የሰዎች ተገደው መሰወር እና የኢትዮጵያ ስብአዊ መብት ኮሚሽን ጥሪ
ረቡዕ፣ ግንቦት 30 2015የኢትዮጵያ ስብአዊ መብት ኮሚሽን ከቅርብ ግዜ ወዲህ እየተባባሰ የመጣ ነው ባለው እና በመንግስት የጸጥታ ኃይላት የሚፈጸም ሰዎችን አስገድዶ የመሰወር ተግባር በአስቸኳይ እንዲቆም ጠየቀ ። ኮሚሽኑ ከትናት በስትያ ሰኞ ባወጣው መግለጫ በተለይ ከአዲስ አበባ ከኦሮሚያ እና ከአማራ ክልል በደረሱት በርካታ አቤቱታዎች እና ጥቆማዎች በመነሳት ሲያደርግ በነበረው ክትትል መሠረት በርካታ የአስገድዶ መሰወርን ድርጊቶች መከሰታቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል ። የኮሚሽኑ የክትትል እና ምርመራ ክፍልም ተጨማሪ ምርመራዎችን እያደረኩ ነው ብሏል።
በተመሳሳይ «መንግሥት ሰብዓዊ መብቶችን የማክበር እና የማስከበር ሃላፊነቱን በአግባቡ ይወጣ ” ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ኢሰመጉ ባወጣው መግለጫ አሳስቧል ።
የኢትዮጵያ መንግስት ወንጀሉን በሚገባ ለመከላከል ሁሉንም ሰዎች ከአስገድዶ መሰወር ለመጠበቅ የተደረገውን ዓለም አቀፍ ስምምነት ኢትዮጵያ በአስቸኳይ ተቀብላ እንድታጸድቅም ኮሚሽኑ ጠይቋል ።
በምዕራብ ወለጋ ዞን ግንቦት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. በወረዳው ፖሊስ ከሌሎች ሦስት ጓደኞቹ ጋር ተይዞ ፖሊስ ጣቢያ ከገባ በኋላ ሰኔ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ቀን ጀምሮ ያለበት ቦታ እና ሁኔታ ማወቅ አልተቻለም።
በተመሳሳይ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የምሥራቅ ወለጋ ዞን የኦፌኮ አስተባባሪ የሆኑ ግለሰብ ጥቅምት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ከቀኑ 10 00 ሰዓት በመንግሥት የደኅንነት ኃይሎች ተይዘው መታሰራቸውን እና ከሰኔ 13 2015 ቀን ጀምሮ ግለሰቡ የት እና በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ ማወቅ አለመቻሉ ተገልጿል።
የቀድሞ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባል ታህሳስ 6ቀን 2015 ከቀኑ 11 ሰአት ከሚሰሩበት ቦታ ለስራ ትፈልጋለህ በሚል ተጠርተው ከሄዱበት ግዜ ጀምሮ እስከ አሁን የት እና በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ ማወቅ አልተቻልም።
በኦሮሚያ ልዩ ኃይል ፖሊሶች ከቡራዩ " አሸዋ ሜዳ "መኖሪያ ቤታቸው ተይዘው በቡራዩ ወረዳ 3 ፖሊስ ጣቢያ በቁጥጥር ስር ውለው የቆዩ አንድ ሰው ከሁለት ወራት የፖሊስ ጣቢያ ቆይታ በኋላ ከሌሎች እስረኞች ተለይተው መወሰዳቸውን እና ከዚያን ቀን ጀምሮ ያሉበትን ቦታም ሆነ ሁኔታ ማወቅ አልተቻለም እያለ በመረጃ እና በማስረጃ በመንግስት አካላት በግዳጅ የሚሰወሩ ዜጎችን የዘረዘረው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮምሺን ሰዎችን አስገድዶ የመሰወር ድርጊት በአገሪቱ ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷዋል ይህም በአፋጣኝ እንዲቆም ሲል ጠይቋል።
ዶ/ር ሚዛኔ አባተ የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ስራ ክፍል ባልደረባ ችግሩ እየተብባሰ ሲመጣ የወንጀሉን አስከፊነት ለማሳያ ጥቂቱን በሪፖርታቸው ማሳየታቸውን ለ DW ተናግረዋል። ዶክተር ሚዛኔ አክለው በአስገድዶ መሰወሩ ወቅት ተፈጽሟል ስለተባለ ተገቢ ያልሆነ አያያዝ እና የማሰቃየት ተግባር ኮሚሽኑ ተጨማሪ ምርመራ እያደረገ መሆኑንም አስረድተዋል ።
ሃና ደምሴ
ታምራት ዲንሳ
ነጋሽ መሐመድ