1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተፈናቀሉት ወጣቶች ፈተና 

ዓርብ፣ ነሐሴ 28 2013

ከትግራይ ክልል አንስቶ ፣የአማራ እና የአፋር ክልሎችን ባደረሰዉ ጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሏል። የታደለው ወደ ቤተሰብ እና ዘመድ አዝማድ ሌላው ደግሞ የማያውቀው ቦታ ቀርቷል። በዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ያነጋገርናቸው ወጣት ተፈናቃዮች እንደገለፁልን የጦርነት ሰለባ እንሆናለን ብለው አስበውም አያውቁም።

https://p.dw.com/p/3zpr0
Äthiopien | Nefas Mewuch
ደቡብ ጎንደር: ንፋስ መውጫምስል Belete Tigabe

የተፈናቀሉት ወጣቶች ፈተና 

ፋንታ፤ ማየት ፣ የዓለም ወርቅ እና ሌሎች ሁለት ሴቶች ጦርነት ያስተዋወቃቸው የጋይንት ወረዳ ነዋሪዎች ናቸው። ይኖሩበት ከነበረው የደቡብ ጎንደር ወረዳ ተፈናቅለው በአሁኑ ሰዓት በአንዲት ገጠራማ መንደር ውስጥ ይገኛሉ። «ይህም የትግራይ ታጣቂዎች ጥቃት እና ዘረፋን ሽሽት ነው» ትላለች በቅርቡ ሴት ልጅ የተገላገለችው ፋንታ።  « የተሰደድነው ነሀሴ 7 ነው። እኔ በሰዓቱ ነፍሰ ጡር ነበርኩ። ሀኪም የሚባል የለም። የልጄ እትብት እንኴን በትክክል ስላልተቆረጠ እንብርቷ አብጣል። » ወጣቷን ያዋለዷት አብረው በሽሽት ላይ ያሉ ሰዎች ናቸው።
ሌላዋ ተፈናቃይ ማየት ሁለት ልጆች አሏት። 25 ዓመቷ ነው።  « በተፈጠረው  ችግር ድንገት ነው ተደናግጠን የወጣነው።» ትላለች። ባለቤቷ አብሯት የለም። ሊዋጋ ዘምቷል።

የዓለም ወርቅ 16 ዓመቷ ነው። የ 10 ኛ ክፍል ተማሪ ናት። አሁን ባለው ሁኔታ የሚመጣው ዓመት ወደ ትምህርት ቤት መመለስ መቻሏ ያጠራጥራል። ምክንያቱም እሷም ጦርነቱን ሸሽታ ትማርበት ከነበረው የጋይንት ወረዳ ተፈናቅላለች። ቤተሰቦቿ የሚኖሩት ሌላ አካባቢ ነው። « ከቀኑ ስምንት ሰዓት ላይ ነው የተሰደድነው። ከባድ ዝናብ እየጣለ ነበር። ነፍሴ አውጪኝ ብዬ ነው የተሰደድኩት። »  ሁሉም ተሰዳጆች ሴቶች እና ህፃናት ነበሩ።
ተፈናቃዮቹ ራሳቸውን ጦርነት ካለበት ቦታ ያሽሹ እንጂ ኑሮዋቸውን እንዴት እንደሚገፉ አያውቁም።  አራሶቹ እናቶች ከፍተኛ ችግር ላይ እንደሆኑ ነው ፋንታ የምትናገረው። « ህፃናት ማጠቢያ ሳሙና የለንም። የምንበላው የለም። መብራትም የለችም» ትላለች ፋንታ። እንደገለፀችልን የስልክ ባትሪ ለመሙላት ራሱ ችግር ነው። መብራት ያለበት ቦታ ሄደው እና ለምነው ስለሆነ ያላቸውን ብቸኛ ስልክ የሚሞሉት፤ ሲጠቀሙም እየቆጠቡ ነው። ብዙም ሳይቆይ ከዶይቸ ቬለ ጋር የነበራቸው የስልክ ግንኙነት ተቋረጠ። ከዚያ በፊት ግን ወጣት ማየት ትልቁ ምኞቷን ገልፃ ነበር። « ሀገር ተረጋግቶ ሰላም ተፈጥሮ ወደ ቤታችን ተመልሰን ልጆቻችንን ማሳደግ ነው የምፈልገው።

Äthiopien Geplündertes USAID-Lager in Nefas Mewcha
የተበዘበዘው የ USAID መጋዘን ንፋስ መውጫ (ደቡብ ጎንደር)ምስል Alemnew Mekonnen/DW

ሌሎቹ በዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ያነጋገርናቸው ወጣቶች ከአፋር ክልል የተሰደዱ ናቸው። በአሁኑ ሰዓት ቤተሰቦቻቸው ወደሚኖሩበት ወረባቦ ወረዳ ተሰደው ይገኛሉ። የ 25 ዓመቱ መሀመድ ነጋዴ ነበር። «አረፋን አክብረን በለበስነው ልብስ ነው የወጣነው።ተኩስ ሲሰማ ቶሎ ብለን ራሳችንን አወጣን» ይላል። ከዚሁ አካባቢ የተፈናቀለችው ሌላዋ ወጣት  21 ዓመቷ ነው። ከወንድሟ ጋር ምግብ ቤት ውስጥ አብረው ይሰሩ ነበር። « ወረባቦ ቤተሰብ ስለነበረን ወደዚህ መጣን። ብዙ ቤተሰብ እና መጠጊያ የሌለው ሰው አለ።» 

ያሲን 30 ዓመቱ ነው። በጦርነት ምክንያት ወደ ወረባቦ ወረዳ ከመፈናቀሉ በፊት ሱቅ ውስጥ ይሰራ ነበር። « መከላከያ ሲገባ እኛ ዘንድ የሚደርሱ አልመሰለንም ነበር። በሁለተኛው ቀን አዳራቸውን ተኩስ ጀመሩ።» ይላል። ያሲን እና ቤተሰቡ ተፈናቅለው ወደ ወረባቦ ከሄዱ አንድ ወር ተኩል እንዳለፋቸው ይናገራሉ። እስካሁን ከቤተሰብ ውጪ ምንም አይነት ርዳታ እንዳላገኙም ነው በጦርነት ምክንያት ከአፋር እና ከአማራ ክልል የተፈናቀሉት ጥቂት ወጣቶች ለዶይቸ ቬለ የገለፁት።

ልደት አበበ

ኂሩት መለሰ