1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተደጋገመው የተፈጥሮ አደጋ፣ የህዳሴው ግድብ የማመንጨት ኃይል፤ ግብጽ በሶማሊያ

ዓርብ፣ ነሐሴ 24 2016

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጥሮ አደጋ እየተደጋገመ መከሰቱን ቀጥሏል። ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን ከእጥፍ በላይ ማደጉ መገለጹ እንዲሁም ግብጽ ሶማሊያን ማስታጠቅ መጀመሯ የሰሞኑ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ ከሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

https://p.dw.com/p/4k6A3
ማዕከላዊ ኢትዮጵያ
በጎርፍ ከተጥተለቀለቁት አካባቢዎች አንዱ የሆነው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ አካባቢምስል Silite Zobe Government communication

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት


ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጥሮ አደጋ እየደረሰ በርካቶችን ለጉዳትና ለመፈናቀል መዳረጉ፤ ንብረትም ማውደሙ ይነገራል። በተለይም በዘንድሮው የክረምት ወቅት የወረደው ዝናብ በደቡባዊ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ያስከተለው የመሬት መናድ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወገኖችን ሕይወት ቀጥፏል። የመሬት መንሸራተቱ በሰሜን ኢትዮጵያም ሕይወት አሳጥቷል። በስልጤ የጎርፍ አደጋ በርጃቶችን ሲያፈናቅል በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ዶዶላ ወረዳ ደግሞ ከባድ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ እንስሳትን መግደሉ የእርሻ ማሳም መዋጡ ተነግሯል። የተፈጥሮ አደጋው ክስተት መደጋገም ካሳሰባቸው አንዱ፤ ገብረየስ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፤ «ዘንድሮ እንዴት ነው በሁሉም ኢትዮጵያ አካባቢ መሬት መደርመስ? ጸሎት ያስፈልጋል ሰው ሁሉ ለምድሪትዋ መጸለይ አለበት እንመለስ እግዚአብሔርም ይምረናል በየቤታችን ቀና አመለካከት ይኑረን» ሲሉ፤  ባለም ንብረት ደግሞ፤ «በጣም ያሳዝናል የሰው ልጅ ኃጥያት ነው በዚህ በቃ ይበለን» ነው ያሉት። አንዷለም ናቃቸው አለሙ በበኩላቸው፤ «ገና ይች ምድር አፏን ከፍታ ትውጠናለች ከባድ ነው በዚች በኢትዮጵያ ምድር ምን ያልተደረገ ግፍና መከራ አለ ወገኖቼ። እንመለስ በዚህ አካሄዳችን አያዋጣንም።» ይላሉ። ራቢያት ሀሰንም እንዲሁ ችግሩን ወደ ፈጣሪ ነው የሚያቀርቡት፤ «አላህ የባሰ አያምጣብን በአዛኝነቱ ይሁንበት በመሃሪነቱ ይማረን በይቅርባይነቱ ይማረን ። መቼም በሀገራችን ይደረጋሉ ብለን የማናስባቸው ግፎች እየፈጠርን ጭካኔያችን ከልክ አለፈ። ይሄው ፈጣሪያችንም በርቀት በሌሎች ሃገራት አየሰማን የዘገነንን በእኛ ሀገር ሰምተን የማናውቀውን መከራዎች በየቦታው እያደረሰ ቁጣውን እያሳየን ነው። ሁሉላችንም በየእምነታችን ፈጣሪን እንማፀን።» ብለዋል። 
አሜክስ ልጅ በበኩላቸው፤ «ለኛ ክፋትስ ቅጣቱ ያንሳል» ባይ ናቸው። ጀሚላ መኮንን መኮንን፤ «ያአላህ ከባድነው ዘንድሮ» ነው የሚሉት። እማዋይሽ ጌትነት ግን ይጠይቃሉ፤ «ዘንድሮ ግን ዝናብ በዛ ማለት ነው» በማለት። ኤቶ ኦቴ ደግሞ፤ «በሰው ክፋትና ተንኮል እንስሶችም ጭምር ተሰቃዩ ወገን ለሀገር ሰላም አሁንም ሰው እንሁን ሰው» ብለዋል። በነገራችን ላይ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ካጋሩት ብዙዎች ሰዎች በሚፈጽሙት ክፉ ተግባር ምክንያት የመጣ የፈጣሪ ቁጣ እንደሆነ በማመላከት ነው የሞከሩት። ኃይለ ሚካኤል ገብሬ ግን፤ ሺመልስ አብዲሳ ያዘነበው የብልፅግና ዝናብ ነው። ተረጋጉ» ነው ያሉት፤ ነጋ አይናለም ደግሞ፤ «ዝናብ ማውረድ እችላለሁ ያለ መንግሥት እንዴት መመጠን አቃተው?» ሲሉ ይጠይቃሉ። ሰው መሆን ይቀድማል የተባሉት የፌስቡክ ተጠቃሚም ጠያቂ ናቸው፤ «ዘንድሮ ዝናብ አብዷል ልበል?» ሲሉ፤ ወርቁ አደራጀው ግን፤ «ፈጣሪ ሆይ ምህረት ላክልን፤ ፖለቲከኞችም ከማይረባ ጎጠኝነት ወጥታችሁ ደም ከመፋሰስ ውጡልን ምርጥ ኢትዮጵያንም ታደጓት» ነው ያሉት። ዘመኑ ዓለም፤ «ጦርነት፣ ጎርፍ፣ ድርቅ፣ መሬት መንሸራተት፣ ኑሮ ውድነት፣ ሌብነት፣ ውሽት፣ ዘረኝነት፣ ተደምረው ኢትዮጵያውያን ሊያጠፏት? የመደመር ምልክቶች ናቸው።» ይላሉ። በየቦታው ደረሰ የሚባለው የተፈጥሮ አደጋ ያሳሰባቸው አሌክስ አለሙ ሳፎሬ ግን፤«ፈጣሪ ሆይ በቃ በለን!» ብለዋል። 


አርሲ ዞን ዶዶላ ወረዳ
ጎርፍና የመሬት መንሸራተት ከፍተኛ አደጋ ያስከተለበት አርሲ ዞን ዶዶላ ወረዳምስል Dodola communication


ሌላው የበርካቶችን ትኩረት የሰባው ኢትዮጵያ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ የምታመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን ከእጥፍ በላይ ማሳደግዋን ማስታወቋን ያመለከተው ዜና ነው። አደም አማን፤ «ድፍረት የተሞላበት እርምጃ፤ በዚሁ ቀጥሉ» በማለት ሲያበረታቱ፤ ካሌብ ካስትሮ ግን መረጃውን ያመኑም አይመስሉም፤ «እውነት ከሆነ ክፍለ ሀገር እንኳ ኤሌክትሪክ ሊዳረስ ለመዲናችን አፍንጫ ስር ላይ በኤሌክትሪክ ሀይል ዕጦት ፍዳችንን ለምንበላ ሰዎች እስቲ የፍጆታ ክፍያ ብቻ ሳይሆን የሀይል መጠኑንም እጥፍ አድርጉልና አስደስቱን። ያኔ ነው አባይ ግድብ የምር መገደቡን የምናረጋግጠው።» በማለት አስተያየታቸውን በሳቅ አጅበው አጋርተዋል። የኤሌክትሪክ ኃይል በእጥፍ የማመንጨቱ ዜና ብዙዎችን ያስደሰተ ቢሆንም በሀገሪቱ የሚታየውን ተጨባጭ ሁኔታ መሠረት በማድረግ ጥያቄና ጥርጣሬያቸውን ያጋሩ ግን ይበረክታሉ። አባት አባት ከእነዚህ አንዱ ናቸው፤ «የኢትዮጵያ ሕዝብ ያገኘው ተጨማሪ ነገር ግን እስካሁን ምንም ነው። ሁሉም ነገር ለፖለቲካ ፍጆታ ነው የሚወራው።» ባይ ናቸው። ትዕግሥት ይልማ ደግሞ፤ «100 ጊዜ ቢያመነጭ ሕዝብ ከጨለማ አልወጣም» ነው የሚሉት። «ምን ቢታለብ ያው በገሌ አለች ድመት» ያሉት ደግሞ ሃና በላይ ናቸው። አሞኘ አንዷለምም፤ «ኧረ እኛ ሠፈር ያው ጨለማ ነው» ይላሉ፤ ጊዜ ለኩሉ፤ «ሰሞኑን እኮ መብራት ሲጠፋ ምንድነው ብዬ ለካ ህዳሴው ኃይል አመነጨ ለማስባል ወደ ህዳሴው አካባቢ ኃይል ተቀንሶ ነው አይይ ጆካ» በማለት ግምታቸውን አጋርተዋል።  ደነቀ ታደሰ ደግሞ፤ «ለዚህ ነው በየሦስት ወሩ የፍጆታ ታሪፍ የሚጨምረው» ብለዋል። 
ከኅዳሴ ግድብ የሚመነጨው ኤሌክትሪክ ለውጭ ገበያ መዋሉን መነሻ ካደረጉ አስተያየት ሰጪዎች መካከል ወንድማገኝ ጌታቸው፤ «ለሱዳን ወይስ ለኢትዮጵያ» በማለት ሲጠይቁ፤ አብዱላዚዝ አወድም እንዲሁ፤ «እኛ እዚሁ የግድቡ አጠገብ ሆነን ያላወቅነዉ ወይም ያላየነዉ ለሱዳን ነው ለኤርትራ ፣ ወይስ ለኬንያ ነዉ ኃይል እየሰጠ ያለው?»ብለው ጥያቄ አክለዋል። ደረጀ ደምሴም፤ «ጠቅላይ ሚንስትሩ ኃይሉን እስከ አውሮፓ ድረስ እንሸጣለን ብለዋል እኮ ገና ከአፍሪካም አልፎ ዜጋው ሻማ እየተጠቀመ» ሲሉ፤ ቶም ፀሐይ ደግሞ፤ «ይገርምሀል ሕዝቦቿ በጨለማ ተውጠው ለሱዳን በነፃ የምትለግስ ብቸኛዋ አገር እኮ ነች ሲገነባ ግን የወርቅ ዋንጫ እየተባለ ዛሬም በኩራዝ መከራዋን የምትበላዋ እናት ከመቀነቷ ፈትታ ለግሳለች» ብለዋል።

ታላቁየህዳሴ ግድብ
ታላቁ የህዳሴ ግድብፎቶ ከማኅደርምስል Amanuel Sileshi/AFP/Getty Images

በእሱ ፈቃድ ግን፤ «ተመስገን ነው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነውና መጨረሻውን ያሣምርልን።  ለእኛ ሳይሆን ለትውልዱ ዋስ ነውና።» ነው የሚሉት። ሙሌ ሙሌ ደግሞ፤ «ለኛ ምን ጠቀመን የመብራት ክፍያ አልቀነሰልን ጭራሽ ባሠበት» ይላሉ። ዮሐንስ ጆኒም የእሳቸውን ሃሳብ ይጋራሉ፤ «እኔን የሚገርመኝ ኃይል ተጨመረ አልተጨመረ ለእኛ ጠብ የሚል የለም። ምክንያቱም መብራት ላይ ዋጋ ለመጨመር እየፎከረ ነው። ስለዚህ ሀይል ቢጭምር ባይጨምር የእናንተ ጉዳይ እንጂ የእኛ ሊሆን አይችልም።» ነው የሚሉት። 
መተኪያ ማሞ በበኩላቸው፤ «እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ፤ በዐባይ ወንዝ ለመጠቀም የኢትዮጵያ ጊዜ ነው።» ሲሉ፤ ሹምባ ማታጎም፣ «ገና ሌላ ግድብ እንጀምራለን ሀብታችንን በማስፈራራት ሳይሆን በልምና መጠየቅ ያለባቸው።» ነው ያሉት። አብ ኢትዮጵያን የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ በበኩላቸው፤ «አያልቅም እንዴ ይሄ ነገር? ከ12 ዓመት በላይ ሆነው ስጦታም ሲዘገይ ያቅራል።» ይላሉ፤ እስከዳር ሰጠኝም፤ «ላም አለኝ በሰማይ ሆነብን መቼ ይሆን ገቢ ማስገኘት ሚጀምረው?» በማለት ይጠይቃሉ። ኢብራሂም አህመድ ደግሞ ከኃይል ማመንጨትና አገልግሎቱ ወጣ ብለው፤ «ስመኘው በቀለ ይኸን ሳያይ መሞቱ ይቆጨኛል። ህልሙ እውን መሆኑ ያስደስታል። መቼም አንረሳህም ስሠኘው።» ሲሉ መሀመድ የኑስም፤ «ስለ ግድቡ ሲዘገብ ወንድማችን ሱሌማን አብደላ ውስጤ ላይ ይመላለሳል አሏህ በቅርብ ኸይር ያሰማን» ብለዋል። መሰለ ሶመኖ ለዕላጎ ግን፤ «የምርጫ ጥሩምባ» ብለውታል። መንግሥቱ ካሣውም፣ «በእጥፍ ጨመረ አልጨመረ ከጨለማ ከጦርነት ከረሀብ ከመፈናቀል ከመታገት ወዘተ አልወጣን» ነው ያሉት።


