1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የናይጄሪያ ምርጫ ለጀርመን ያለው አንድምታ

ረቡዕ፣ የካቲት 15 2015

ምዕራብ አፍሪቃዊቷ ሀገር ናይጄሪያ የፊታችን ቅዳሜ የካቲት 17 ቀን 2015 ዓም ምርጫ ለማካሄድ ቀጠሮ ይዛለች። ምርጫውን ሂደት እና ውጤት በ211 ሚሊዮን ናይጄሪያውያን ብቻ ሳይሆን በአጋሮቿ ዘንድም በከፍተኛ ጉጉት የሚጠበቅ ነው።

https://p.dw.com/p/4NqwY
Nigeria | Rückgabe der Benin-Bronzen in Abuja
ምስል Annette Riedl/dpa/picture alliance

መጭው የናይጀሪያ ምርጫ

መጭውን የናይጄሪያ ምርጫ የሀገሪቱ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ጀርመንን የመሳሰሉ አጋር ሀገራትም  በቅርበት እየተከታተሉት ነው። ምክንያቱም ውጤቱ ሀገሪቱ ከጀርመን ጋር ባላት ሁለንተናዊ ግንኙነት ላይተፅዕኖ አለውና።

በጎርጎሪያኑ የካቲት 25 ቀን የሚካሄደው የናይጀሪያ።የምርጫ በ211 ሚሊዮን ናይጄሪያውያን ብቻ ሳይሆን በአጋሮቿ ዘንድም  በከፍተኛ ጉጉት የሚጠበቅ ነው። ምርጫውን ሂደት እና ውጤት የውጭ ሀገራትም በቅርበት ይከታተላሉ።
ምክንያቱም በአፍሪካ ህብረት፣ በአለም አቀፍ ጉዳዮች ፣ በአየር ንብረት ለውጥ  እና በሩሲያ በዩክሬን  ጦርነት ላይ የአቡጃ ተጽዕኖ ትልቅ ነውና።የዘንድሮው የናይጄሪያ ምርጫ በስደት ላይም ትልቅ ተፅዕኖ አለው።በዚህ ምርጫ ሶስት እጩዎች ተሰናባቹን ፕሬዝዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪን ለመተካት እየተፎካከሩ ነው። የገዥው ኤፒሲ ፓርቲ ቦላ ቲኒው፣ የቀድሞው የፒዲፒ ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቲኩ አቡበከር እና የሌበር ፓርቲ ፒተር ኦቢ ናቸው።ኦቢ በተለይ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የበይነመረብ የምርጫ ቅስቀሳን ተከትሎ በወጣት መራጮች ዘንድ ይታወቃሉ።ይሁን እንጂ የናይጄሪያ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ንኩቹቹኩ ኦርጂ በመጪው ምርጫ የናይጄሪያ የግዛት አንድነት አደጋ ላይ መሆኑን ይገልፃሉ።

«ናይጄሪያ በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱ አንድነት በከፍተኛ ሁኔታ ጥያቄ ውስጥ የገባበት ደረጃ ላይ ደርሳለች። በናይጄሪያ አጠቃላይ የጸጥታ ችግር ባለበት ሁኔታ ምርጫ  ስናካሂድ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ ነው።ይህም በክልል  ወይም በአንዳንድ ግዛቶች ውስጥ ሊሆን ይችላል።»
በአፍሪካ በትልቅ ኢኮኖሚዋና በሕዝብ ብዛቷ በምትታወቀው ናይጄሪያ ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት የጸጥታው ሁኔታ የተሻለ ቢሆንም  ቀደም ባሉት ምርጫዎች ብጥብጥ ተከስቷል። በዚህ የተነሳ በበርሊን እና በሌሎች የአውሮጳ መዲናዎች የሚገኙ የፖለቲካ ታዛቢዎች  በአሁኑ ምርጫም ስጋት አላቸው። 
በደቡብ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙ ተገንጣዮች እና የወንጀለኞች ቡድኖች በአንድ በኩል ፣በሌላ በኩል ደግሞ በገበሬዎችና በአርብቶ አደሮች መካከል  ደም አፋሳሽ ግጭቶች አሉ። በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል ደግሞ በአክራሪ የሽብር ቡድኖች በርካታ የአገሪቱን ክፍሎች ወደ ትርምስ ከተዋል ።

