የቻይና እና የአፍሪቃ ትብብር
ቅዳሜ፣ ጳጉሜን 2 2016የቻይና እና የአፍሪቃ ትብብር (FOCAC) የላቀ እመርታ በማሳየት ላይ ነው ። የቻይና እና አፍሪቃ የትብብር ጉባኤ ትናንት ሲጠናቀቅ ቻይና ለአፍሪቃ 51 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ መመደቧ ተሰምቷል ። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2000 የተመሰረው የቻይና እና አፍሪቃ የትብብር መድረክ ላይ የተሰማው የድጋፍ ዜና ለ1 ሚሊዮን ሰዎች የሥራ እድል ይፈጥራልም ተብሏል ።
ከ50 በላይ የአፍሪቃ መሪዎች እና ተወካዮች የተገኙበት የሦስት ቀናቱ ጉባኤ ዐርብ ተጠናቋል ። ጉባኤው የተጠናቀቀው በስኬት መሆኑ ተገልጧል ። በእርግጥም ቻይና በጉባኤው ወቅት ከ30 ሃገራት ጋ አንድም ሥልታዊ ትብብር መስርታለች አለያም ትብብሩን ከፍ አድርጋለች ። የቻይና ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባዪት ማዎ ኒንግ ።
ቻይና በጉባኤው ወቅት ከ30 ሃገራት ጋ ሥልታዊ ትብብር አጠናክራለች
«ይህ ጉባኤ ቻይና እና አፍሪቃ በጋራ ለማደግ ቁርጠኛ ስለመሆናቸው ጠንካራ መልእክት አስተላልፏል ። ጉባኤው በደቡባዊ የዓለም ንፍቀ ክበብ ያሉ ሃገራት ለአብሮነት እና ትብብር ያላቸውን ጽኑእ እምነት ያሳየ ነው ። ለሰው ልጅ የወደፊት የጋራ ተጠቃሚነት ያለው ማኅበረሰብ በመገንባቱ ረገድ የደቡባዊ የዓለም ንፍቀ ክበብ ሃገራት ሚናን አጉልቶ ዐሳይቷል ።»
ቻይና እና አፍሪቃ በጋራ ዘመናዊነትን ለማፋጠን ስድስት ዋና ዋና ሐሳቦችን ይፋ አድርገዋል ። ትብብራቸውንም ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ ለማድረግ የሚያስችል ዕቅድም ነድፈዋል ። ጉባኤው የቤጂንግ ስምምነት እና የድርጊት መርኃ ግብር አጽድቋል። የቻይና ፕሬዝዳንት ሺ ቺንፒንግ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ከአፍሪቃ ጋ ዘመናዊነትን በጋራ ለማራመድ 10 የትብብር የድርጊት መርኃ ግብሮችን ይፋ ማድረጋቸውንም ቃል አቀባዩዋ ዐሳውቀዋል ።
የአፍሪቃ እና ቻይና ትብብር ከፍ ብሏል
የቻይና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት መሪዎች ጋ በጉባኤው ወቅት በቅርበት ለመነጋገር መቻላቸው ተዘግቧል ። የቻይና ጠቅላይ ሚንሥትር ሊ ሺያንግ ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ ጋ ቤጂንግ ውስጥ ሐሙስ ዕለት ፊት ለፊት ተገናኝተው ተነጋግረዋል ።
ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ፖለቲካዊ የእርስ በርስ መተማመንን ለማጠናከር፣ ሁለንተናዊ ወዳጅነትን ለማጎልበት እንደምትሠራ የቻይናው ጠቅላይ ሚንሥትር ተናግረዋል ። ብሎም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ሁለንተናዊ ትብብር ለማስፋት እና ከኢትዮጵያ ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ የላቀ እድገት ለማስመዝገብ እንደምትገፋበትም አክለዋል ሲል አሶሺየትድ ፕሬስ አትቷል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