1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ

ሰኞ፣ መስከረም 21 2005

አባስ እስራኤል በፍልስጤም ግዛቶች የምታስገነባዉን የአይሁድ ሠፈራ መንደርም የፍልስጤሞችን ዘር ለማጥፋት ያለመ በማለት አዉግዘዋል።ሁሉም ሰሟቸዉ።እስራኤልን ጨምሮ የጥቂቶቹ ግን የዓለም ዘዋሪዎች ትኩረት ግን ከሶሪያ ቀጥሎ የኢራን የኑክሌር መርሐ-ግብር እንጂ የፍልስጤሞች ጩኸት፥ ተማፅኖ አይደለም።

https://p.dw.com/p/16IMc
Qatar Emir Shek Hamad bin Kalifa Al-Thaniduring the UN General Assembly at the United Nations on September 25,2012 in New York. AFP PHOTO / ERIC FEFERBERG (Photo credit should read ERIC FEFERBERG/AFP/GettyImages)
የተመድ ጉባኤምስል Eric Feferberg/AFP/GettyImages

01 10 12



የልዕለ-ሐያሊቱ ትልቅ ሐገር ትልቅ ከተማ ኒዮርክ ስልሳ-ስድስት ዓመት እንዳደረገችዉ ሁሉ የዓለም ታላቅ ፖለቲካዊ ድግስን አስተናገደች።ኒዮርኮች ከዓለም ትልቅ ድርጅት ትልቅ አዳራሽ የታደሙ እንግዶቻቸዉን ለማየት፥ ለመስማት ጊዜ ከነበራቸዉ መጡ፥ ተናገሩ ሔዱ ይሉ ይሆናል።አሉም አላሉ የሆነዉ፥ ይኸዉ ነዉ።ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ኒዮርክ የታደሙት የዓለም መሪዎች የየራስ፥ የየወዳጆቻቸዉን ዕቅድ ምግባር አወድሰዉ፥የየደካማ ጠላቶቻቸዉን ምግባር አዉግዘዉ ተለያዩ።የዓለም ፖለቲካዊ ዑደትም በነበረበት ዛቢያ መሾሩን ቀጠለ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ መነሻ፥ የጉባኤተኞቹ የጎላ መልዕክት ማጣቃሻ የዓለም ፖለቲካዊ ሒደት መድረሻችን ነዉ፥ ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።

                  
ተሰናባቹ የሶማሊያ ጠቅላይ ሚንስትር አብዲወሊ መሐመድ ዓሊ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሐገራቸዉ ሠላም ለማስፈን ላደረገዉ ድጋፍ ኒዮርክ ላይ ሲያመሰግኑ ርዕሠ-ከተማ ሞቃዲሾ ዉስጥ እሳቸዉ ከአመት በፊት ጠቅላይ ሚንስትርነቱን የተኳቸዉ መሐመድ አብዱላሒ መሐመድ (ፈርማጆበቅፅል-ስማቸዉ) በጠቅላይ ሚንስትርነት መሾማቸዉ ተወራ።

የወሬዉ እዉነት-ሐሰትነት እስካሁን አልተረጋገጠም።ተሰናባቹ ጠቅላይ ሚንስትር አብዲወሊ መሐመድ ዓሊ ለኒዮርክ ጉባኤተኞች እንደተናገሩት ግን አዲስ ፕሬዝዳት ሾማ፥ አዲስ ካቢኔ ለመመሥረት አንድ ሁለት የምትለዉ ሶማሊያ መሠረታዊ ችግሯ አሁንም የሠላምና ፀጥታ መታወክ ነዉ።ዋና ጠላቷ ደግሞ አክራሪዉ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አሸባብ።

የኒዮርኩ ጠቅላላ ጉባኤ ከመከፈቱ ከሁለት ቀናት በፊት ደግሞ አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳት ሐሰን ሼኽ መሐሙድ የመንግሥታቸዉን ዋና ጠላት አሸባብ የፈጠረዉን ሥጋት ለማስወገድ አዲሱ መንግሥታቸዉ አዲስ ዕቅድ መንደፉን አስታዉቀዉ ነበር።የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ በኒዮርኩ ንግግራቸዉ እንደጠቀሱትም በሶማሊያ አዲስ ፕሬዝዳት መመረጡ  ለሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር አብነት ነዉ።
                   
«ባለፈዉ ዓመት በማላዊና በሴኔጋል ሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር፥ በሶማሊያ ደግሞ አዲስ ፕሬዝዳት ሥልጣን መያዛቸዉን አይተናል።»  

