1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቤት እንስሳቱ የረገፉበትን አርብቶ አደር ማን ይታደገዋል?

ረቡዕ፣ የካቲት 9 2014

በአፍሪካ ቀንድ የበረታው ድርቅ ለሐመር አርብቶ አደር የኅልውና ጥያቄ ጋርጦበታል። የውኃ እና የግጦሽ ሣር እጦት "ዕለት በዕለት የአርብቶ አደሩ መተዳደሪያ የሆኑ የቁም እንስሳትን በከፍተኛ ሁኔታ እየጨረሰ" መሆኑን የሐመር ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሐማ አይኬ ተናግረዋል። በሐመር 33 ቀበሌዎች የከፋው ድርቅ ከ55 ሺሕ በላይ ነዋሪ ለረሐብ አጋልጧል

https://p.dw.com/p/477iJ
Äthiopien | Folgen von Dürre - Totes Vieh
ምስል Hamar Woreda Government Communication Affairs Office

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ የቤት እንስሳቱ የረገፉበትን አርብቶ አደር ማን ይታደገዋል?

በሐመር እንደ ሶማሌ እና እንደ ቦረና ሁሉ ለአርብቶ አደሮች ጊዜው ከፍቷል። በደቡብ ኦሞ ሸለቆ በሚገኙ ጥሻዎች የቀንድ ከብቶቹ ላይመለሱ ከንበል እያሉ ነው። ሰውነታቸው ፈርሶ አጥንታቸው ገጦ የወዳደቁ እንስሳት በድን እዚህም እዚያም ይታያል። ሞታቸው ትኩስ ለመሆኑ ሳይበሰብስ ተቦጫጭቆ በአጥንታቸው ላይ የቀረ ቆዳቸው ይመሰክራል።

የሐመር ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሐማ አይኬ "አሁን በሐመር ድርቁ ዕለት በዕለት የአርብቶ አደሩ መተዳደሪያ የሆኑ የቁም እንስሳትን በከፍተኛ ሁኔታ እየጨረሰ ነው። ውኃ የለም፤ ሣር የለም። አርብቶ አደሩ የእንስሳት ተዋጽዖ በመመገብ ነው የሚኖረው። ዝናብ የለም በዚህ ምክንያት ብዙ ከብቶች እየሞቱ ነው። ሰውም በጣም በከፍተኛ ሁኔታ በረሐብ እየተሰቃየ ነው" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

አቶ ሐማ አይኬ እንደተናገሩት ድርቅ የከፋው፣ የአርብቶ አደሩ እንስሳትም ሞት የበረታው በተለይ በወረዳው በሚገኙ 33 ቀበሌዎች ውስጥ ነው። ዶይቼ ቬለ የወረዳው ባለሙያዎች ድርቅ ወደ ተከሰተባቸው ቦታዎች አቅንተው ያነሷቸውን የሞቱ የቤት እንስሳት የሚያሳዩ በርካታ ፎቶግራፎች ተመልክቷል። ምስሎቹ የድርቁን ክፋት ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው። በሕይወት የቀሩት የቤት እንስሳትም ቢሆኑ ሰውነታቸው አልቆ አጥንታቸው ቆዳቸውን እየገፋ ነው። በየጥሻው የቀሩ የቤት እንስሳት የሐመር አርብቶ አደር የኑሮ መሠረት ነበሩ። ውኃ የጠማቸው፣ መኖ የቸገራቸው የቀንድ ከብቶች በኦሞ ሸለቆ ለሚኖረው አርብቶ አደር ብቸኛ ጥሪት ናቸው። የሐመር ወረዳ የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አወቀ ንጋቱ ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ድርቅ የጨከነባቸውን አካባቢዎች ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

Äthiopien | Folgen von Dürre - Totes Vieh
የሐመር ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሐማ አይኬ "አሁን በሐመር ድርቁ ዕለት በዕለት የአርብቶ አደሩ መተዳደሪያ የሆኑ የቁም እንስሳትን በከፍተኛ ሁኔታ እየጨረሰ ነው" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።ምስል Hamar Woreda Government Communication Affairs Office

