1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቻይና ፀረ-ኮቪድ ሕግ፣ ተቃዉሞዉና አፀፋዉ

ሰኞ፣ ኅዳር 26 2015

የ1989ኙ የዩነቪርስቲ ተማሪዎች አመፅ ከከሸፈ በኋላም የቻይናን ኮሚንስታዊ አገዛዝ በቀጥታም በተዘዋዋሪም በመቃወም የተለያዩ ተቃዉሞዎች፣የአደባባይ ሰልፍና አመፆች ተደርገዋል።የቻይና የሶሻል ሳይንስ አካዳሚ እንዳጠናዉ ቻይና ዉስጥ በየዓመቱ በአማካይ 90ሺሕ ተቃዉሞች ይደረጋሉ።

https://p.dw.com/p/4KV9V
Gedenken und Protest nach Feuer in Urumqi
ምስል Thomas Peter/REUTERS

ተቃዉሞዉ በርግጥ የፀረ ኮቪድ ሕግ ነዉ?

አጠቃላይ የሐገር ዉስጥ ምርቷ (GDP) 17 ትሪሊዮን ዶላር ይገመታል።ዩናይትድ ስቴትስን ተከትላ ከዓለም ሁለተኛዋ ናት።በ2021 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ)የአዉሮጳ ሕብረትን በልጧል።አዋቂዎች እንደሚገምቱት በ2028 የዓለምን ምጣኔ ሐብት በአንደኝነት ትመራለች።ቻይና።በሕዝብ ብዛት፣ በሚሊየነሮችና በወታደር ቁጥር  ከዓለም አንደኛ ናት።የጦር መሳሪያና የጠፈር ቴክኖሎጂዋን ከምዕራባዉያን ለማስተካከል እየጣረች፣የአፍሪቃና የከፊል እስያን ምጣኔ ሐብት ከምዕራባዉያን እጅ መጭንቃ ለመዉሰድ እየባተለች ነዉ።የኮሮና ስርጭትን ለመቆጣጠር የምትወስደዉ እርምጃ ግን ዕድገቷን እያወላከፈ፤ ለምዕራብ ባላንጦችዋ ሴራ መደላድል እያመቻቸ፣ ኮሚንስታዊ ስርዓቷን ለአዲስ ብልሐት እያራወጠ ነዉ።የቻይና ፀረ-ኮሮና ሕግ የገጠመዉ ተቃዉሞ መነሻ፣ ፈጣን ዕድገቷ ማጣቀሻ፣ ከምዕራባዉያን ጋር የገጠመችዉ ግብግብ መድረሻችን ነዉ፣ ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።

                                  

የቻይና ኮሚንስት ፓርቲ መሥራችና የርዕተ-ዓለም አባት ማዖ ዜዱንግ በ1939 እንዳሉት ለቻይና ኮሚንስት ፓርቲ አብዮታዊ ትግል ግብ መምታት መሰረቱን የጣለዉ ግንቦት 1919 የተደረገዉ ፀረ-ኢፕሪያሊስትና ፀረ-ፊዉዳል  አመፅ ነዉ።በልማዱ «የግንቦት 4 ንቅናቄ» ተብሎ የሚጠራዉ አብዮት ወይም አመፅ፣ የፖለቲካ አዋቂዎች ዉስጣዊና ዉጪያዊ የሚሉት ሁለት ዋና ዋና መነሻዎች ነበሩት።አለቅጥ የከፋዉን የቻይናን  ፊዉዳላዊ አገዛዝ ዉስጣዊዉ ሲሉት፤ የመጀመሪያዉ የዓለም ጦርነት ካበቃ  በኋላ የጦርነቱ አሸናፊዎች ቫርሴይ-ፈረንሳይ ዉስጥ ያደረጉት ዉል የቻይናን  ጥቅም አለማስከበሩን-ዉጪያዊ።

ግንቦት 4፣1919 በየከተማዉ አደባባይ የወጣዉ በአብዛኛዉ የዩኒቨርስቲ ተማሪ የሐገሪቱን አገዛዝና የቫርስይ ስምምነትን ለመፈረም ዳርዳር የሚሉ ባለስልጣናትን በግልፅ አወገዘ።በተለይ ከ4 ሺሕ የሚበልጡ የያንቺንግና የፔኪንግ ዩኒቨርስቲዎች፣ የሌሎች ትምሕርት ቤቶች ተማሪዎችና ደጋፊዎቻቸዉ ትያናንሜን አደባባይ ላይ ያቀጣጠሉት አመፅ የጥንታዊቱን ሐገር የብዙ ዘመን ጉዞ ባዲስ ጎዳና የዘወረ ነበር።

