ካለ ደግሞ እንዴት ይሁን? ነው፣ ንፁህ ተፈናቃይ ያለ አግባብ የተፈናቀለ ግን አሁንም መመለስ አለበት፣ መሬት የሁላችን የጋራ ናት፣ አንዱ ይኑር፣ አንዱ አይኑር የሚባል ነገር የለም፣ በሰልፉ ግን አንዳንዶቹ ይሉ የነበሩት ራያ አላማጣ ወረዳ እየኖረበት ያለው ከሌለ አካባቢ የመጣ ሰው ነው፣ የራያ አላማጣ ተወላጆች አይደለምመ የሚል ነው፣ ይህ ደግሞ ተገቢ ኤደለም፣ የራያ አላማጣ ህዝብ የት ይሂድ?”
በቅርቡ የፌደራሉ መንግስት የየኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ በሰጡት መግለጫ፣ “በትግራይ ክልል በኩል በአማራ ክልል አዋሳኝ የሚታየው አዝማሚያ ተገቢነት የሌለው” ነው በማለት ችግሮቹ በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት መፈታት እንዳለባቸው ጠቁመው ነበር፡፡ ከሳምንታት በፊት በተመሳሳይ በአዋሳኝ አካባቢዎች በተነሱ ግጭቶች ዙሪያ የአማራና የትግራይ ክልሎች መንግስታት በየግላቸው ባወጧቸው መግለጫዎች አንዱ ሌላውን ተወቃሽ ሲያደርጉ ተደምጠዋል፡፡
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከአማራ ክልል የተማሪዎች መማሪያ መጽሐፍት ጋር አስታክኮ ባወታው መግለጫ፣ “የአማራ ክልላዊ መንግስት አስተዳደር በመማሪያ መጽሐፍት ላይ የትግራይ ክልል አካል የሆኑ አካባቢዎችን በካርታው ውስጥ አካቶ ማውጣቱ «ጠብ አጫሪነት» ነው” ያለ ሲሆን፣ የአማራ ክልል መንግስት ባወጣው የአፃፋ መግለጫ ደግሞ፣ « የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለሀገሪቱ ቋሚ የቀውስ ምንጭ ከሚያደርጉት ተግባራት እንዲታቀብና ከአጓጉል የካርታ ፖለቲካ ጨዋታ እንዲወጣና የህዝብን ፍላጎት ማዕከል ባደረጉ ውይይቶች ላይ እንዲያተኩር እንመክራለን» ማለቱ ይታወሳል።
የሰሞኑን ግጭት በተመለከተ ተጨማሪ አስተያየት ለማካተት ለትግራይ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ረዳኢ ኃለፎም የአጅ ስልክ በተደጋጋሚ ብንደውልም፣ አጭር የጽሁፍ መልዕክት ብንልክም ምላሽ አላገኘንም፡፡
ይሁን እንጂ ከዚህ በፊት በአካባቢዎቹ ስለነበሩ ግጭቶችና ተያያዥ ጉዳዮች ጠይቀናቸው፣ “ጥቃት ፈፅመውብናል የሚል ተረት ቢያቆሙት ነው የሚሻለው፣ ጥቅም የለውም፣ እነርሱ በኃይል ከያዟቸው የትግራይ አካባዎች ቢወጡ ነው ለሰላም ጥቅም የሚሆነው፣ የተጠቃቀሱት ቦታዎች በሙሉ የትግራይ ራያ አካባቢዎች ናቸው እንጂ የአማራ አካባቢዎች አይደሉም፣ እነርሱ ጥቃት ፈፅመው መልሰው እነርሱ ጯሂ ሆነው እየሰማኋቸው ነው፣ ሰሞኑንም እንደዚያ እየታዘብናቸው ነው፡፡ ጥፋት የፈፀሙ፣ ጉዳት የፈፀሙ እነርሱ ናቸው፣ ሲጀመር ደግሞ ጥፋት እየፈፀሙ ያሉት በእኛ በትግራይ መሬት ላይ ተቀምጠው እያሉ መልሰው መጮሁ ጥቅም ያለው አይመስለኝም፡፡” ብለው ነበር፡፡
ዓለምነው መኮንን
አዜብ ታደሰ
ኂሩት መለሰ