"በርካታ እንስሳቶች ሞተዋል። ይኸንንም ሔደን በደንብ አረጋግጠን ተመልሰናል። ህብረተሰቡ አምርቶ የሚበላው ነገር የለም" የሚሉት አቶ አወቀ ንጋቱ በቱርሚ ክላስተር ሥር በሚገኙት ሚርሻ ኩለማ፣ ሚኖ ገልቲ፣ አስቺሌ፣ ወንጋ ባይኖ፣ ገምበላ፣ ዘለከታ እና ኤጉዴ የተባሉ ቀበሌዎች በተለይ ድርቅ እንደጠናባቸው አስረድተዋል። "ለዚህ አርብቶ አደር የኅልውና መሠረቱ እንስሳቱ ነበሩ። እነዚህን እንስሳት ሲያጣ ይራባል። በወረዳችን በተሰራ ዳሰሳ ከ55 ሺሕ በላይ የሐመር ወረዳ ነዋሪ በዚህ ድርቅ ለረሐብ ይጋለጣል የሚል እምነት አለን" ሲሉ የሐመር ወረዳ የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አወቀ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ደቡብ ኦሞ ወረዳ በሚገኘው የሐመር ወረዳ የተከሰተው፤ የአፍሪካ ቀንድ አገራት ላይ የበረታ ድርቅ አካል ነው። የዓለም የምግብ መርሐ-ግብር እንዳለው ይኸን ብርቱ ድርቅ ያስከተለው ደረቅ የአየር ጠባይ ባለፉት 40 ገደማ አመታት ከታየው ሁሉ የከፋ ነው። በዚህ ደረቃማ የአየር ጠባይ ምክንያት በኢትዮጵያ፣ በኬንያ እና በሶማሊያ ሶስት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች ከሽፈዋል።

በሐመር አካባቢ "በመስከረም፣ ጥቅምት እና እስከ ህዳር አጋማሽ ድረስ ዝናብ ይጥል ነበር። ያ ዝናብ ባለመጣሉ ነው ይኸ [ድርቅ] በከፍተኛ ኹኔታ የተፈጠረው" የሚሉት የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ሐማ "ዝናብ በሚጥልበት ጊዜ አርብቶ አደሩ ኩሬዎች እና ወራጅ ውኃዎችን ነው የሚጠቀመው። እነዚያ ሙሉ በሙሉ ደርቀዋል፤ ጠፍተዋል" ሲሉ ተናግረዋል። "አማራጭ ያለው የኦሞ ወንዝ ነው። በኦሞ ወንዝ [ከብቶችን ውኃ] ለማጠጣት ያለው ነገር በጣም አዳጋች ነው። ርቀቱ አለ። ከብቶች እስከዚያ ድረስ ተንቀሳቅሰው መሔድ አይችሉም። ውኃ ማግኘት ቢችሉ እንኳን ሣር የለም። ውኃ መጠጣታቸው ብቻ ሕይወታቸውን አያቆይም። ሣር እና መኖ አለመኖሩ ትልቅ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው። በየትኛውም አማራጭ ውኃ ማግኘት ወደማይቻልበት ሁኔታ ነው የተደረሰው" ሲሉ የችግሩን ብርታት አቶ ሐማ ለዶይቼ ቬለ አብራርተዋል።

"የመኖር እና አለመኖር ጥያቄ" የተጋረጠበት የኢትዮጵያ አርብቶ አደር

ይኸ ፈተና በሐመር ብቻ የተወሰነ አይደለም። በውኃ ጥም እና በመኖ እጦት የደከሙ ከብቶቻቸውን በአራት እግሮቻቸው ለማቆም የሚታገሉ አርብቶ አደሮች በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጭምር ታይተዋል።

Äthiopien | Folgen von Dürre - Totes Vieh
የሐመር ወረዳ አስተዳዳሪ አርብቶ አደሮች ከዚህ ቀደም በመደበኛነት ለምግብነት የማይውሉ ፍራፍሬዎች እና ቅጠላ ቅጠሎችን ለመብላት መገደዳቸውን ተናግረዋል።ምስል Hamar Woreda Government Communication Affairs Office

ድርቅ በተጫነው የሶማሌ ክልል ነዋሪ የሆኑ አቶ መሐመድ አደም የተባሉ አርብቶ አደር በአካባቢያቸው ሁለት የዝናብ ወቅቶች መክሸፋቸውን ተናግረዋል። "ይኸ ከዚህ በፊት ገጥሞን አያውቅም" የሚሉት አቶ መሐመድ በቀያቸው የሚያዩት "የአቧራ ማዕበል ብቻ ነው።" አቶ መሐመድ ይኸው የአቧራ ማዕበል ሸፍኖ መቃብራቸው እንዳይሆን ያሰጋቸዋል። በቀብሪ ድኻር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር አብዱሰላም አብዱላሒ "በሶማሌ ክልል ከ70 እስከ 75 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ አርብቶ አደር ነው።  ይኸ ማህበረሰብ ደግሞ ለድርቅ በጣም ተጋላጭ ነው። በሶማሌ ክልል አስራ አንድ ዞኖች አሉ። ከአስራ አንዱ ዞኖች የመንግሥት ሪፖርት እንደሚያሳየው ዘጠኝ ዞኖች በዚህ ድርቅ ተጎድተዋል" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

"በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ እንስሳቶች፤ ከብት፣ ፍየል እና ግመሎች በዚህ ድርቅ ሞተዋል። የአርብቶ አደር ሕዝብ ኑሮ ሙሉ በሙሉ የሚንጠለጠለው እንስሳት ላይ ነው። ይኸ የእንስሳት ሞት ሲከሰት የመኖር እና አለመኖር ጥያቄ ውስጥ ነው የሚገቡት" በማለት የአፍሪካ ቀንድ ላይ የበረታው ድርቅ የአርብቶ አደሩን ኅልውና እስከ መፈታተን እንደሚደርስ ያስረዳሉ።

ይኸን የኅልውና ጥያቄ አቶ ሐማ በሐመር አርብቶ አደሮች ዘንድ ፊት ለፊት ተጋፍጠውታል። "የአርብቶ አደር ልጅ እንደመሆናችን የተሰማንን ነገር ይኸ ነው ብሎ ለመናገር ይከብዳል" የሚሉት አቶ ሐማ "የአንድ ሰው 20 ከብት፤ 40 ከብት፤ እስከ መቶ የሚጠጋ ፍየል በአንድ መንደር ውስጥ [ሞቶ] ይታያል። አርብቶ አደሩ ያለቅሳል። የሚሆነውን ነገር ያጣል። በዚህ ሁኔታ ´ራሴን አጠፋለሁ` የሚሉም አሉ" ብለዋል። "ሰው ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ነው። የከፋ ባይሆንም ሞት ይታያል" የሚሉት የሐመር ወረዳ አስተዳዳሪ አርብቶ አደሮች ከዚህ ቀደም በመደበኛነት ለምግብነት የማይውሉ ፍራፍሬዎች እና ቅጠላ ቅጠሎችን ለመብላት መገደዳቸውን ተናግረዋል። "የሞቱትን እንስሳት ለመብላት ከመክሳታቸው የተነሳ ብዙም አይገፋፋም። አሁን በጫካ እየዞሩ የእንጨት ፍሬ፣ ቅጠላ ቅጠሎችን እየለቀሙ የሚመገቡት" ብለዋል።

ደግሞ ደጋግሞ ብቅ የሚለው ድርቅ

ለእንዲህ አይነት ድርቅ ኢትዮጵያም ሆነች የምሥራቅ አፍሪካ አገራት እንግዳ አይደሉም። በተለይ የከባቢ አየር ለውጥ ያስከተላቸው ተደጋጋሚ ድርቆች ባለፉት አመት በኢትዮጵያ፣ በሶማሊያ እና በኬንያ ብርቱ ጉዳት አድርሰዋል። ረዳት ፕሮፌሰር አብዱሰላም አብዱላሒ በአስር አመታት አንዴ ብቅ ይል የነበረው ድርቅ የሚከሰትበት የጊዜ ልዩነት እየጠበበ መምጣቱን ጥናታዊ ጽሁፎች እያጣቀሱ ይዘረዝራሉ።

በአስር አመት አንዴ ይከሰት የነበረው ድርቅ በስድስት አመታት መከሰት ጀምሮ እንደነበር የጠቀሱት ረዳት ፕሮፌሰር አብዱሰላም "ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ2010 እና በ2011 የተከሰተ ድርቅ አለ። ያን ተከትሎ ደግሞ በ2015 በጣም የከፋ የኤልኒኞ ድርቅ ተከስቷል። ከ2011 እስከ 2015 ባሉት አራት አመታት ሁለት ጊዜ ነው ድርቅ የተከሰተው። በቀጣይ ደግሞ በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ2016 እና በ2017 የተከሰተ ድርቅ አለ። ቀጥሎ ደግሞ የአሁኑ ነው። ይኸም ማለት በጥናታዊ ውጤቶች መሠረት በየሶስቱ አመት ድርቅ ይመጣል ተብሎ ይታሰባል" ሲሉ ለውጡን ያስረዳሉ። ድርቅ የሚከሰትበት የጊዜ ልዩነት እየጠበበ ሲሔድ "በመንግሥት ደረጃም ሊሆን ይችላል በማህበረሰብ ደረጃም" በቂ ዝግጅት እየተደረገ እንዳልሆነ አብዱሰላም ይተቻሉ። "እነዚህ ጥናቶች ይኸንን ሲያሳዩ በቂ ዝግጅት አለመደረጉ አንዱ ትልቅ ክፍተት ነው። ከተከሰተ በኋላ ደግሞ ሙሉ በሙሉ መልስ መስጠት አይቻልም። ምክንያቱም ተፈጥሯዊ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

Äthiopien | Folgen von Dürre - Totes Vieh
በሐመር አካባቢ በመስከረም፣ ጥቅምት እና እስከ ህዳር አጋማሽ ድረስ መጣል የነበረበት ዝናብ በመክሸፉ የተከሰተው ድርቅ ብዛት ያላቸው የቤት እንስሳትን ለሞት ዳርጓል። ምስል Hamar Woreda Government Communication Affairs Office

በኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ኬንያ በዚሁ ድርቅ ሳቢያ 13 ሚሊዮን ሰዎች መራባቸውን የዓለም የምግብ መርሐ-ግብር (WFP) ባለፈው ሣምንት አስታውቋል። የድርጅቱ ቃል አቀባይቶምሰን ፊሪ "ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ምርት ከመደበኛው እስከ 70 በመቶ" መቀነሱን ተናግረዋል። "የምግብ እና የውኃ ዋጋ እጅግ እያሻቀበ ነው" ያሉት ቃል አቀባዩ ይኸ "የቤተሰቦችን የመሸመት አቅም እየተፈታተነ" እንደሚገኝ ባለፈው ሣምንት በጄኔቫ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል። "በተለያዩ ገበያዎች የምግብ እህል ዋጋ ከመደበኛው ከሶስት እስከ አምስት በመቶ ሲጨምር" የቁም እንስሳት ዋጋ እየረከሰ ንግድ መዳከሙ ቶምሰን ፊሪ የጠቀሱት ሌላ ፈተና ነው።

በሐመር ወረዳ ድርቅ ከተከሰተ በኋላ በተደጋጋሚ ሪፖርት እና ጥያቄ ለሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት መቅረቡን የሚያስረዱት አቶ ሐማ አይኬ አርብቶ አደሩንም ሆነ እንስሳቱን "የሚታደግ እርዳታ አልደረሰንም" ብለዋል። የሐመር አርብቶ አደር "ቀሪዎቹ እንስሳት ተርፈውልን እኛም ከእነሱ የሆነ ነገር እያገኘን ራሳችንን የምናተርፍበት ሁኔታ ቢፈጠር የሚል ጥያቄ ነው የሚያቀርቡት። አሁን ሣር የለም፤ ግጦሽ ማግኘት አይችሉም። ይኸንን መነሻ አድርገው መኖ  የሚቀርብበት መንገድ እዲመቻችላቸው፤ ውኃ እንዲደርስላቸው፤ እንስሳት ቢሞቱ እንኳን የሰው ልጅ ውኃ የሚያገኝበት ሁኔታ ቢመቻች የሚል ነው በሰፊው የሚጠይቁት" ሲሉ አቶ ሐማ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።  

Äthiopien | Folgen von Dürre - Totes Vieh
በሕይወት የሚገኙት የሐመር አርብቶ አደር የቤት እንስሳትም ቢሆኑ ሰውነታቸው አልቆ አጥንታቸው ቆዳቸውን እየገፋ ነው። ምስል Hamar Woreda Government Communication Affairs Office

በኢትዮጵያ ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የፌድራል መንግሥት ከክልል መስተዳድሮች ጋር በመተባበር ዕገዛ ለማቅረብ የሚያደርጋቸው ጥረቶች እንዳሉ ይታያል። በቀብሪ ድኻር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር አብዱሰላም አብዱላሒ ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች "የሰው ሕይወትን ማዳን" ቀዳሚው ሥራ እንደሆነ ያሳስባሉ።

"ማህበረሰቡ ሐብቱን አጥቷል። ያ ሐብት ለወደፊት የሚመለስበት መንገድ ስትራቴጂክ የሆነ መፍትሔ ይፈልጋል። አሁን ግን ሕይወት የማዳን ሥራ መሰራት አለበት። የእኛ አገር አሁን በብዙ ፈተና ነው እየተፈተነች ያለችው። ይኸ ድርቅ ብቻ አይደለም። የሰላም እጦት አለ። በየቦታው የሚፈጠሩ ችግሮች አሉ። እነዚህ ችግሮች እያሉ ይኸ እንደ አንድ ችግር ታይቶ ከፌድራል እስከ ክልል መንግሥት እስከ ታች ድረስ ትኩረት ተሰጥቶት መሠራት አለበት" ሲሉ ረዳት ፕሮፌሰር አብዱሰላም አብዱላሒ ተናግረዋል።

ድርቅ በየሁለት አመቱ ሊከሰት እንደሚችል የሚያስጠነቅቁ ጥናቶች መኖራቸውን የጠቆሙት አብዱሰላም "በፖሊሲ ደረጃ" ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። የጥናት ውጤቶችን "ወደ ፖሊሲ አምጥተን ድርቅ ሳይከሰት በፊት ቅድመ-ዝግጅት ማድረግ አለብን። ጥናቶቹ የሚያሳዩትን ነገሮች ወደ ሥራ ማስገባት አለብን" በማለት ረዳት ፕሮፌሰር አብዱሰላም ኢትዮጵያ ብርቱ ሥራ እንደሚጠብቃት ገልጸዋል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሰ