1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰኔ 19 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሰኔ 19 2015

የኢትዮጵያ ብስክሌት ሻምፒዮና ትግራይ ክልል ውስጥ እሁድ ሰኔ 18 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ተጠናቋል ። ኤርትራ አስመራ ከተማ ውስጥም የኤርትራ ብሔራዊ የጎዳና ላይ የብስክሌት የፍጻሜ ፉክክር ትናንት ተከናውኗል ። ልዩ የኦሎምፒክ ጨዋታዎች በትናንትናው ዕለት ጀርመን ቤርሊን ከተማ ውስጥ ተፈጽሟል ። ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ውድድሮችንም ቃኝተናል ።

https://p.dw.com/p/4T5iQ
Fussball Frauen Testspiel, Deutschland - Vietnam
ምስል Mirko Kappes/foto2press/IMAGO

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በኢትዮጵያ ስታዲየሞች በአፍሪቃ የእግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF) መስፈርት መሠረት ባለመስተካከላቸው ብሔራዊ ቡድኑ ውጭ ሃገራት እየተጓዘ ለአላስፈላጊ ወጪ እና ደጋፊ እጦት ተዳርጓል ። ቃለ መጠይቅ አድርገናል ። የኢትዮጵያ ብስክሌት ሻምፒዮና ትግራይ ክልል ውስጥ ትናንት ተጠናቋል፤ ዘገባ ይኖረናል ። ኤርትራ አስመራ ከተማ ውስጥም የኤርትራ ብሔራዊ የጎዳና ላይ የብስክሌት የፍጻሜ ፉክክር ትናንት ተከናውኗል ። ልዩ የኦሎምፒክ ጨዋታዎች በትናንትናው ዕለት ጀርመን ቤርሊን ከተማ ውስጥ ፍጻሜ አግኝቷል ።  

በአፍሪቃ የእግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF)
በአፍሪቃ የእግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF)

አትሌቲክስ
የጀግናው ሻምበል አበበ ቢቂላ ማራቶን አንጋፋው ውድድር በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዓመታዊ የውድድር መርኃ ግብር መሠረት ለ39ኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተከናውኗል ። ልዮ ስሙ ሰሚት ለስላሳ ፋብሪካ አካባቢ እሁድ ሰኔ 18 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ከማለዳው 1:00 ጀምሮ ውድድሩ ሲካሄድ ቆይቶ በስኬት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዐስታውቋል። 

በሴቶች ውድድር፦ አሸናፊ በመሆን የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀችው ከመቻል ቡድን ጠጂቱ ሥዩም ስትሆን ፤ 2:41.33 ሮጣ በአንደኛነት አጠናቃለች ። አስናቀች ግርማ ከኦሮሚያ ፖሊስ እንዲሁም ብዙአገር አደራ፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የብር እና የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል ። በወንዶች ተመሳሳይ ፉክክር የፌዴራል ፖሊስ አትሌት ብርሃን ነበበው 2:14.51 በመሮጥ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል። ልመንህ ጌታቸው ከመቻል ስፖርት እንዲሁም የፌዴራል ማረሚያ አትሌቱ ገልገሎ ጦና ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ይዘው በማጠናቀቅ የብር እና የነሐስ ሜዳሊያ አጥልቀዋል ። 

ከ13 ዓመታት በኋላ የኦሎምፒክ እና ፓራሊምፒክስ ጨዋታዎችን ለማዘጋጀት ተስፋ የሰነቀችው ጀርመን ቤርሊን ከተማ ውስጥ ትናንት ልዩ ኦሎምፒክ አጠናቃለች ። የቤርሊኑ ልዩ ኦሎምፒክ ላይ 330,000 ግድም ሰዎች ታድመውበታል ። ብራንደንቡርግ መግቢያ ላይ በተከናወነው የመዝጊያ ስነስርዓቱ ወቅትም የኦሎምፒክ ሠንደቅ ዓላማ ቀጣዩን የ2025 ልዩ የክረምት ኦሎምፒክ ለምታዘጋጀው ለቱሪን ከተማ ተሰጥቷል ።  ልዩ ኦሎምፒክ የአእምሯዊ ጉዳተኞች መገለል እንዳይገጥማቸው በሚል የተጀመረው ከግማሽ ምእተ ዓመት በፊት እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1968 ዓ.ም ነው ።
እግር ኳስ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ማጣሪያ ግጥሚያዎቹን በአጠቃላይ በስታዲየም እንከን የተነሳ ከሜዳው ውጪ እንዲያደርግ ተገድዷል ። ከዚህ ቀደም ባደረጋቸው የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ሞሮኮ ውስጥም ሆነ ማፑቶ ሞዛምቢክ ውስጥ ያገኛቸው ውጤቶች አመርቂ አይደሉም ።  ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ማፑቶ ውስጥ ከማላዊ ጋር የነበረውን ግጥሚያ ያለምንም ግብ አጠናቋል ። በአፍሪቃ የእግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF) አሟሉ ብሎ በሰጠው መመሪያ መሠረት የስታዲየም ችግራችን ባለመቀረፉ ውድድሮቹን ሌሎች ሃገራት በመጓዝ ለማድረግ ተገደናል ። በአሁኑ ሰአት ስታዲየሞቻችን ይዘታቸው ምን ይመስላል? የስፖርት ጋዜጠኛ ዖምና ታደለ ስታዲየሞቹ ላይ ቅኝት አድርጓል ። ለዓለም አቀፍ ውድድር ተዘጋጁ የተባሉት አራቱም ስታዲየሞች የተጠየቀውን መስፈርት የሚያሟሉ አይደሉም ተብሏል ።

የኢትዮጵያ ብስክሌት ሻምፒዮና 
ከረዥም የጦርነት ግዚያት በኃላ በትግራይ ክልል ተወዳጁ የብስክሌት ውድድር ዳግም ተመልሷል። ሰሞኑን መቐለ የ2015 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብስክሌት ሻምፒዮና ውድድር እያስተናገደች የሰነበተች ሲሆን፥ ትናንት በነበሩ ውድድሮችም ሀገራዊው ሻምፒዮና ተጠናቋል። ከሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች እና የተለያዩ የሀገሪቱ ክለቦች የተሳተፉበት ይህ የኢትዮጵያ ብስክሌት ሻምፒዮና፥ በጦርነቱ ምክንያት በትግራይ ለረዥም ግዜ ተቋርጦ የቆየው ተወዳጁ ስፖርትን ዳግም ያነቃቃ ሆኗል። ትናንት ጠዋት በመቐለ ጎዳናዎች የነበረውን የብስክሌት ውድድር በርካታ የከተማዋ ነዋሪ ወጥቶ ሲከታተለው ነበር። የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት ወንድሙ ኃይሌ በትግራይ የስፖርቱ እንቅስቃሴ መልሶ ለማነቃቃት እና ህዝቡ ወደ ስፖርቱ ለመሳብ ዓመታዊ የኢትዮጵያ ብስክሌት ሻምፒዮና በመቐለ መዘጋጀቱ ገልፀውልናል ።

የብስክሌት ተፎካካሪ በጎዳና ላይ ብስክሌቱን ሲዘውር
የብስክሌት ተፎካካሪ በጎዳና ላይ ብስክሌቱን ሲዘውርምስል Stefan Schurr/Westend61/IMAGO
ልዩ ኦሎምፒክ በጀርመን ቤርሊን ከተማ ውስጥ
ልዩ ኦሎምፒክ በጀርመን ቤርሊን ከተማ ውስጥ ምስል Dominika Zarzycka/ZUMA Wire/IMAGO

በውድድሩ የትግራይ ቡድኖች እና የግል ተወዳዳሪዎች በወንድ እና ሴት እንዲሁም በአዋቂ እና ወጣት የበላይነት ያሳዩ ሲሆን፣ በትናንትናው መዝጊያ ውድድር ብስክሌተኛው ብዙዓየሁ ተስፍኡ በወንዶች አሸናፊ ሲሆን በሴቶች ደግሞ የመስፍን ኢንዳስትርያል ኢንጅነሪንግ ስፖርት ቡድን ብስክሌተኛዋ ፅጌ ካሕሳይ አሸንፋለች ። ስለውድድሩ አስተያየታቸውን የሰጡን አሸናፊዋ ብስክሌተኛ ፅጌ ካሕሳይ እና ከድሬደዋ የተገኘው ኪያ ጀማል ውድድሩ ጠንካራ ፉክክር የታየበት ነበር ብለዋል ።  የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌደሬሽን ትናንት የተገባደደው በመቐለ የተዘጋጀው የኢትዮጵያ ብስክሌት ሻምፒዮና በትግራይ የስፖርቱ እንቅስቃሴ ዳግም የመለሰ ብሎታል ።

በተያያዘ ዜና፦ የኤርትራ ብሔራዊ የጎዳና ላይ የብስክሌት የፍጻሜ ፉክክር ትናንት ተካሂዷል ። አራት ሰአት ግድም በፈጀው የኤርትራው ብርቱ ፉክክር በወንዶች አወት አማን አሸናፊ ሆኗል ። ጴጥሮስ መንዲ የሁለተኛ ደረጃ አግኝቷል ። ኄኖክ ሙሉብርሃን ሦስተኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል ። 

