የተመድ ሠራዊት ከማሊ መዉጣት፣የሳሕል ትብብር
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 1 2015070723
ማሊ የሠፈረዉ የዉጪ ሠራዊት መዉጣት
የተባበሩት መንግስታት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ማሊ የሠፈረዉ ድርጅቱ ሠላም አስከባሪ ሠራዊት እስከ 2023 ማብቂያ ድረስ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ምዕራብ አፍሪቃዊቱን ሐገር ለቅቆ እንዲወጣ ወስኗል።ምክር ቤቱ MINUSMA በሚል ምሕፃረ ቃል የሚጠረዉ ሠራዊት ተልዕኮ እንዲቋረጥ የወሰነዉ የማሊ መንግስት በተደጋጋሚ ባደረገዉ ጥሪና ግፊት ምክንያት ነዉ።
ታዛቢዎች እንደሚሉት ዉሳኔዉ ለማሊ፣ለተመሳሳይ ተልዕኮዎችና ከ1000 በላይ ወታደሮችን ላዘመተችዉ ለጀርመን ጨምሮ ወታደር ላዘመቱ ሐገራት ሁሉ ጫና ማሳደሩ አይቀርም።ግን የማይጠበቅ አልነበረም።ኮሎኔል አስሚ ጎይታ የመሯቸዉ የጦር መኮንኖች የማሊን የሲቢል አስተዳደር አስወግደዉ ሥልጣን ከያዙ ከግንቦት 2021 ወዲሕ ማሊ ከአብዛኛዉ ዓለም ጋር ያላት ግንኙነት የተበላሸ ነዉ።
ማሊ አባል የነበረችበት የምዕራብ አፍሪቃ የምጣኔ ሐብት ማሕበረሰብ (ECOWAS) ማዕቀብ ጥሎባታል።የቀድሞ የማሊ ቅኝ ገዢ ፈረንሳይና በፈረንሳይ በኩል ሌሎች ምዕራባዉያን መንግስታትም የባማኮ ገዢዎችን «አይናችሁ ላፈር» እያሏቸዉ ነዉ።ፈረንሳይ ለምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሐገር የቀድሞ ቅኝ ገዢ ብቻ ሳትሆን በ2012 የቱአሬግ አማፂያን የባማኮን ማዕከላዊ መንግሥት ሲፈታተኑ ፓሪሶች «አሸባሪዎችን ለመዉጋት» ላሉት ተልዕኮ በርካታ ወታደሮችን አዝምተዋል።
የማሊ ወደራዊ ገዢዎች ከፓሪሶች ጋር የገጠሙት እሰጥ አገባ ተካርሮ የፈረንሳይ ብቻ ሳይሆን በፈረንሳይ ግፊትና የፈረንሳይን ጦር ተከትሎ ማሊ የሰፈረዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሠራዊትም ከማሊ ነቅሎ እንዲወጣ የባማኮ ገዢዎች አበክረዉ ይጎተጉቱ ገቡ።
የማሊ ወታደራዊ ገዢዎች እንደሚሉት «ሰማያዊ መለዮ ለባሽ» እየተባለ የሚንቆለጳጳሰዉ ዓለም አቀፍ ሠራዊት ባልደረቦች በየከተማ-ጦር ሠፈሩ ከመርመስመስ ባለፍ ሠራዊቱ ለማሊ ሠላም የፈየደዉ የለም።የሠራዊቱ አዛዦች ግን ተቃራኒዉን ነዉ የሚሉት።ዓለም አቀፉ ሠራዊት ከማሊ ወታደራዊ ገዢዎች ትብብር አላገኘም እንዲያዉም በተቃራኒዉ የባማኮ ገዢዎች የሰራዊቱን ተልዕኮ እስከ ማደናቀፍ ይደርሳሉ ባዮች ናቸዉ።
የማሊ ወታደራዊ ገዢዎች መረጃና ማስረጃ እየደረደሩ ከፈረንሳይ፣ በፈረንሳይ በኩል ከምዕራባዉያንና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር የገጠሙት እሰጥ አገባ ከመቀጠል ይልቅ ሁሉንም እርግፍ አድርገዉ ትተዉ ፊታቸዉን ወደ ሩሲያ ማዞሩን እንደ ጥሩ ስልት የያዙት ይመስላሉ።
