የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል አዛዥ መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ በኢጋድ ጉባኤ መጋበዛቸውን ገለጹ
ቅዳሜ፣ ጥር 4 2016የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል አዛዥ መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ በመጪው ሐሙስ በዩጋንዳ በሚካሔደው የምሥራቅ አፍሪካ በይነ-መንግሥታት አስቸኳይ የመሪዎች ጉባኤ እንዲሳተፉ መጋበዛቸውን አስታወቁ።
የኢጋድ አስቸኳይ ጉባኤ ከሚመክርባቸው አጀንዳዎች መካከል ለዘጠኝ ወራት ብርቱ ውጊያ የተደረገባት የሱዳን ጉዳይ ይገኝበታል። በኢጋድ የወቅቱ ሊቀ-መንበር የጅቡቲው ፕሬዝደንት ኢስማኤል ዑመር ጉሌሕ የተጠራው አስቸኳይ ጉባኤ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ውዝግብ ላይ ጭምር ይመክራል።
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል አዛዥ የሆኑት መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ በጉባኤው እንዲሳተፉ በኢጋድ ጽህፈት ቤት መጋበዛቸውን በቀድሞው ትዊተር በአሁኑ ኤክስ በኩል አስታውቀዋል። ዳጋሎ “በስብሰባው ላይ እንድገኝ እና እንድሳተፍ የቀረበልኝን ግብዣ መቀበሌን አረጋግጫለሁ” ብለዋል።
ኢጋድ ከዚህ ቀደም የሱዳን ጦር አዛዥ አብደል ፋታኅ አል-ቡርኻን እና መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎን ፊት ለፊት ለማገናኘት ጥረት በማድረግ ላይ እንደሆነ አስታውቆ ነበር።
በኢጋድ አስቸኳይ ጉባኤ አብደል ፋታኅ አል-ቡርኻን ከታደሙ ሁለቱ ተቀናቃኞች በሱዳን ውጊያ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ፊት ለፊት ሲገናኙ የመጀመሪያቸው ይሆናል። ዳጋሎ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ ከሁለት ሣምንታት በፊት ስድስት የአፍሪካ ሀገሮችን ሲጎበኙ የተደረገላቸውን አቀባበል አብደል ፋታኅ አል-ቡርኻን ተቃውመዋል።
ኢጋድ እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አል-ቡርኻን እና ዳጋሎን ለማደራደር ግፊት በሚያደርግበት ወቅት የሱዳን ውጊያ እንደቀጠለ ነው። ባለፈው ሐሙስ የአየር ድብደባን ጨምሮ በኻርቱም ተቀናቃኝ ኃይሎች ባደረጉት ውጊያ በትንሹ 33 ሰዎች መገደላቸውን በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውን በሱዳን ዴሞክራሲያዊ መንግሥት እንዲቋቋም ግፊት የሚያደርገው የጠበቆች ቡድን አስታውቋል።
በሱዳን ጦርነት በወግ አጥባቂ ግምት 12 ሺሕ 190 ሰዎች ተገድለዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከሰባት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን አስታውቋል።
እሸቴ በቀለ
ታምራት ዲንሳ