አዲስ አበባ የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታትና የመበተን ሥራ ሊጀመር ነው
የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታትና የመበተን ሥራ ሊጀመር ነው ሲል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ዛሬ አስታወቀ, ትጥቅ የፈቱ፣ የሰላም ስምምነት የፈረሙ ድርጅቶች ውስጥ አባል የነበሩ እና በስድስት ክልሎች የሚገኙ 371, 971 የቀድሞ ተዋጊዎችን በ18 ወራት ውስጥ ትጥቅ በማስፈታት ወደ ተሃድሶ ማዕከላት ለማስገባት በሂደት ላይ መሆኑን ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ዛሬ አስታውቋል። ተጠሪነቱ ለመከላከያ ሚኒስቴር የሆነው የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ብጋድየር ጀነራል ደርቤ መኩሪያው በሚቀጥሉት አራት ወራት ውስጥ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሴቶች፣ በዕድሜ የገፉ እና ጤነኛ 75 ሺህ ተዋጊዎችን ኮሚሽኑ ወደ ማዕከል እንደሚያስገባ አስታውቀዋል።
በትግራይ ክልል ውስጥ 320 ተዋጊዎች ትጥቃቸውን ያስረክባሉ ተብሏል። በአራት ወራት ውስጥ ትጥቅ በማስረከብ ወደ ማዕከላት እንደሚገቡ ተነግሯል። ለዚሁ ተግባርም በትግራይ ክልል በመቀሌ፣ ዳጋ ሐሙስ እና አድዋ ከተሞች የመከላከያ ካምፕ የነበሩ ማዕከላት የቀድሞ ተዋጊዎችን ለማስልጠን እና ለማቆያነት ተመርጠዋል ተብሏል። በመግለጫው እንደተነገረው ስራው በዚህ ሳምንት ቅዳሜ በመቀሌ የመጀመርያው ዙር የቀድሞ ተዋጊዎችን ከነበሩበት የዉጊያ ዕዝ በማስወጣት ይጀመራል ።
ፖርት ሱዳን በማዕከላዊ ሱዳን በፈጥኖ ደራሹ ኃይል በተፈጸመ ጥቃት 40 ሰዎች ተገደሉ
ማዕከላዊ ሱዳን አንድ መንደር ውስጥ ፈጥኖ ደራሹ ኃይል ከትናንት አንስቶ ባደረሰው ጥቃት 40 ሰዎች መገደላቸውን አንድ ሐኪም ተናገሩ።ዋድ ኦሼይብ ከተባለው መንደር በስተሰሜን በሚገኘው በዋድ ራውአህ ሆስፒታል የሚሰሩት ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት የሕክምና ባለሞያው እንዳሉት 40ውም የተገደሉት በቀጥታ በተተኮሱባቸው ጥይቶች ነው። የዓይን ምስክሮች ደግሞ ከሚያዚያ 2015 ዓ.ም. አንስቶ የመንግሥት ጦርን የሚወጋው ፈጥኖ ደራሹ ኃይል ከአልጀዚራ ግዛት ዋና ከተማ ዋድ ማዳኒ በስተሰሜን 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው መንደሩን ያጠቃው ትናንት ምሽት ነው፤ጥቃቱ ዛሬም ቀጥሏል፤ታጣቂዎቹ ንብረት እየዘረፉም ነው ብለዋል ። በፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘገባ መሠረት የህክምና ባለሞያዎች ስማቸው እንዲነገር የማይፈልጉት በተደጋጋሚ ጥቃት ስለሚፈጸምባቸው ነው ።የዳቦ ቅርጫት ትባል ከነበረችው ከአልጀዚራ ግዛት የተፈናቀሉት ሰዎች ቁጥር የተመድ እንደሚለው ከ340 ሺህ በላይ ነው። በሱዳን ጦርና በፈጥኖ ደራሹ ኃይል መካከል በሚካሄደው ውጊያ በመላ ሀገሪቱ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል ፤ ከ11 ሚሊዮን በላይ ደግሞ ተፈናቅለዋል ፤ከነዚህም ከሦስት ሚሊዮን የሚበልጡት ከሱዳን ውጭ ናቸው።
ናይሮቢ ቻድ የሚገኙ የሱዳን ስደተኞች ከኅብረተሰቡ ጋር እንዲዋሀዱ የተጀመረ ፕሮጀክትን ጀርመን ልታግዝ ነው