ዉዝግቡን በቅርብ እርቀት ስትከታተል የነበረችዉ ሩሲያም በቀጥታና በቫግነር ወታደራዊ ኩባንያ በኩል ምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሐገር ዘዉ ብላ ገባች።የቫግነር ቅጥረኛ ወታደሮችና ወታደራዊ አሰልጣኞች የትንሺቱን ምዕራብ አፍሪቃዊት ሐገር ፀጥታ ማስከበር፣ወታደሮቿን ማሰልጠንና ማማከር ይዘዋል።የማሊ ወታደራዊ መሪዎች «የሐገራችንን ፀጥታና ደሕንነት ማስከበር ያለብን ራሳችን ነን» ይላሉ።
የሳሕል ጉዳይ የፖለቲካ ተንታኝ አብዱላዬ ሶናዬ የባማኮዎች ዉሳኔ ልክ ነዉ ዓይነት ይላሉ።ግን ደግሞ ጣጣም አያጣም።
«ፀጥታን በተመለከተ የማሊ መንግስት የሐገሩን ሉዓላዊነት ለማስከበር መወሰኑ ትክክል ነዉ።ማሊ ነፃ ሐገር በመሆንዋ ይሕን ርምጃ መዉሰዷን ማንም ሊቃወም አይገባም።በሌላ በኩል ግን ማሊ የአብዛኛ ግዟቷን በተለይም በሐገሪቱ ሰሜናዊ ግዛት የሚኖር ዜጋዋን ደሕንነት ማስጠበቁ ይከብዳታል።የማሊ መንግስት በሩሲያዉ የቫግነር ቡድን ድጋፍ እንኳን ይሕን አካባቢ መቆጣጠር አልቻለም።»
የምዕራብ ሐገራት ታዛቢዎች እንደሚሉት ዓለም አቀፉ ሠራዊት ለቅቆ ሲወጣ ሰሜናዊ ማሊ ዉስጥ የሸመቁ አማፂያንና የአሸባሪ ቡድን አባላት አካባቢዉን ሙሉ በሙሉ ሊቆጣጠሩት፣ ከማሊ አልፎ የሳሕል አካባቢ ሐገራትንም ሊያተርምሱት ይችላሉ።
የማሊ ዝርያ ያላቸዉ ፈረንሳዊቷ የፖለቲካ አዋቂ ኒያጋሌ ባጋዮኮ እንደሚሉት ደግሞ ማሊን ከምዕራባዉያን ጋር ያላተመዉ የባማኮ-ፓሪሶች ጠብ ነዉ።መዘዙ ወዲፊት አፍሪቃዊቱን ሐገር ከግጭትና ጦርነት አዙሪት መዶሉ አይቀርም-እንደ ባጋዮኮ።
«የማሊ ወታደራዊ ገዢዎች ከዚሕ ዉሳኔ ላይ እንዲደርሱ ያደረጋቸዉ የማሊና የፈረንሳይ ግንኙነት መበላሸት ነዉ።ማሊዎች ራሳቸዉን ቀድሞ ቅኝ ገዢያቸዉ ፈረንሳይ ተፅዕኖ ማላቀቅ ይሻሉ።የፈረንሳይና የMINUSMA ጦር ከማሊ መዉጣት አፍሪቃ ዉስጥ የሚደረጉ ግጭትና ጦርነቶችን እስካሁን በተለመደዉ መንገድ ማስቆም ከባድ መሆንኑን አመልካች ነዉ።ቀዉሱ የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮችን በመኮናተርም ሊፈታ አይችልም።»
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሠራዊት ከማሊ ለቅቆ እንዲወጣ የመወሰኑ ዜና ከሐገሪቱ ዜጎች ደስታም፣ቅሬታም አስከትሏል።እሳቸዉ የሰራዊቱ መዉጣት ጥሩ ነዉ ይላሉ።
«ዓለም አቀፍ ሰራዊት ሰፍሮም ጂሐዲስቶች በሐገሪቱ ማዕከላዊና ሰሜናዊ ግዛቶች የሚያደርሱት ጥቃት አልቆመም።በየጊዜዉ ጥቃት፤ ግድያና ጉዳት እየደረሰ ነዉ።ሰማያዊ መለዮ ለባሾቹ ሐገሪቱን ለቅቀዉ እንዲወጡ መወሰኑ ጥሩ ነዉ።
ይኸኛዉ ያሳሰበዉ ሠራዊቱ ያቀዳቸዉ የርዳታ ፕሮጀክቶች ጉዳይ ነዉ።
«MINUSMA ማዕከላዊና ሰሜናዊ ማሊ ዉስጥ ያቀዳቸዉ የርዳታ ፕሮጄክቶች እንዴት ይሆናሉ።ዓለም አቀፉ ሠራዊት ሲወጣ እዚያ ያሉ ሰዎች እንዴት ይሆናሉ?»