የኡሩምቺ ሟቾች መታሰቢያ ሰልፍና ተቃዉሞ
የኡሩምቺ ሟቾች መታሰቢያ ሰልፍና ተቃዉሞ ምስል Mario Tama/AFP/Getty Images

አመፁ፣ ሊቀመንበር ማዖ ከ20 ዓመት በኋላ እንዳሉት የቻይና ኮሚንስት ፓርቲ ለመራዉ አብዮት መስፈንጠሪያ፣ ለሕዝባዊት ቻይና ሪፐብሊክ መሰረት የጣለ ነዉ።የግንቦት 4ቱ ንቅናቄ በተደረገ በ70ኛ ዓመቱ ኮሚንስታዊዉን አገዛዝ የሚቃወሙ ተማሪዎች ከታሪካዊዉ ትያናንሜን አደባባይ ሲወጡ ሕዝባዊ አመፅ በጫረዉ እሳት የተቀጣጠለዉ አብዮታዊ ትግል ሥልጣን የያዘዉ ኮሚንስታዊዉ ሥርዓት በሕዝባዊ አመፅ ሊሰናበት አስብሎ፣ በተለይ ምዕራባዉያንን  ሲበዛ አጓጉቶ ነበር።

ይሁንና ዴንግ ሺዮፒንግ እንደ መሪ ጂያንግ ዘሚን እንደ ምክትል ያዘዙት ጦር አመፀኞችን በታንክ ደፍልቆ መላምት፣ ትንቢት ጉጉቱን በነበር አስቀረዉ።በነገራችን ላይ አመፁ ከተደፈለቀ ከወራት በኋላ የሕዝባዊት ቻይናን የመሪነት ስልጣን የያዙት ጂያንግ ዘሚን ባለፈዉ ሳምንት አረፉ።ሰዉዬዉ ለደጋፊዎቻቸዉ ምርጥ ኮሚንስት፣ቆራጥ መሪ፣ዲፕሎማት፣የጦር ስልት አዋቂ፣ የምጣኔ ሐብት አሳዳጊም ነበሩ።

 «ጓድ ጂያንግ አሚን ታላቅ ማርክሲስት፣ታላቅ ወጣደራዊ አብዮታዊ መሪ፣የጦር ስልት አዋቂና ዲፕሎማት፣ለረጅም ጊዜ የተፈተኑ ታላቅ ኮሚንስት፣የቻይናን ባሕሪ የተለባሰዉ የሶሻሊዝም ዓላማ ታላቅ መሪ ነበሩ።» ይላል የኮሚንስት ፓርቲዉ የሐዘን መግለጫ።

ጂያንግ ዘሚን በርግጥ ዴንግ ሺዮፒንግን እንጂ ሚኻኤል ጎርቫቾቭን አልነበሩም።በኃይል ያስደፈለቁት አመፅ ያነቃነቀዉን ኮሚንስታዊ ሥርዓት ያረጋጉ፣የምዕራባዉያንን ዉግዘት፣ሴራና ሻጥርን ያከሸፉ፣ ጫና፣ግፊትና መገለሉን ተቋቁመዉ ሐገሪቱን ከዓለም ቱጃሮች ተርታ ያሰለፉ መሪ ነበሩ።

በ1990ዎቹ መጀመሪያ የሶቭየት ሕብረት ኮሚስታዊ ስርዓት ሞስኮ ላይ እንደተንኮታኮተ ሁሉ፣ ቤጂንግ ላይ ተመሳሳዩ እንዲሆን ለተመኙ፣ለደገፉና ለሞከሩት ጠላቶቻቸዉ ግን ሰዉየዉም ሥርዓታቸዉም ጨካኝ፣ ጨቋኝ አምባገነን፣ ሰባአዊ መብት ደፍላቂ ናቸዉ።

የትያናንሜን አደባባይ ተቃዉሞን የደፈለቀዉ የታንክ አጀብ
የትያናንሜን አደባባይ ተቃዉሞን የደፈለቀዉ የታንክ አጀብምስል Jeff Widener/AP Photo/picture alliance

የ1989ኙ የዩነቪርስቲ ተማሪዎች አመፅ ከከሸፈ በኋላም የቻይናን ኮሚንስታዊ አገዛዝ በቀጥታም በተዘዋዋሪም በመቃወም  የተለያዩ ተቃዉሞዎች፣የአደባባይ ሰልፍና አመፆች ተደርገዋል።የቻይና የሶሻል ሳይንስ አካዳሚ እንዳጠናዉ ቻይና ዉስጥ በየዓመቱ በአማካይ 90ሺሕ ተቃዉሞች ይደረጋሉ።ፓሪስ፣ለንደን፣ዋሽግተን፣በርሊን ወይም ብራስልስ ዉስጥ በየዓመቱ የሚደረጉ ተቃዉሞች ግን ቻይና ዉስጥ ከሚደረጉት በብዙ እጅ ይበልጣሉ።

የቤጂንግ፣የቴሕራን፣የሞስኮ፣የቬኑዙዌላ ተቃዉሞ ሰልፎች ፓሪስ፣ ለንደን፣ሮም፣ዋሽግተን ከሚደረጉት ደምቀዉ የሚራገቡበት ምክንያት በርግጥ ብዙ ያነጋግራል።የቻይና መንግስት የኮሮና ተሕዋሲ ስርጭትን ለመቆጣጠር የደነገገዉን የመንቀሳቀስ ዕገዳ በመቃወም ሰሞኑን በተለያዩ የቻይና ከተሞች የተደረገዉ የአደባባይ ሰልፍና አመፅ ግን ከ1989ኙ አመፅ ወዲሕ በጣም ከፍተኛዉ ነዉ።

ካለፈዉ ጥቅምት ማብቂያ ጀምሮ ከናንሺያግ ግዛት እስከ ቤጂንግ፣ ከሻንጋይ እስከ ሺያን በሚገኙ በ10 የቻይና ግዛቶችና ትላልቅ ከተሞች የተደረገዉ ተቃዉሞ መሰረታዊዉ መነሻ የቻይና መንግስት 0-ኮቪድ በሚለዉ ደንብ ሰዎች ከየቤታቸዉ እንዳይወጡ ማገዱ ነዉ።የ1989ኙን የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን አመፅ ከመሩት አንዱ ዋንግ ዳን እንደሚሉት ግን ያሁኑ ተቃዉሞ ከያኔዉ ጋር ተመሳሳይ ነዉ።

«በመላዉ ቻይና የሚደረገዉን አስደናቂ ተቃዉሞ ሳይ መጀመሪያ የታዘብኩት የ1989ኙ መንፈስ ከ33 ዓመት በኋላ እንደገና ተመለሰ ብዬ ነዉ። እንደሚመስለኝ ተመሳሳይ ነዉ።ምክንያቱም ባሁኑም ተቃዉሞ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ግንባር ቀደም ናቸዉ።የወጣቱን ትዉልድ ትግል ዳግም እያየን ነዉ።ይሕ ብዙዎችን ያስደንቅ ይሆናል።ምክንያቱም ብዙ ሰዎች የዘመኑ ወጣት የሚያስበዉ ገንዘብ፣የተሻለ ስራና ክፍያ እንጂ ለፖለቲካ ብዙ አይጨነቅም በሚልበት ወቅት ነዉ።»

ነዋሪዎች ካያሉበት እንዳይቀሳቀሱ ከታገደባቸዉ ከተሞች አንዷ ኡሩምቺ ዉስጥ አንድ ሕንፃ በእሳት ጋይቶ 10 ሰዎች ሞተዋል።ሌሎች 11 ቆስለዋል።ቃጠለዉ የሰዉ ሕይወት ያጠፋዉ ነዋሪዎቹ በእግዳዉ ምክንያት ፈጥነዉ መሸሽ ባለመቻላቸዉና የእሳት አደጋ መከላከያ ቀልጥፎ ባለመድረሱ እንደሆነ በሰፊዉ ይነገራል።

ቃጠሎዉ ያደረሰዉ ጥፋት ተቃዉሞዉን አባብሶታል።ጉዳቱን በተለይም የቻይና ፀጥታ አስከባሪዎች በተቃዋሚዎቹ ላይ ወስደዉታል የተባለዉን የኃይል እርምጃን  የመብት ተሟጋቾች እያወገዙ፣እርምጃዉ እንዲቆም እየጠየቁም ነዉ።ቤጂንጎችን ለማሳጣት አቀባብለዉ የሚጠብቁት የዋሽግተን-ብራስልስ፣ የለንደን ኦታዋ መንግስታትም የቻይና ኮሚንስት ፓርቲን ለመኮነን ጥሩ አጋጣሚ ነዉ የሆነላቸዉ።

ጂያንግ ዘሚን
ጂያንግ ዘሚን ምስል XINHUA/AFP

ተቃዉሞዉ በተቀጣጠለበት መሐል ዩናይትድ ስቴትስ ሕዋዌ በተባለዉ የቻይና የተንቀሳቃሽ ስልክ አምራች ግዙፍ ኩባንያ ላይ ማዕቀብ ጥላለች።ዩናይትድ ስቴትስ ጦር ከቻይና የረጅም ጊዜ ጠላት ከሕንድ ጦር ጋር ቻይና ድንበር አጠገብ የጋራ የዉጊያ ልምምድ አድርጓል።ዩናይትድ ስቴትስ የምትመራዉ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ተሻራኪ ድርጅት NATO ዋና ፀሐፊ የንስ ሽቶትልበርግ ደግሞ የድርጅቱ አባል ሐገራት ከቻይና ጋር ያላቸዉን ንግድ እንዲቀንሱ መክረዋል።

«የዩክሬኑ ጦርነት በሩሲያ ጋዝ ላይ ያለንን አደገኛ ጥገኝነት በግልፅ አሳይቷል።ይሕ በሌሎች ፈላጭ ቆራጭ መንግስታት ላይ ያለንን ጥገኝነት እንድናጤን ሊያደርገን ይገባል።በተለይ ከቻይና ጋር ለአቅርቦት ሰንሰለታችን፣ ለቴክኖሎጂያችንና ለመሰረተ ልማት አዉታራችን ያለንን ጥገኝነት ማጤን አለብን።ከቻይና ጋር የንግድ ልዉዉጥ ማድረጋችንን፣ ምጣኔ ሐብታዊ ግንኙነታችንን በርግጥ እንደቀጥላለን።ነገር ግን የጥገኝነታችንን ደረጃ፤ተጋላጭነታችንንና አደጋዉን መቀነስ አለብን።»

 

የተቃዉሞዉ ጥንካሬ፣ ሒደትና መልዕክቱ፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ጥያቄ፣የምዕራባዉያን ዉግዘት፣የአሜሪካኖች ማዕቀብ ሲተነተን የአዉሮጳ ሕብረት ምክር ቤት ፕሬዝደንት ሻርልስ ሚሼል ቤጂንግ ገቡ።የቤልጂጉ ፖለቲከኛ ጉዞ የቀሰዉ ጉምጉምታ በየመገናኛ ዘዴዉ ሲራገብ ብልጡ ፖለቲከኛ ከቻይና ባለስልጣናት ጋር ስለ ሰብአዊ መብትም ተነጋግሬያለሁ አሉ።

«የሰብአዊ መብቶችን፣ የአናሳዎችን መሰረታዊ ነፃነትንና መብቶችን አንሳቼያለሁ።ሰብአዊ መብት ሁለንተናዊ ነዉ።የአዉሮጳ ሕብረትና ቻይና በሰብአዊ መብት ጉዳይ ላይ የሚያደርጉት ምክክር እንዲቀጥል ጥግጁነት ማየቴን በደስታ ተቀብዬዋለሁ።የገባነዉን ቃል ገቢር ማድረጋችንን እንቀጥላለን።»

የፀጥታ አስከባሪዎችና የተቃዋሚዎች ፍጥጫ
የፀጥታ አስከባሪዎችና የተቃዋሚዎች ፍጥጫምስል HECTOR RETAMAL/AFP/Getty Images

የቻይና መንግስት ከዉጪና ከዉስጥ ለገጠመዉ ተቃዉሞ ብዙ የተጨነቀ አይመስልም።ይሁንና በሐገር ዉስጥ የተነሳዉ ተቃዉሞ የቻይና የዉስጥ ጉዳይ መሆኑን ምዕራባዉያን እንዲገነዘቡ ማሳሰቡ ግን አልቀረም።የሐገሪቱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ማኦ ኒንግ በቀደም እንዳሉት ደግሞ የኮሮና ተሕዋሲ ስርጭትን ለመከላከል መንግስታቸዉ የሚከተለዉ  መርሕ ሳይንሳዊና ዉጤታማ ነዉ።

«ቻይና ዉስጥ ያለዉ የኮቪድ 19 ስርጭት፣ምልክትና የሕመምተኛ ቁጥር በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለዉ ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ነዉ።እዉነታዉ ይሕን ያረጋግጣል።ቻይና ወረርሽኞችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በቅርብ ዓመታት የወሰደቻቸዉ እርምጃዎች ሳይንሳዊና ዉጤታማ ናቸዉ።»

የቻይና መንግስት በጣለዉ እገዳ ምክንያት የተቀጣጠለዉ አመፅና ተቃዉሞ ባለፉት ጥቂት ቀናት ረገብ ያለ መስሏል።ፀጥታ አስከባሪዎች በተቃዋሚዎች ላይ የሚወስዱትን ጠንካራ ርምጃም ቀንሰዋል።ጥንታዊቱ፣ትልቂቱ፣ሐብታሚቱ፣ ኮሚንስታዊቱ ሐገር ከምዕራባዉያን ጋር የገጠመችዉ ሽኩቻና ሽሚያ ግን አሁንም በየመስኩ እንቀጠለ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ታምራት ዲንሳ