የተፈናቃዮች መልሶ ማቋቋም እና ስጋቶቹ
ሰኞ፣ ጥቅምት 19 2016ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከኦሮሚያ ክልል ከተለያዩ ዞኖች ተፈናቅለው አማራ ክልል የሚገኙ ተፈናቃዮች ቁጥር እጅግ ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ተፈናቃዮቹ ከሰሞኑ የሁለቱ ክልሎች አመራሮች በመልሶ ማቋቋም ሃሳብ ላይ መወያየታቸውን በመልካም መውሰዳቸውን ገልጸው ቢሆንም አሁንም ስጋቶች እንዳሏቸዉ ስደተኞቹ ይናገራሉ። እንደ ተፈናቃዮቹ ከመልሶ ማቋቋም ጎን ለጎን ዘላቂ መፍትሄ ሊታሰብ ይገባል ሲሉ ተማጽነዋል። የወለጋ ተፈናቃዮች ሮሮ
ከሶስት ዓመታት በፊት ሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞን ጃርደጋ ጃርቴ ከሚባል ወረዳ ተፈናቅለው አሁን ላይ ደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ ደጋን የተፈናቃዮች መጠለያ ካምፕ ውስጥ እንደሚገኙ ነግረውን አስተያየታቸውን የሰጡን ተፈናቃይ ከሰሞኑ የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬያቸው ለመመለስ የመከሩበትን ጉዳይ በአንክሮ ተከታትለናል ይላሉ፡፡ እንደ ተፈናቃዩ ገለጻ በዚህ የመጠለያ ካምፕ በግጭት መዘዝ ከምዕራብ ኦሮሚያ የተፈናቀሉ 600 እና ከአፋር ክልል የተፈናቀሉ 1400 ተፈናቃዮች ይገኛሉ፡፡ ተፈናቃዩ አክለውም በዚህ መጠለያ ካምፕ ይህን ያህል ከምእራብ ኦሮሚያ የተፈናቀሉ ዜጎች ይኑር እንጂ በደቡብ ወሎ ብቻ ግን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች በተለያዩ አከባቢዎች ተበታትነውም እንደሚገኑ ያስረዳሉ፡፡
ታዲያ የሁለቱን ክልሎች አመራሮች ውይይት በቅርበት ተከታትለው ስለ ወደ ፊቱ እጣፈንታቸው መምከራቸውን የሚገልጹት እኚህ ተፈናቃይ፤ ጥያቄ ፈጥሮብናል ያሉትንም አስተያየቶች በማጋራት ነው፡፡ “በዚያም ያሉ ተፈናቃዮች በመሰረተ ልማት እጦት ሲቸገሩ እዚህ ያሉ ተፈናቃዮች ይመለሱ ሲባል በምን አይነት መስፈርት ይመለሱ የሚለው ጥያቄ ፈጥሮብናል፡፡ ለዘላቂ ፍትህም ትያቄ አቅርበናል፡፡”የጃራ ካምፕ ተፈናቃዮች እሮሮ
አስተያየት ሰጪው ተፈናቃይ ያሳስበናል ያሉትንም አስተያየታቸውን አከሉ፤ “የሚያሳስበን በዋናነት ኦሮሚያ ክልል ከዚህ በፊት በተለያዩ አከባቢዎች ተበታትነን መኖራችን በሞትና መፈናቀሉ የችግር ገፈጥ ቀማሽ አድርጎናል፡፡ አሁንም በዚሁ አግባብ ብንሄድ ነገ ከነገ ወዲያ ለተመሳሳይ ችግር ላለመዳረጋችን ምን ዋስትና ይኖረናል ብለን ነው የምንሰጋው፡፡ ተመልሰን ስንቋቋም ማንነታችን ተከብሮልን ሰብዓዊ መብታችን ተከብሮ መሆን አለበት በመሚል ነው ህዝቡ የሚያነሳው፡፡፡”
ሌላም በደቡብ ወሎ ዞን በመጠለያ ካምፕ ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃይ አስተያየታቸውን ቀጠሉ፡፡ “ደቡብ ወሎ እና ሰሜን ወሎ ውስጥ ከአራቱም ወለጋ ዞኖች የተፈናቀሉ 16 የተፈናቃዮች ካምፕ ውስጥ ነው ያሉ፡፡ በብዛት ተገናኝተን እንወያያለን፡፡ አሁን የሁለቱ ክልሎች መንግስታት መልሶ ሊያቋቁሙን ማሰባቸውን ስንሰማ ጎን ለጎን መታሰብ ያለበት ነገር አለ፡፡ መሰረተ ልማትን አስቀድሞ መመለስ፡፡ ማቋቋሚያ ተሰጥቶን ተጠያቂነትም እንዲሰፍን እንፈልጋለን፡፡ በሚደረገው ውይይት ከዚህ ተፈናቃይ ተወካዮች ቀርበው ስጋቶችን ማቅረብና መፍትሄ መፈለግ ያሻዋል፡፡ ሰላም ያስፈልገናል፡፡ ግን ደግሞ ለዚ መድረክ ተመቻችቶ ልንወያይ ይገባል፡፡”ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬያቸው ለመመለስ ውይይት
ሰሜን ወሎ ጃራ የተፈናቃዮች ካምፕ ውስጥ መክረማቸውን የሚግልጹት ተፈናቃዮችም ስለሁለቱ ክልሎች አመራሮች ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬያቸው የመመለስ ውይይት በደስታ የሚቀበሉት መሆኑን አስረድተው፤ ጉዳዩን እስካሁን ከሚዲያ በዘለለ በቅርበት ከተፈናቃዮች ጋር ውይይት ተደርጎበት እንደማይታወቅ አስረድተውናል፡፡
ተፈናቃዮቹ መሰረተ ልማት መልሶ እንዲገነባ ይጠይቃሉ፡፡ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ የሚቻለው ተጠያቀዊነት ተረጋግጦ ፍትህ ሲሰፍን በመሆኑ ያም አስቀድሞ መረጋገጥ ይኖርበታል የሚል አስተያየታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ ጉዳዩ የሚመለከተው የመንግስት አካል ቀርቦ እንዲያወያያቸውም ይጠብቃሉ፡፡
ባለፈው ሳምንት ውስጥ የሁለቱ ክልሎች አመራሮች ተፈናቃዮቹን መልሶ ማቋቋም በሚቻልበት አግባብ ላይ መወያየታቸውን ተከትሎ ቃለ ምልልስ ያደረግንላቸው የኦሮሚያ ክልል ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ፤ ተፈናቃዮቹ ወደ ቀዬያቸው ሲመሉ በአከባቢው ህዝባዊ ውይይት ማድረግ፣ ተጠያቂነትን ማስፈን እና የመሰረተ ልማቶች መልሶ ጥገና ብሎም ተፈናቃዮች የሚቋቋሙበት ድጋፍ ከወዲሁ መታሰቡን መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡
ስዩም ጌቱ
አዜብ ታደሰ
ኂሩት መለሰ