ከኒዮርኩ ጉባኤ ጎን ሥለ ሶማሊያ የተወያየ አነስተኛ ስብሰባም እዚያዉ ኒዮርክ ዉስጥ ተሰይሞ ነበር።የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩን የመሩት ስብሰባ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ  ለአዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳትና ለሚመሩት አዲስ መንግሥት ድጋፉን እንደሚሰጥ በድጋሚ ቃል የገባበትም ነበር።

አሸባብን ከሶማሊያዋ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ኪስማዮ ያስወጣዉ ግን የኬንያ መራሹ የአፍሪቃ ሕብረት ጦር ድብደባ እንጂ የሐገሪቱ ተሰናባች ጠቅላይ ሚንስትር የኒዮርክ ንግግር፥ ካሜሩን የመሩት ስብሰባ፥ የኦባማም መልዕክት ወይም የአዲሱ ፕሬዝዳት ዕቅድ አይደለም።

አዲሱን ፕሬዝዳትን በተመረጡ ሳልስት የሳተዉ የአሸባብ የቦምብ ጥቃት የሞቃዲሾ ምግቤት ታዳሚዎችን አልሳተም።የኒዮርኩ ጉባኤ፥ ከመጀመሩ ጥቂት ቀደም ብሎ ሞቃዲሾን ባሸበረዉ ቦምብና ጥይት አስራ-ስምንት የከተማይቱ ነዋሪዎች ተገድለዋል።ከሟቾቹ ሰወስቱ ጋዜጠኞች፥ አንዱ የአዲሱ የሶማሊያ ምክር ቤት እንደራሴ ነበሩ።

ድንበር የለሽ ዘጋቢዎች የተሰኘዉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ትናንት እንዳስታወቀዉ ደግሞ ሶማሊያ ዉስጥ ባለፈዉ ቅዳሜና እሁድ ሁለት ተጨማሪ ጋዜጠኞች ተገድለዋል።አስረኛ ወሩን ዛሬ በጀመረዉ በጎርጎሮሳዉያኑ ሁለት ሺሕ አስራ-ሁለት ሶማሊያ ዉስጥ በሰዉ እጅ የተገደሉት ጋዜጠኞች ቁጥር አስራ-አምስት ደርሷል።

የሰሜንና የደቡብ ሱዳን መሪዎች ኒዮርክ ድረስ ሔደዉ አንዱ ሌላዉን ከማዉገዝ፣ ማሳጣት አዲስ አበባ ቆይተዉ መደራደር መስማማታቸዉ ለየሐገሮቻቸዉ ሠላም ጥሩ ተስፋ፥ ለየራሳቸዉም አድናቆትና ምስጋና ነዉ ያተረፈዉ።

በዘንድሮዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የሶሪያዉን ጦርነት ያሕል ብዙ የተወራ፥ የተነገረለት፥ ከደማስቆ ገዢዎች እኩል የተወገዘ፥ የተብጠለጠለ ሥርዓት የለም።ኦባማ ጀመሩ።
                     
«የሶሪያ ሕዝብ ስቃይ እንዲያበቃና አዲስ ጎሕ እንዲፈነጥቅ፥ የበሽር አል-አሰድ ሥርዓት እንዲወገድ አሁን እዚሕ እንደተሰበሰብንም በድጋሚ እናሳስባለን።»

የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩን ደገሙት።
               
«አሰድ በራሳቸዉ ሕዝብ ላይ ያደረሱትን ግፍ የሚጠራጠር ሰዉ ከነበረ፥ ሴቭ ዘ-ችልድረን በዚሕ ሳምንት ያሳተመዉን ዘገባ ይመልከት።ትምሕር ቤቶች የማሰቃያ ማዕከላት ሆነዋል።ልጆች ለኢላማ መለማመጃ ሆነዋል።የነዚሕ ልጆች ደሞ ለዚሕ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በግልፅ የሚታይ ዘግናኝ ሐቅ ነዉ።»

የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጊዶ ቬስተርቬለ አሰለሱ።ቬስተርቬለ እንደ ዲፕሎማሲዉ ወግ በተዘዋዋሪ የወቀሱት በሶሪያ መንግሥት ላይ እርምጃ እንዳይወሰድ ያገዱትን ሩሲያንና ቻይናን ነዉ።
               
«የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት የሶሪያ ሕዝብን ደሕንነት ለማስጠበቅ ያለበትን ሐላፊነት እስከ ዛሬ በቅጡ አልተወጣም።ይሕን አጥብቄ እተቻለሁ።በፀጥታዉ ምክር ቤት የታየዉ እገዳ የመጨረሻዉ ቃል ሊሆን አይገባም።»