ላሁኑ ያለዉ መልስ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት መወሰኑ ነዉ።በዉሳኔዉ መሠረት ከ2013 ጀምሮ ማሊ የሰፈረዉ 13 ሺሕ የፖሊስና የጦር ሠራዊት አባላት እስከ ታሕሳስ 31፣ 2023 ድረስ ሙሉ በሙሉ ከማሊ ነቅለዉ ይወጣሉ።ሠራዊቱ የሠፈረዉ 2013 ነዉ።ብዛቱ 13 ሺሕ ነዉ።ለቅቆ እንዲወጣ የተወሰነዉ ሰኔ 30፣2023 ነዉ።ተጠቃልሎ የሚነቅለዉ ታሕሳስ 31፣ 2023 ነዉ።3 በዛበትሳ?
የሳሕል ትብብርና ጀርመን
የጀርመንዋ የልማት ተራድኦ ሚንስትር ስፌንያ ሹልስ የፊታችን ሰኞ ወደ ንዋክሾት-ሞሪታንያ የሚያደርጉት ጉዞ ቃልና ተስፋን የቀየጠ ነዉ።ሚንስትሯ ሞሪታንያዋ ርዕሰ ከተማ በሚደረገዉ የሳሕል-ትብብር ጉባኤ ላይ የትብብሩ ፕሬዝደንት ሆነዉ ይመረጣሉ።ለፕሬዝደንትነቱ ሌላ ተፎካካሪ ስላልቀረበ ምርጫ ከመባል ይልቅ ሹመት ቢባል ይቀላል።
ለነገሩ ስልጣኑም የሳሕል አካባቢ ሐገራትን ሚረዱና የተረጂ መሪዎችን ከማስተባበር በላይ ብዙም ፋይዳ የለዉም።የሳሕል-ትብብር የተባለዉ ስብስብ G5 ተብለዉ የሚጠሩትን የሳሕል አካባቢ ሐገራትን ሞሪታንያ፣ማሊ፣ቡርኪና ፋሶ፣ ኒዠር፣ ቻድንና ምዕራባዉያን ርዳታ ሰጪዎቻቸዉን የሚያስተናብር ዓለም አቀፍ ስብስብ ነዉ።
እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር በ2017 ጀርመን፣ ፈረንሳይና የአዉሮጳ ሕብረት መሠረቱት።ዘንድሮ ረጂዎቹ 18 ደርሰዋል።ብዙ ታዛቢዎችም አሉት።«ወይዘሮ ሹልስ ወደ ንዋክሾት-ለመጓዝ ሲዘጋጁ ትናንት «የሳሕል ትብብር በጣም አስፈላጊ ለጋሾችን በአባልነት ያቀፈ ነዉ።» አሉ።
«ይሕ ትብብር የልማት አጋሮችን በሙሉ ያቀፈ ነዉ።ለአካባቢዉ ከፍተኛ ድጋፍ የሚሰጥ ትብብር ነዉ።ተባብረን ሁነኛ ለዉጥ ለማምጣት እንሻለን፣ እንችላለንም።»
ስብስቡ አምና 1 400 የልማት ፕሮጄክቶችን ለአስምቱ ሐገራት ለመስራት አቅዷል።ለዕቅዱ ማስፈፀሚያ 29 ቢሊዮን ዩሮ ያስፈልጋል። አምስቱ ሐገራት የሚገኙበት አካባቢ በጣም ከደኸዩ አካባቢዎች አንዱ፣ ሞቃት፣ በዉሐ እጥረት፣በድርቅና ረሐብ የሚጠቃ አካባቢ ነዉ።«ግጭትም የበዛበት አካባቢ ነዉ» ይላሉ ሹልስ።