የአውሮጳ እግር ኳስ

ዕድሜያቸው ከ21 ዓመት በታች የአውሮጳ እግር ኳስ ውድድር የጀርመን ቡድን
ዕድሜያቸው ከ21 ዓመት በታች የአውሮጳ እግር ኳስ ውድድር የጀርመን ቡድንምስል Sebastian Kahnert/dpa/picture alliance

ዕድሜያቸው ከ21 ዓመት በታች የአውሮጳ እግር ኳስ ውድድር የጀርመን ቡድን በሁለተኛ ጨዋታውም ውጤት አልቀናውም ። በትናንትናው ዕለት ከቼክ ሪፐብሊክ ጋር የተጋጠውመው የጀርመን ቡድን የአንድ ለዜሮ ሽንፈት ገጥሞታል ። በምድብ «ሐ» የሚገኘው የጀርመን ቡድን ባለፈው ሳምንት ሐሙስ በመጀመሪያው ጨዋታ ከእሥራኤል ጋር ተጋጥሞ አንድ እኩል ተለያይቷል ። በወቅቱ ጥቁር የቆዳ ቀለም ያላቸው ተጨዋቾች ፍጹም ቅጣት ምት በመሳታቸው ለብርቱ የዘረኝነት ስድብ እና የበይነ መረብ ጥቃት ተዳርገዋል ።
 

የጀርመን የሴቶች ብሔራዊ ቡድን

በአንጻሩ የጀርመን የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ መዳረሻ ከቬትናም ጋር ባደረገው የወዳጅነት ጨዋታ 2 ለ1 አሸንፏል ። ሆኖም ግን ጠንካራ የነበረው ተጋጣሚው ላይ ያሳየው የሚጠበቀውን ያህል አይደለም ተብሏል ። በቅዳሜው ውድድር ላይ አምበሏ አሌክስ ፖፕ እና አምስት የባየርን ሙይንሽን ተጨዋቾች አልተሰለፉም ። አውስትራሊያ እና ኒውዚላንድ የሚያዘጋጁት ከ6 አኅጉራት የተውጣጡ 32 ሃገራት የሚሳተፉበት የሴቶች የዓለም ዋንጫ እግር ኳስ ግጥሚያ ሊጀመር አንድ ወር ግድም ቀርቶርቶታል ። የሴቶች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫን ለአራት ጊዜያት በመውሰድ ዩናይትድ ስቴትስ ጠንካራ ቡድን መሆኗን አስመስክራለች ። የጀርመንም ቡድን ቢሆን ባለፈው የዓለም ዋንጫ ለፍጻሜ ደርሶ ዋንጫውን ያጣው ለጥቂት በእንግሊዝ ቡድን 2 ለ1 በመሸነፍ ነበር ። 
የዝውውር ዜና

በጀርመን የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ መዳረሻ  በወዳጅነት ጨዋታ 2 ለ1 የተሸነፈው የቬትናም ቡድን
በጀርመን የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ መዳረሻ በወዳጅነት ጨዋታ 2 ለ1 የተሸነፈው የቬትናም ቡድንምስል Sebastian Christoph Gollnow/dpa/picture alliance

የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊው ኢልካይ ጉንዶዋን የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ካነሳበት ማንቸስተር ሲቲ ወደ ስፔኑ ባርሴሎና በነጻ ዝውውር መፈረሙ ተዘግቧል ። በሌላ ዜና፦ የባርሴሎናው የ34 ዓመቱ ተጨዋች ሠርጂዮ ቡስኬት እንደ ሊዮኔል ሜሲ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ኢንተር ሚያሚ ቡድን ያቀናል ተብሏል ። ቡስኬት የባርሴሎናን መለያ ለ18 ዓመታት ለብሶ ተጫውቷል ። 

የእንግሊዝ ብሔራዊ የእግር ቡድን የቀድሞ ተጨዋች እና የእግር ኳስ ተንታኙ ጋሪ ኔቭል ተጨዋቾች በዝውውር ወደ ሳዑዲ አረቢያ እንዳይጎርፉ ፕሬሚየር ሊጉ አስቸኳይ ማዕቀብ ሊጥል ይገባል ሲል አስጠንቅቋል ። ከዚህ ቀደም ክሪስቲያኖ ሮናልዶ፤ ካሪም ቤንዜማ እና ንጎሎ ካንቴን ጨምሮ ታዋቂ የአውሮጳ ተጨዋቾች ለሳዑዲ ዓረቢያ ቡድኖች ፈርመዋል ። የቸልሲው ግብ ጠባቂ ኤድዋርድ ሜንዲ የሳዑዲ ፕሮ ሊግን ሊቀላቀል ይችላል የሚለው ዜናም ሰሞኑን ጎልቶ ተሰምቷል ።  

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ/ዖምና ታደለ

ሸዋዬ ለገሰ