1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኅዳር 16 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ኅዳር 16 2017

ሊቨርፑል ተቀናቃኞቹ ማንቸስተር ሲቲ እና አርሰናልን ወደ ኋላ ትቶ በመሪነቱ እየገሰገሰ ነው ። ከማንቸስተር ሲቲ በ8 ከሌላኛው ዋነኛ ተፎካካሪው አርሰናል ደግሞ በ9 ነጥብ ርቋል ። ነገ እና ከነገ በስተያ 18 የሻምፒዮንስ ሊግ እንዲሁም ሐሙስ ሌላ 18 የአውሮጳ ሊግ ግጥሚያዎች ይኖራሉ ።

https://p.dw.com/p/4nPZb
UEFA Nations League | Deutschland - Bosnien und Herzegowina
ምስል Adam Pretty/Getty Images

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ሊቨርፑል ተቀናቃኞቹ ማንቸስተር ሲቲ እና አርሰናልን ወደ ኋላ ትቶ በመሪነቱ እየገሰገሰ ነው ። ከማንቸስተር ሲቲ በ8 ከሌላኛው ዋነኛ ተፎካካሪው አርሰናል ደግሞ በ9 ነጥብ ርቋል ።  ነገ እና ከነገ በስተያ 18 የሻምፒዮንስ ሊግ እንዲሁም ሐሙስ ሌላ 18 የአውሮጳ ሊግ ግጥሚያዎች ይኖራሉ ። የሪያል ማድሪዱ ወሳኝ ተጨዋች ቪንሺየስ ጁኒዬር እና አንዳንድ ተጨዋቾች በጉዳት አይሰለፉም ተብሏል ። ሆላንዳዊው የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ተፎካካሪ፦ ማክስ ፈርሽታፐን ተከታታይ አራተኛ የውድድር ዘመን ድሉን ትናንት ላስቬጋስ ውስጥ አስመዝግቧል ።

አትሌቲክስ

በጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር በ2024 ከስታዲየም ውጭ በተደረጉ ውድድሮች የዓመቱ ምርጥ አትሌት አሸናፊ የፊታችን እሁድ፤ ኅዳር 22 ቀን፣ 2017 ዓ.ም ይፋ ይሆናል ። የዓለም አትሌቲክስ ለፍጻሜው ለታጩት 12 አትሌቶች ደጋፊዎች የድምፅ አሰጣጥ ክፍት አድርጎ ነበር ።  ከ12ቱ የመጨረሺያ እጩዎች መካከል  ኢትዮጵያዊው አትሌት ታምራት ቶላ ይገኝበታል ። የዘንድሮ አሸናፊ ሞናኮ ፈረንሣይ ውስጥ በሚደረገው የሽልማት ሥነሥርዓት ይፋ ይሆናል ። 

እግር ኳስ

ሞሮኮ በምታዘጋጀው የአፍሪቃ ዋንጫ ተሳታፊ 24 አገራት ተለይተዋል ። ቀደም ሲል ዋንጫ የወሰዱት ካሜሩን፣ የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ፣ ናይጄሪያ፣ ቱኒዚያ፣ ዛምቢያ እና ደቡብ አፍሪቃ በ35ኛው የአፍሪቃ ዋንጫም ተሳታፊ መሆናቸውን አረጋግጠዋል ። ከአስተናጋጇ ሞሮኮ ባሻገር በቀጣዩ የአፍሪቃ ዋንጫ ተሳታፊ የሆኑ ሌሎች አገራት፦ አልጄሪያ፣ አንጎላ፣ ቤኒን፣ ቦትስዋና፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ኮሞሮስ፣ አይቮሪ ኮስት፣ ግብጽ፣ ሴኔጋል፣ ኤኳቶሪያል ጊኒ፣ ጋቦን፣ ማሊ፣ ሞዛምቢክ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ዚምባብዌ እና ጎረቤት አገር ሱዳን ናቸው ። የኅዳር 09 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

6ኛ እና የመጨረሻ የምድብ ጨዋታውን በአሸናፊነት ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ቀደም ሲል ተደጋጋሚ ሽንፈትን ስላስተናገደ ለአፍሪቃ ዋንጫ ሳይልፍ ቀርቷል ። ብሔራዊ ቡድኑ በቀዳሚው ጨዋታ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ቡድን 2 ለ0 ተሸንፎ ነበር፥ በመልሱ ጨዋታ ባለፈው ሳምንት 2 ለ1 አሸንፏል ። ዋልያዎቹ ቀደም ሲል በነበራቸው የማጣሪያ ግጥሚያዎች፦ በመጀመሪያው ጨዋታ ከታንዛንያ ጋር ያለምንም ግብ ተለያይተው በመልሱ 2 ለ0 ተሸንፈዋል ።  የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በጊኒ በደርሶ መልስ 4 ለ1 እና 3 ለ0 ሽንፈት አስተናግዷል ። የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድሮች፦ በሚቀጥለው ዓመት ታኅሣሥ 12 ቀን፣ 2018 ዓ.ም ሞሮኮ ውስጥ ጀምረው በጥር 10 ቀን፣ 2018 ዓ.ም ይጠናቀቃሉ ።

የባለፈውን የአፍሪቃ ዋንጫ ያሸነፈው የአይቮሪ ኮስት ቡድን
የባለፈውን የአፍሪቃ ዋንጫ ያሸነፈው የአይቮሪ ኮስት ቡድን ሞሮኮ በምታዘጋጀው ውድድርም አልፏልምስል Themba Hadebe/AP/picture alliance/dpa

ፕሬሚየር ሊግ

በፔፕ ጓርዲዮላ ዘመን ማንቸስተር ሲቲ በሜዳው ኤቲሀድ ስታዲየም እጅግ አስደንጋጭ ሽንፈት ሲገጥመው ሊቨርፑል በደረጃ ሰንጠረዡ መሪነት እየገሰገሰ ነው ።  ማንቸስተር ሲቲን ቅዳሜ ዕለት በደጋፊው ፊት 4 ለ0 ጉድ ያደረገው ስድስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቶትንሀም ሆትስፐር ነው ። ለአሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ የቅዳሜውን ጨምሮ በተከታታይ አምስተኛ ሽንፈታቸው ነው ። በልደቱ ቀን ሁለት ግቦችን ያስቆጠረው ጄምስ ማዲሰን ረዥም ርቀት በመሮጥ ራሱን ለግብ ነፃ አድርጎ በማመቻቸት ብቃቱን ዐሳይቷል ። ዎልቨር ሐምፕተንም ቅዳሜ ዕለት ፉልሀምን 4 ለ1 አሸንፏል ።

የማንቸስተር ሲቲ ሽንፈት ቶትንሀምን ብቻ ሳይሆን በደረጃ ሰንጠረዡ መሪ የሆነው የሊቨርፑል ደጋፊዎችንም ያስፈነጠዘ ውጤት ነበር ። ሊቨርፑል የማታ ማታ 3 ለ2 ቢያሸንፍም የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ 20ኛ ላይ የሰፈረው ሳውዝሐምፕተን ትናንት የሞት ሽረት አድርጎ ነበር ። በትናንቱ ድል ሊቨርፑል 31 ነጥብ በመሰብሰብ ተከታዩ ማንቸስተር ሲቲን በ8 ነጥብ ርቆታል ።

አርሰናል አስተማማኝ በሆነ መንገድ ኖቲንግሀም ፎረስትን 3 ለ0 ድል አድርጓል ። በመጀመሪያው አጋማሽ የበላይ ሆነው ረፍት የወጡት መድፈኞቹ ከረፍት መልስም ኖቲንግሀም ፎረስት ላይ የበላይነታቸውን ዐሳይተዋል ። የሰሜን ለንደኑ አርሰናል በቅዳሜው ጨዋታ የበላይ ሆኖ አጠናቋል ። ለአርሰናል ቀዳሚዋን ግብ ጨዋታው በተጀመረ 15ኛ ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ቡካዮ ሳካ ነው ። ከዚያም በ52ኛ እና 86ኛ ደቂቃ ላይ ሁለቱን ግቦች ቶማስ ፓርቴይ እና ኤታን ንዋኔሪ አስቆጠረዋል ። አርሰናል በፕሬሚየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ከቸልሲ በግብ ተበልጦ በተመሳሳይ 22 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ።   የኅዳር 02 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ቅዳሜ በነበረ ሌላ ግጥሚያ፦ ቸልሲ ላይስተር ሲቲን በሜዳው ሁለት ለአንድ አሸንፎ ተመልሷል ። ለቸልሲ ኒኮላስ ጃክሰን እና ኤንዞ ፈርናንዴዝ አስቆጥረዋል ። በዜሮ ከመሸነፍ ያተረፈውን ብቸኛ ግብ ጆርዳን ዐየው በ90 ደቂቃው ላይ ከመረብ አሳርፏል ። 59ኛ ደቂቃ ላይ አንድ ተጨዋቹን በቀይ ካርድ ያጣው ብራይተን ቦርምስን በተመሳሳይ ሁለት ለአንድ አሸንፏል ።

አስቶን ቪላ ከክርሲታል ፓላስ ጋር ሁለት እኩል ሲወጣ፥ ኤቨርተን እና ብሬንትፎርድ ያለምንም ግብ ተለያይተዋል ። ትናንት በነበረ ሌላ ግጥሚያ 12ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ ወደ ኢፕስዊች ታውን ሄዶ አንድ እኩል ተለያይቷል ።  ኢፕስዊች ታውን በ9 ነጥብ 18ኛ ወራጅ ቀጣናው ውስጥ ይገኛል ።  ዛሬ ማታ ኒውካስል እና ዌስትሀም 12ኛ ተስተካካይ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ ። 

ከሊቨርፑል ወሳኝ ተጨዋቾች አንዱ ሞሐመድ ሳላኅ
የሊቨርፑል አጥቂ ሞሐመድ ሳላኅ እስካሁን ድረስ ውሉ አልተራዘመም ። የ32 ዓመቱ አጥቂ ከ8 ወራቶች በኋላ ስለሚጠናቀቀው ውሉ አዲስ ነገር አለመስማቱ እንዳበሳጨውም በጋዜጠኞች ተጠይቆ ተናግሯል ።ምስል Jon Super/AP Photo/picture alliance

ቡንደስሊጋ

ቡንደስሊጋውን በ29 ነጥብ የሚመራው ባዬርን ሙይንሽን አውግስቡርግን 3 ለ0 አሸንፏል ። በ23 ነጥብ ተከታዩ አይንትራኅት ፍራንክፉርት ከትናንት በስትያ ቬርደር ብሬመን ላይ ባስቆጠረው ብቸኛ ግብ ለድል በቅቷል ። በሆፈንሀይም የ4 ለ3 ሽንፈት የገጠመው ላይፕትሲሽ 21 ነጥብ አለው፥ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ባዬርን ሌቨርኩሰን ሐይደንሀይምን 5 ለ2 ድል አድርጎ ነጥቡን 20 አድርሷል ። ከበታቹ በአንድ ነጥብ ተበልጦ አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ፍራይቡርግን ቅዳሜ ዕለት 4 ለ0 ድል አድርጓል ። ትናንት ሳንክት ፓውሊን 2 ለ0 ያሸነፈው ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ በ17 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል ። ከስሩ በተመሳሳይ ነጥብ ፍራይቡርግ ይገኛል ። ሳንክት ፓውሊ፣ ሾልሽታይን ኪዬል እና ቦሁም ከ16ኛ እስከ 18ኛ ወራጅ ቀጣናው ውስጥ ተደርድረዋል ።

የሻምፒዮንስ ሊግ

በአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያዎች አንዳንድ ወሳኝ ተጨዋቾች በጉዳት አይሰለፉም ። የስፔኑ ሪያል ማድሪድ አጥቂ ቪንሺየስ ጁኒዬር ከሊቨርፑል ጋር ረቡዕ ማታ በሚኖረው ግጥሚያ እንደማይሰለፍ ቡድኑ ዛሬ ዐሳውቋል ። አንዳንድ የስፔን ጋዜጦች የጡንቻ ስር መዞር ያጋጠመው ብራዚሊያዊው የክንፍ አጥቂ ምናልባትም ለወር ያህል ላይሰለፍ ይችላል ሲሉ ዘግበዋል ። ቪንሺየስ ጁኒዬር ቡድኑ በስፔን ላሊጋ ሌጋንስን ትናንት 3 ለ0 ባሸነፈበት ግጥሚያ 90 ደቂቃ ተጫውቷል ። ለኬሊያን እምባፔም የመጀመሪያው ግብ እንዲቆጠር ኳስ አመቻችቷል ። የጥቅምት 25 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ 

ቪንሺየስ ጁኒዬር በሌለበት ሪያል ማድሪድን የሚገጥመው ሊቨርፑል በሻምፒዮንስ ሊጉም በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግም የደረጃ ሰንጠረዡን እየመራ ነው ። በአዲሱ አሰልጣኝ አርኔ ስሎት የሚመራው ሊቨርፑል ትናንት በነበረ የፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያ ሳውዝሐምፕተንን 3 ለ2 አሸንፏል ። በትናንቱ ግጥሚያ ሊቨርፑል ከ2 ለ1 ከመመራት 3 ለ2 እንዲያሸንፍ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር ሞሐመድ ሳላኅ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል ። ሆኖም እስካሁን ድረስ ሊቨርፑል ለግብጻዊው አጥቂ ውሉን አለማራዘሙ ታውቋል ። የ32 ዓመቱ አጥቂ ከ8 ወራቶች በኋላ ስለሚጠናቀቀው ውሉ አዲስ ነገር አለመስማቱ እንዳበሳጨውም በጋዜጠኞች ተጠይቆ ተናግሯል ። ሞሐመድ ሳላኅ ካለፉት ሰባት ዓመታት አንስቶ የሚጫወተው ለሊቨርየጥቅምት 25 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባፑል ቡድን ነው ። በቅርቡ ጫማውን መስቀል እንደማይሻም ዐሳውቋል ። የዘንድሮ ጨዋታ ዘመን ሲጠናቀቅ የቪርጂል ቫን ጂክ እና ትሬንት አሌክሳንደር-አርኖልድ ውልም አብሮ ይጠናቀቃል።  

የጀርመኑ ላይፕትሲሽ ቡድን ከስፔኑ ኢንተር ሚላን ጋር በሚያደርገው ግጥሚያ ተከላካዩ ሉቃስ ክሎስተርማን እንደማይሰለፍ ቡድኑ ዛሬ ይፋ አድርጓል ። ሉቃስ ባለፈው ሳምንት በቡንደስ ሊጋው ላይፕትሲሽ ሆፈንሀይምን 4 ለ3 ባሸነፈበት ግጥሚያ ጡንቻው ላይ በደረሰበት ኅመም ተቀይሮ ወጥቷል ።

የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም አሸናፊ ማክስ ፈርሽታፐን
ማክስ ፈርሽታፐን በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ታሪክ እጅግ ስኬታማ ከሆኑት መካከል አንዱ ነውምስል Evelyn Hockstein/REUTERS

የፖርቹጋሉ ስፖርቲንግ ሊዘቦን ነገ የእንግሊዙ አርሰናልን ያስተናግዳል ። ማንቸስተር ሲቲ በበኩሉ የሆላንዱ ፌዬኑርድን ይገጥማል ። አትሌቲኮ ማድሪድ ከስፓርታ ፕራህ እንዲሁም ባዬርን ሙይንሽን ከፓሪ ሳንጃርሞ ጋር የሚጋጠሙት በነገው ዕለት ነው ። ነገ እና ከነገ በስትያ በአጠቃላይ 18 የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያዎች ይከናወናሉ ። የፊታችን ሐሙስ ደግሞ በተመሳሳይ 18 የአውሮጳ ሊግ ጨዋታዎች ይኖራሉ ።