ቻድ የሚገኙ የሱዳን ስደተኞች ከኅብረተሰቡ ጋር እንዲዋሀዱ ይረዳል የተባለን ፕሮጀክትጀርመን ለመደገፍ ማቀዷን የጀርመን የልማት ሚኒስትር አስታወቁ። ሚኒስትሯ ስቬንያ ሹልዘ ይህን ያሉት ዛሬ በቻድ ባደረጉት ጉብኝት ወቅት ነው። የቻድ መንግሥት ለሚቀጥሉት 5 ዓመታት በሊዝ ነፃ ለመስጠት ካቀደው 100 ሺህ ሄክታር መሬት ግማሹን ለስደተኛ ቤተሰቦች ፣ የተቀረውን ደግሞ በአስተናጋጅ ማኅበረሰብ ውስጥ መሬቱ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ለመስጠት አቅዷል ። የሚሰጠውም በቤተሰብ አንድ ሄክታር ነው። የዓለም የምግብ ድርጅት በምህጻሩ WFP ቤተሰቦች የሚሰጣቸውን መሬት ጥቅም ላይ እንዲያውሉ እርዳታ ይሰጣል። ይህንኑ ምሥራቅ ቻድ ውስጥ የሚገኘውን አድሬ የተባለው ድንበር የጎበኙት ሹልዝ «እንዳለመታደል ሆኖ የሱዳን ስደተኞች ወደ ሀገራቸው መመለስ እንደማይችሉ መገመት አለብን ብለዋል። ሰብዓዊ እርዳታም ዘላቂ መፍትኄ እንዳይደለም ገልጸዋል። ለስደተኞቹና ለአስተናጋጁ ኅብረተሰብ መሬት በመስጠት ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ የሚከናወነው ተግባር ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው ሲሉ አወድሰዋል።በአሁኑ ጊዜ በአድሬ አካባቢ ብቻ ቁጥራቸው 250 ሺህ የሚደርስ ስደተኞች ይገኛሉ።
ባኩ በኮፕ 29 ባለጸጋ ሀገራት «አዳዲስ የከሰል ድንጋይ የኃይል ማመንጫ» ላለመገንባት ተስማሙ
የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ፣ በምህጻሩ ኮፕ 29 ላይ የተሳተፉ 25 ሀገራት አዳዲስ የድንጋይ ከሰል የኃይል ማመንጫ ላለመገንባት ቃል ገቡ። ይህን ቃል የገቡት አዘርባጃን በተካሄደው ኮፕ 29 ላይ ከተካፈሉ ባለጸጋ ሀገራት መክከል ብሪታንያ ፣ ካናዳ ፣ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ዋነኛዋ የድንጋይ ከሰል አምራች አውስትራሊያ ይገኙበታል። ይሁንና ባኩ ፣አዘርባጃን ውስጥ በተካሄደው በዚህ ጉባኤ ከዓለም ዋነኛ የድንጋይ ከሰል ኃይል አመንጪዎች ቻይና ህንድ እና ዩናይትድ ስቴትስ ጨምሮ አብዛኛዎቹ ሀገራት ስምምነቱን አልፈረሙም ።አዳዲስ የድንጋይ ከሰል የኃይል ምንጭ ላለመገንባት ቃል የገቡት ሀገራት በጎርጎሮሳውያኑ 2026 መጀመሪያ ላይ እቅዳቸውን እንዲያቀርቡ ይገደዳሉ። ሀገራቱ ከማምረት የሚቆጠቡት የበካይ ጋዝ ልቀትን ለመከላከል የሚያስችሉ እርምጃዎች ሳይታከልበት የተቃጠለ የድንጋይ ከሰልን ነው። ሀገራቱ የተስማሙበት የድንጋይ ከሰል አመራረት የድንጋይ ከሰልን ማውጣትንም ሆነ ወደ ውጭ መላክን አይከለክልም።
ሞስኮ ሩስያ የኃይል ተቋማትን ሥራ ለማስተጓጎል በማቀድ የጠረጠረችውን የጀርመን ዜጋ አሰረች
የሩስያ ከፍተኛ የሀገር ውስጥ የደኅንነት መስሪያ ቤት የኃይል ማመንጫ ተቋማት ስራን ለማስተጓጎል በማቀድ የጠረጠውን አንድ የጀርመን ዜጋ ማሰሩን አስታወቀ። በቁጥጥር ስር የዋለው ጀርመናዊ ከአንድ የዩክሬን ዜጋ ትዕዛዝ ተቀብሏል ብላለች ሞስኮ ። ይኽው በምህጻሩ FSB የተባለው የፌደራል የደኅንነት አገልግሎት በሩስያ የዜና አገልግሎት ድርጅቶች በኩል ባወጣው መግለጫ ጀርመናዊው ኒኮላይ ጋይዱክ ወደ ምዕራብ ሩስያው ካሊኒግራድ ሲገባ ነው የተያዘው ። በመኪናውም ውስጥ ግማሽ ሊትር ፈሳሽ ፈንጂዎች ተገኝተውበታል። ሆኖም የደኅንነት አገልግሎቱ ጋይዱክ የሩስያ ዜጋም ይሁን አይሁን ወይም ወደ ሩስያ ሲገባ ቪዛ ይኑረው አይኑረው የገለጸው ነገር የለም። የደኅንነት መስሪያ ቤቱ በጎርጎሮሳዊው 1967 የተወለደው የሰሜን ጀርመንዋ ከተማ ሀምቡርግ ነዋሪ ጋይዱክ እዚያው ሀምቡርግ ከሚኖረው ከአሌክሳንደር ዚሆሮቭ ስራን የማስተጓጎል ትዕዛዝ ተቀብሏል ብሏል። ጋይዱክ ባለፈው ዓመት መጋቢት ካሊንኒንግራድ በሚገኝ የጋዝ ማከፋፋፈያ ጣቢያ ላይ በደረሰ ፍንዳታ እጁ እንዳለበትም ገልጿል። ድርጊቱም በሽብር ጥቃት ክስ እንዲመሰረትበት አድርጓል። ያኔ ፍርድ ቤቱ ጋይዱክ በቅድመ ምርመራ እንዲያዝ አድርጎ ነበር። የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉዳዩን እንደሚያውቅ አስታውቋል። ቃል አቀባይ ካትሪን ዴሻወር ግለሰቡ ጥቅምት መታሰሩንና ሴንት ፒተርስበርግ የሚገኘው የጀርመን ቆንስላም እንደሚያውቅ ተናግረዋል። በጉዳዩ ላይ ከሩስያ ባለስልጣናት እየተነጋገሩ መሆኑን አስረድተዋል። ይሁንና ግለሰቡ ሀምቡርግ ከሚኖር ዩክሬናዊ ትዕዛዝ ተቀብሏል ስለመባሉ ምን ዓይነት አስተያየት አልሰጡም።
ኂሩት መለሰ
ታምራት ዲንሳ