የትራምፕ ንግግር በሪፐብሊካን ፓርቲ ጉባኤ መዝጊያ ላይ
ዓርብ፣ ሐምሌ 12 2016ዶናልድ ትራምፕ የሪፐብሊካን ፓርቲ እጩነታቸው በይፋ ተቀበሉ። በሪፐብሊካን ፓርቲ ጉባኤ መዝጊያ ላይ ባደረጉት ንግግር ከግድያ ተርፈው ለዚህ መብቃታቸውን የፈጣሪ ታምር ሲሉ ገልጸውታል። የሁሉም አሜሪካውያን ፕሬዝዳንት እሆናለሁ ያሉት ዶናልድ ትራምፕ በሃገር ውስጥ ህገወጥ ስደተኞችን ማባረር፣ ኢኮኖሚውን ማሳደግ እና ግብር መቀነስን በዋና ግብነት አስቀምጠዋል። በውጪ ግንኙነታቸውም የጋዛና የዩክሬይንን ግጭት መፍትሄ ከመስጠት ጀምረው አለምን ካጣችው ሰላም ጋር እንደሚያስታርቋት ቃል ገብተዋል።
ዶናልድ ትራምፕ የሪፐብሊካን ፓርቲ እጩነታቸው በይፋ ተቀበሉ። በሪፐብሊካን ፓርቲ ጉባኤ መዝጊያ ላይ ባደረጉት ንግግር ከግድያ ተርፈው ለዚህ መብቃታቸውን የፈጣሪ ታምር ሲሉ ገልጸውታል። የሁሉም አሜሪካውያን ፕሬዝዳንት እሆናለሁ ያሉት ዶናልድ ትራምፕ በሃገር ውስጥ ህገወጥ ስደተኞችን ማባረር፣ ኢኮኖሚውን ማሳደግ እና ግብር መቀነስን በዋና ግብነት አስቀምጠዋል። በውጪ ግንኙነታቸውም የጋዛና የዩክሬይንን ግጭት መፍትሄ ከመስጠት ጀምረው አለምን ካጣችው ሰላም ጋር እንደሚያስታርቋት ቃል ገብተዋል። ትራምፕ ላይ የተፈጸመው የግድያ ሙከራ
በትላንትናው ምሽት ዶናልድ ትራምፕ የሪፐብሊካን ፕሬዝዳንታዊ እጩነታቸውን በይፋ ተቀብለዋል። የግድያ ሙከራው በተደርገባቸው ቅጽበት በስተቀኝ በኩል የነበረወን የስደተኞች ጉዳይ መረጃ የያዘ ቻርት ለማየት ዞር ማለታቸው ህይወታቸውን እንዳተረፈው አውስተው፣ ለዛሬዋ ምሽት የበቁት በእግዛብሄር ድጋፍ መሆኑን ጠቁመዋል። በግድያ ሙከራው ወቅት ህይወቱን ላጣው ታዳሚና ለቆሰሉት ሁለት ሰወች የመታሰብያና የህሊና ጽሎት ተደርጓል።
በሃገሪቷ ውስጥ የሰፈነው መከፋፈል፣ መጠላላት እና ግጭት ባስቸኳይ መቆም አለበት ያሉት ዶናልድ ትራምፕ፣ የግማሹ ህዝብ ብቻ ሳይሆን የሁሉም አሜሪካዊ ፕሬዝዳንት እሆናለሁ ብለዋል። ዘንድሮ ከምንም ጊዜ በላይ በቁርጠኝነት ተነስተናል ያሉት ዶናልድ ትራምፕ እስካሁን የተከፈቱባቸውን ክሶች ኮንነዋል።ሃገሪቷ ብሁሉም አቅጣጫ እያሽቆለቆለ ነው ያሉት ትራምፕ፤ የዋጋ ግሽበቱን አስቆማለሁ፣ የወለድ ጫናን እቀንሳለሁ፣ አሜሪካ ውስጥ ነዳጅ በማውጣት የሃይል አቅርቦትን እጨምራለሁ ሲሉ ቃል ገብተዋል።
በፖሊሲ ራዕያቸው ላይም ትኩረታቸውን በግብር ቅነሳ፣ በስደተኞች ጉዳይ፣ በውጪ ጉዳይና በኢኮኖሚ ፖሊሲወች ላይ አድርገዋል። አሜሪካ በከፍተኛ የስደተኞች ቀውስ ውስጥ ናት ያሉ ሲሆን፣ ችግሩን ለመቅረፍም ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ህገወጥ ስደተኞችን ወደ ሃገራቸው የመመለስ ታላቅ ዘመቻ እጀምራልሁ ብለዋል። ፕሬዚዳንት ባይደን ለአሜሪካውያን ያደረጉት ንግግርና የትራምፕ መልዕክት
የውጪ ግንኙነትን በተመለከተ ዶናልድ ትራምፕ፣ አሜሪካ በማያገባት ቦታ ሁሉ እየዘለለች የማትገባበት፣ የግብር ከፋዩዋን ገንዘብ በየሃገሩ የማታፈስበት፣ ይልቁንም በራሷ የውስጥ ጉዳይ ላይ አተኩራ ያምትሰራበት ፖሊሲ ነው ያስቀመጡት ። በታይዋን፣ በኮርያ፣ በፊሊፒንስ እና በሌሎችም የአለም ሃገራት የጦርነት ዳመና አንዣቧል፤ አለም ወደ ሶስተኛው አለም ጦርነት ለመግባት ጠርዝ ላይ ደርሳለች ብለዋል ዶናልድ ትራምፕ። ሩሲያ በጆርጅ ቡሽ፣ በኦባማና በትራምፕ ዘመን ጆርጅያን፣ ክራይሚያን እና ዩክሬይንን መውረሯን አስታውሰው፣ በሳቸው ዘመን አንድም ነገር እንዳልወረረችና እንዳልወሰደች ጠቁመዋል።
እናም ገና ወደ ስልጣን እንደወጡ የሩሲያና የዩክሬይንንም ሆነ የእስራኤልና ፍልስጤምን ግጭቶች እንደሚያቆሙ ገልጸዋል። ቻይና በታይዋን ላይ የምታሳየውን እብሪት እንደሚያስተነፍሱ፣ ራሽያ ወደ ኪዩባ የላከችውን በኒዩክሌር የሚሰራ ባህር ሰርጓጅ መርከብም ልክ እንደሚያስገቡ ዝተዋል። ለመላው አለም በሙሉ ደሞ ማንኛውንም በእጃችሁ ያሉ አሜሪካውያን ታጋቾች እግሬ የኋይት ሃውስን በር ሳይረግጥ በፊት በአስቸኳይ ልቀቁ፤ አለዝያ ከባድ ዋጋን ትከፍላላችሁ ሲሉ አስጠንቅቀዋል። የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ዕጩዎች ክርክር በአትላንታ
ማንኛውንም የግጭት ጥንስስ በአንድ የስልክ ጥሪ ማቆም እችላለሁ ያሉት ዶናልድ ትራምፕ፣ የስልጣን ዘመናቸው በአለም ሁሉ ሰላም የሚሰፍንበት፣ የአሜሪካ ደህንነትም የሚረጋገጥበት መሆኑን ጠቁመዋል።አሁን አሜሪካ ያለችበት መንገድ አቅጣጫውን የሳተ መሆኑን ገልጸው ከትክክለኛ አመራር ጋ አሜሪካ ከገባችበት አረንቋ ውስጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ ትወጣለች ብለዋል።#የአሜሪካምርጫ2024 #USElection2024
አበበ ፈለቀ
ኂሩት መለሰ
ታምራት ዲንሳ