የቱርክ፥ የቀጠርና የሌሎችም የሶሪያ ተቃዋሚዎችን በቀጥታ የሚረዱት መንግሥታት መሪዎችና ተወካዮች መልዕክት የአሰድን መንግሥት የሚያወግዝ፥ የአሰድ መንግሥትን ይረዳሉ የሚባሉትን ሩሲያና ቻይናን ከጥንቃቄ ጋር የሚተች ነበር።

የቀጠሩ አሚር ሐማድ ቢን ከሊፋ አ-ሳኒ የሶሪያዉን ዉጊያ ለማስቆም የአረብ ሐገራት ጦር እንዲዘመት ጠይቀዋል።አሳኒ እንደሚሉት የሊባኖስን ጦርነት ለማስቆም በ1970ዎቹ አረቦች ጦር እንዳዘመቱ ሁሉ አሁንም ወደ ሶሪያ ማዝመት አይገዳቸዉም።

የሩሲያዉ ፕሬዝዳት ቭላድሚር ፑቲን በመንግሥታቸዉ ላይ በቀጥታም በተዘዋዋሪም ለተሰነዘረዉ ትችትና ወቀሳ አፀፋዉን ለመስጠት ኒዮርክ ድረስ መሔድ አላስፈለጋቸዉም።
                
«የሐይል እርምጃ ቀርቶ፥ የተባበሩት መንግሥታትን ሁለንተናዊ ቻርተር በተወሰኑ ወገኖች ፍላጎትና ሥምምነት ለመቀየር መሞከር ጥሩ እንዳልሆነ ግልፅ ነዉ።እንዲሕ አይነቱ እርምጃ አለመረጋጋትና ሁከትን ነዉ የሚያስከትለዉ።ይሕ እንደሚሆንና እኛ ትክክል መሆናችንን ደግሞ በቅርቡ  አይተናል። ሰዉ ካለፈዉ መማር አለበት።

ከሕዝባዊ አመፅ ድል በሕዋላ በተደረገ ምርጫ ሥልጣን የያዙት አዲሱ የግብፅ ፕሬዝዳት መሐመድ ሙርሲ የሶሪያን መንግሥት ከሌሎቹ እኩል ማዉገዛቸዉ አልቀረም።የሶሪያዉን ጦርነትም የዘመናችን ድቀት ብለዉታል።የዉጪ ጦር ጣልቃ ይግባ የሚለዉን የአሳኒና የብጤዎቻቸዉን ሐሳብ ግን በእሳቱ ላይ ነዳጅ ከማርከፍከፍ ነዉ-የቆጠሩት።
                       
«በሶሪያ የዉጪ ጦር ጣልቃ ከገባ መዘዙ አደገኛ ነዉ-የሚሆን።»

እንደ ኢራቅ፥ እንደ ሊቢያ፥ እንደ ሶማሊያ ወይም እንደ አፍቃኒስታን ሶሪያ የዘመተ የዉጪ ጦር በርግጥ የለም።ለሶሪያ አማፃያን ከዉጪ የሚሰጠዉ ድጋፍና ርዳታ ግን ዕለት በዕለት እየጨመረ ነዉ።ባራክ ኦባማ የኒዮርክ ንግግራቸዉን እንዳበቁ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሒላሪ ክሊንተን መንግሥታቸዉ ለሶሪያ አማፂያን የሚሰጠዉን ርዳታ መጨመሩን አስታዉቀዋል።
                 
«ዩናይትድ ስቴትስ እየጠበቀች አይደለም።ለሶሪያ ሕዝብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣዉን ሰብአዊ ርዳታ ጥያቄ ለማሟላትና እና ተቃዋሚዎች ወደ ሁሉን አቀፍ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለመደገፍ፥ በሥርዓቱ ላይ ይበልጥ ግፊት ለማድረግና ለማግለል አዲስ እርምጃዎች እየወሰድን ነዉ።»

ሶሪያም ትተረማመሳለች።በጣሙን አሌፖ።ሕዝቧም ይረግፋል።ፍልስጤሞች የነፃነት ጥያቄያቸዉን ለስልሳ-ሰባተኛ ዓመት አነሱ።እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ከ1970ዎቹ ጀምሮ ሊቀመንበር ያሲር አረፋት በየዓመቱ ያሉ፥ የተናገሩትን የነፃነት ጥያቄ ማሕሙድ አባስ ሥልጣን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ ያልደገሙበት ዓመት የለም።ዘንድሮም ደገሙት።
                      
«ከአካባቢያዊ ድርጅቶችና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ሐገራት ጋር ያላሰለሰ ዉይይት እየተካሔደ ነዉ።የተባበሩት መግሥታት ድርጅት በዚሕ ጉባኤዉ ፍልስጤምን መንግሥት ያልሆነች አባሉ አድርጎ እንዲቀበል እንጠይቃለን።»