Nigeria Region Borno Boko Haram
ምስል Audu Ali Marte/AFP/Getty Images

ይህ መሰሉ ችግር ያለባት ናይጄሪያ በአሁኑ ምርጫ ብጥብጥ ወይም በውጤቱ ላይ  አለመግባባቶች ከተከሰቱ፣ ተንታኞች እንደሚሉት ከምዕራባውያን ለጋሾች ስጋት በተጨማሪ፡ የሀገሪቱ የመሪነት ሚና ሊቀንስ ይችላል።
አዲሱ መንግስት የናይጄሪያን ችግር መቆጣጠር ካልቻለ ምዕራባውያን ሀገሮች ውጤቱን በሌላ መንገድ ሊያዩት ይችላል። የፖለቲካ ተንታኙ ኦርጂ እንደሚሉት የስደተኞች ጉዳይም ትልቅ ችግር ሊሆን ይችላል።
«በጥሩ ሁኔታ ካልታካሄደ  በስደት ዙሪያ ትልቅ  ችግር  ሊያጋጥም ይችላል። ስለዚህ ስደት ትልቅ ችግር ይሆናል።ምክንያቱም ሰዎች ቀድሞውንም ሀገር ለቀው እየወጡ ነው።ከዚያም ናይጄሪያውያን ሀገሪቱን ለቀው የሚወጡበት  ፍጥነት ከፍተኛ ይሆናል።ይህም በሀገሪቱ ህዝቦቿን የመንከባከብ አቅም እንደሌላት ይነግርሃል።»
ይህም እንደ ጀርመን ላሉ ዓለምአቀፍ አጋሮች እንደ ችግር ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም ናይጄሪያውያን ጀርመን ውስጥ ጥገኝነት ለመጠየቅ ከሚመጡ የአስር ሀገራት ዜጎች መካከል ናቸው።ከዚህ ጋር ተያይዞ ናይጄሪያ ሕገ-ወጥ የጉዞ እንቅስቃሴ በመቀነሱ ሂደት ተባባሪ እንድትሆንና እንዲሁም ተቀባይነት ያላገኙ የጥገኝነት ጠያቂዎችን በቀላሉ እንድትቀበል ጀርመን ስታግባባ  ቆይታለች።
በሌላ በኩል የጀርመን የንግድ ማህበረሰብ በናይጄሪያ የሚመጣውን የስልጣን ለውጥ በጉጉት እየጠበቀ ነው።በአፍሪካ የጀርመን  የንግድ ማህበር ባልደረባ የሆኑት ክሪስቶፍ ካነንጌሰር  እጩ ተወዳዳሪዎቹ አሁን ካለው መንግስት የበለጠ ለንግድ ምቹ ይሆናሉ የሚል  ተስፋ አላቸው። «አጠቃላይ ስርዓቱ ብዙ እና የተለያዬ ነው።ይህ አወንታዊ ነው።  እናም በአሁኑ ጊዜ የሚወዳደሩት ሁሉም እጩዎች በዚህ ረገድ ከአሁኑ መንግስት የበለጠ ንግድን የሚደግፉ መሆናቸውን እናያለን። ከዚህ አኳያ ከጀርመን አንፃር ስናየው ከምርጫ በኋላ የኢኮኖሚ ለውጥ  ጉዳይ  ተስፋን ያሳድራል።».
ሀገሪቱ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ከደቡብ አፍሪካ ቀጥሎ ለጀርመን ኩባንያዎች በጣም አስፈላጊ የንግድ አጋር ነች። ለወደፊቱም በተለይ  በታዳሽ ኃይል ፣ በንግድ እና የፖለቲካ ትብብርን ማስፋት ይፈልጋሉ። ከአየር ንብረት-ገለልተኛ ለመሆን የምትፈልገው ጀርመንም ግቧን ለማሳካት  ግብዓት  ትፈልጋለች። ናይጄሪያም ይህንን ማቅረብ ትችላለች ።ለዚህም  የጀርመን መንግሥት በዋና ከተማዋ አቡጃ በ 2021 ዓ/ም መጀመሪያ ላይ የግንኙነት ቢሮ ከፍቷል።እናም ነገሮች በሰላም ከቀጠሉ እና የምርጫው ውጤት ተዓማኒነት ያለው ከሆነ፣ የጀርመን መንግስት ነገሩን በአዎንታዊ መንገድ ማየቱ አይቀርም።

Nigeria Annalena Baerbock
ምስል Annette Riedl/dpa/picture alliance


ፀሀይ ጫኔ
ሂሩት መለሰ