«በተጨማሪ ሳሕል የእስላማዊ አሸባሪዎች ዋና ማዕከል እየሆነ ነዉ።ሩሲያ ባካባቢዉ ላይ የምታሳድረዉ ተፅዕኖም እየተጠናከረ ነዉ።ይሕ ለአካባቢዉ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለተቀረዉም አካባቢ ትልቅ አደጋ ነዉ።»
የዓለም ምግብ ድርጅት እንዳስታወቀዉ ባለፈዉ ዓመት ጀርመን ለሳሕል አካባቢ ሐገራት 1.7 ቢሊዮን ዮሮ ረድታለች።ብዙ ርዳታ በመስጠት ጀርመን ከዩናይትድ ስቴትስ ቀጥላ ሁለተኛዋ ሐገር ናት።
ይሁንና ለጀርመን የልማት ተራድኦና ለዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ለመጪዉ ዓመት በጀት የተመደበዉ ገንዘብ ከዘንድሮዉ ያነሰ በመሆኑ ጀርመን ለሳሕል አካባቢ ሐገራት የምትሰጠዉ ርዳታ ይቀንሳል የሚል ስጋት አሳድሯል።
የጀርመን መንግስት በጀቱን መቀነሱን የጀርመኑ የሕፃናት አድን ድርጅት፣የጀርመን ርዳታ ለዓለም ሕዝብ፣የዓለም ረሐብተኞች መርጃ ድርጅትኦክስፋምና ሌሎች ግብረ-ሠናይ ድርጅቶች በጋራ ባወጡት መግለጫ ተቃዉመዉታል።ተቃዉሟቸዉ እስካሁን በተመደበዉ በጀት ላይ ያመጣዉ ለዉጥ የለም።የልማት ተራድኦ ሚንስትሯም እንዴት የሚለዉን ጥያቄ ባይመልስም ርዳታዉ ይቀጥላል የሚል ተስፋ አላቸዉ።በቅርቡ የሚይዙት የፕሬዝደንትነት ሥልጣንም መንግስታቸዉ የሳሕል አካባቢን ለመርዳት ያለዉን ቁርጠኝነት መስካሪ ነዉ ባይ ናቸዉ።
«የሳሕል-ትብብርን የፕሬዝደንትነት ሥልጣን የምይዘዉ ጀርመንና ተባባሪዎችዋ አካባቢዉን ለመርዳት ዝግጁ መሆናቸዉንና ምግባራቸዉን እንደማያቋርጡ ለማሳየት ነዉ።በሳሕል አካባቢ የሚደረግ አወንታዊ ለዉጥ የበለጠ መረጋጋትና ለተሻለ ኑሩ መሰረት የሚጥል ነዉ።ይሕ ደግሞ ለብዙ ያካባቢዉ ሕዝብ አስፈላጊ ነዉ።»
የሳሕል-ትብብር ባቀደዉ መሰረት ለአምስቱ ሐገራት ሕዝብ የዉሐ ቧምቧዎች፣ ትምሕርት ቤቶች፣ ሐኪም ቤቶች የመሳሰሉ የመሠረተ ልማት አዉታሮች ይገነባሉ።ወጣቶችና ሴቶች ሥራ እንዲያገኙ በተለያዩ ሙያ ይሰለጥናሉ።በረሐማዉ አካባቢ ወርቅ፣የከበሩ ድንጋዮች ምናልባትም ነዳጅ እንዳለበት ቢታመንም እስካሁን ለአገልግሎት አልዋለም።
ነጋሽ መሐመድ
ኂሩት መለሰ