የጀርመኑ ሐምቡርግ እና የእንግሊዙ ላይስተር ሲቲ የሆላንድ ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ ተጨዋች ሩድ ቫን ኒስተልሮይን በአሰልጣኝነት ለመቅጠር እየተፎካከሩ ነው ። የጀርመን ማሰራጪያ ስካይ ሐምቡርግ ተሰናባች አሰልጣኝ ስቴፋን ባውምጋርትን ሩድ ቫን ኒስተልሮይ ለመተካት ጫፍ ደርሷል ሲል ዘግቧል ። የእንግሊዝ ጋዜጦች በበኩላቸው የ48 ዓመቱ ሩድ ቫን ኒስተልሮይ ላይስተርን ለመረከብ ጫፍ ከደረሱ ሦስት አሰልጣኞች አንዱ ነው ብለዋል።  የቀድሞው የቸልሲ አሰልጣኝ ግራሀም ፖተር እና የቀድሞ የዌስትሐም ዩናይትድ አሰልጣኝ ዴቪድ ሞዬስ ለእጩነት ከቀረቡት ውስጥ ናቸው ። ሩድ ቫን ኒስተልሮይ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ2010 እስከ 2011 ለጀርመኑ ሐምቡርግ ቡድን መጫወቱ የሚታወስ ነው ። የጥቅምት 18 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

የመኪና ሽቅድምድም

ሆላንዳዊው የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ተፎካካሪ፦ ማክስ ፈርሽታፐን ተከታታይ አራተኛ የውድድር ዘመን ድሉን ትናንት ላስቬጋስ ውስጥ አስመዝግቧል ። ማክስ ፈርሽታፐን በላስቬጋሱ ውድድር ባያሸንፍም ለዘንድሮ የውድድር ዘመን አሸናፊነት ግን በቅቷል ። የ27 ዓመቱ የሬድ ቡል አሽከርካሪ በመኪና ሽቅድምድም ስማቸው ከፍ ብሎ እንደሚጠሩ አሽከርካሪዎች አራተኛ ዋንጫውን አንስቷል ። አራት ጊዜ ዋንጫ ካነሱ አሽከርካሪዎች መካከል ሚሻኤል ሹማኸር፣ ሌዊስ ሐሚልተን፣ ጁዋን ማኑዌል ፋንጊዮ፣ ሠባስቲያን ፌትል ይጠቀሳሉ ። የሚቀጥለው የውድድር ዘመን ላይ ምናልባትም ድል ከቀናው በፎርሙላ አንድ የውድድር ታሪክ እንደ ሚሻኤል ሹማኸር አምስት የውድድር ዘመኖች ላይ በማሸነፍ ታሪክ ይቋደሳል ማለት ነው ።

በትናንትናው የላስቬጋስ ሽቅድምድም ሩሴል አንደኛ ሲወጣ፣ ሌዊስ ሐሚልተን የሁለተኛ ደረጃ አግኝቷል ። የውድድር ዘመኑ አሸናፊ ማክስ ፈርሽታፐን ከካርሎስ ሳይንዝ እና ሽርል ሌክሌርክ ኋላ አምስተኛ ሁኖ ነው ያጠናቀቀው ። በአጠቃላይ ነጥብ ግን ማክስ ፈርሽታፐን 403 በማግኘት ለድል በቅቷል ። ላንዶ ኖሪስ በ340 ሁለተኛ፤ ሻርል ሌክሌርክ በ319 ሦስተኛ ወጥተዋል ። በተደጋጋሚ አሸናፊ የነበረው ሌዊስ ሐሚልተን በዘንድሮ አጠቃላይ 208 ነጥብ የ7ኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል ። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ፀሐይ ጫኔ