የሶማሊያ የባሕር ጠረፍ
የሶማሊያ የባሕር ጠረፍ ጠባቂ ፖሊሶች ፎቶ ከማኅደር ምስል Jackson Njehia/AP Photo/picture alliance


ግብፅ ለሶማሊያ የጦር መሣሪያ ማስታጠቅ መጀመርዋ እየተነገረ ነው። ዲፕሎማቶችና የሶማሊያ ባለሥልጣናትን በምንጭነት የጠቀሰው ሮይተርስ የዜና አገልግሎት እንደሚለው የተለያዩ ጦር መሣሪያዎችና ጥይቶችን የጫኑ ሁለት የግብፅ የጦር አዉሮፕላኖች ሰኞ ጠዋት ሞቃዲሾ አውሮፕላን ማረፊያ ደርሰዋል። ይህን መረጃ ከሰሙት መካከል ታደለ ቃንሹሜ፤ «ግብፅ ወደ ሶማሊያ መሳርያ ጭና ልታመጣ ትችላለች ነገር ግን ልብ ከየትም ልታመጣ አትችልም። ማንም ይሁን ማወቅ የሚገባዉ የእኛ ኢትዮጵያዉን መሳርያ ልባችን፡ ምን ጊዜም ኢትዮጵያ ታሸንፋለች።» ብለዋል። ፍሬው ሙሉጌታ ግን፤ «ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ላደረገችው አስተዋጽኦ ይህ አይገባትም ቢሆንም ፈጣሪ አይረሳንም!» ይላሉ። ሀሰን ከድር በበኩላቸው፤ «ግብፅ ለራሷ ጥቅም እንደምትታገል ኢትዮጵያም ጥቅሟን ለማስጠበቅ ትታገላለች።» ነው የሚሉት። አሊ አህመድ፤ «የግብፅ ጠላትነት ዛሬ የጀመረ አይደለም፤ በደማቸው አለ ለዘላለም። ይህን አውቀን ጠንቀቅ ማለት ጥሩ ነው።» ባይ ናቸው። አቶ ገሞራው ደግሞ፤ «መላዉ ኢትዮጵያዉያን ችግሮቻችንን ቁጭ ብለን እንፍታ በግብፅም ላይ በአንድነት እንነሣ።» የሚል ጥሪ አቅርበዋል። ወንጌል ይልማ ከልሌ በበኩላቸው፤ «እነሱ ከአባቶቻቸው አይበልጡም እኛም ከአባቶቻችን አናንስም» ነው የሚሉት፤ በፍቅርሽ መያዜ የተባሉት ሌላው የፌስቡክ ተጠቃሚ ደግሞ፤ «ሰላም ለምሥራቅ አፍሪቃ ይሁንልን» ብለዋል። ካር ካሬቶል ደግሞ፤ «ግብፅ ጎረቤታችን ሆነች።» ብለዋል በአጭሩ። እኛም በዚሁ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ጥንቅርን አበቃን።

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