አባስ እስራኤል በፍልስጤም ግዛቶች የምታስገነባዉን የአይሁድ ሠፈራ መንደርም የፍልስጤሞችን ዘር ለማጥፋት ያለመ በማለት አዉግዘዋል።ሁሉም ሰሟቸዉ።ብዙዎች ምናልባት ከፈንራቸዉን መጠዉ፥ አዝነዉ፥ ደግፈዋቸዉም ይሆናል።እስራኤልን ጨምሮ የጥቂቶቹ ግን የዓለም ዘዋሪዎች ትኩረት ግን ከሶሪያ ቀጥሎ የኢራን የኑክሌር መርሐ-ግብር እንጂ የፍልስጤሞች ጩኸት፥ ተማፅኖ አይደለም።
«ኢራን የኑክሌር ቦምብ እንዳትታጠቅ ማድረግ ያለብንን ሁሉ ዩናይትድ ስቴትስ ታደርጋለች።»

የሌሎች የምዕራባዉያን ሐገራት መሪ፥ ተወካዮችም ተመሳሳዩን መልዕክት ደጋገሙት።የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከመድረኩ የወጡት እንደ ኬሚስትሪ መምሕር የቦምብ ምናልባትም የኑክሌር ቦምብ ሥዕል ይዘዉ ነበር።ካከንገቱ ላይ ቀይ ያሰመሩበትን የቦምብ ሥዕል ለጉባኤተኞች እያመለከቱ በኢራን ላይ ዉግዘታቸዉን፥ ኢራንን ለመዉጋት በሚያንገራግረዉ ዓለም ላይ ደግሞ ትችታቸዉን ያወርዱት ያዙ።    
                  
«አል-ቃኢዳ ኑክሌር የታጠቀባትን ዓለም አስቡ።ይሕን አደገኛ መሳሪያ ከዓለም እጅግ አደገኛ የሆነ አሸባሪ ሥርዓት ይታጠቀዉ ወይም ከዓለም እጅግ አደገኛ የሆነ አሸባሪ ቡድን ይታጠቀዉ ብዙም ልዩነት የለዉም።»

የኢራኑ ፕሬዝዳት ማሕሙድ አሕመዲኒጃድ እስራኤልን «ያስልጠነች ፅዮናዊት» በማለት ነበር ያጣጣሏት።
                 
«የአልሰለጠኑት ፅዮናዉያን ታላቅዋ ሐገሬን በጦር ሐይል ለማጥቃት በተደጋጋሚ እየዛቱ ነዉ።ይሕ (በግልፅ የሚታይ) የዓለም መራር ሐቅ ነዉ።»

የመሪዎቹ የዘንድሮዉ የመሪዎች ንግግር፥ ዛቻ፥ ፉከራ፥ አፀፋ ዛቻ፥ ፉከራ ከኒዮርክ አበቃ።ጉባኤዉ ግን በዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ወይም በአምባሳደር ደረጃ ቀጥሏል።አምናም እንዲሕ ነበር።የቀድሞዉ የጀርመን ዲፕሎማት እንደሚሉት ግን የዘንድሮዉ ያምናዉን ያክል እንኳን አይደለም።
             
«በመሠረቱ ከቀዳሚዉ አመት ጋር መነፃፀር ያለበት።በዚሕ ዓመት ከፍተኛ ዉሳኔዎች ይተላለፉበታል ተብሎም አይጠበቅም ነበር።ብዙዉ ነገር ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ ከሚካሔደዉ የምርጫ ዘመቻ ጋር የተያያዘ ነዉ።ሁሉም በተለይ አሜሪካኖች ትኩረታቸዉ ምርጫዉ ላይ ነዉ።»

ዓለምም ከጉባኤዉ በፊት በነበረችበት ትረግጣለች።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

Iran's President Mahmoud Ahmadinejad speaks during the 67th United Nations General Assembly at U.N. headquarters in New York, September 26, 2012. REUTERS/Mike Segar (UNITED STATES - Tags: POLITICS)
አሕመዲኒጃትምስል Reuters
NEW YORK, NY - SEPTEMBER 27: Benjamin Netanyahu, Prime Minister of Israel, pauses after drawing a red line on a graphic of a bomb while discussing Iran during an address to the United Nations General Assembly on September 27, 2012 in New York City. The 67th annual event gathers more than 100 heads of state and government for high level meetings on nuclear safety, regional conflicts, health and nutrition and environment issues. (Photo by Mario Tama/Getty Images)
ኔታንያሁምስል Getty Images
U.S. President Barack Obama addresses the 67th United Nations General Assembly at the U.N. headquarters in New York September 25, 2012. REUTERS/Mike Segar (UNITED STATES - Tags: POLITICS)
ኦባማምስል Reuters

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሰ