1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎትና ፈተናው

ሐሙስ፣ ነሐሴ 4 2015

ሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ ያገረሸው የጸጥታ መደፍረስ ሰብኣዊ አቅርቦቶችን ክፉኛ እንደሚፈትን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ (UNOCHA) አስታወቀ። ድርጅቱ በምዕራብ ኦሮሚያ ተሻሽሏል ያለው የጸጥታ ሁኔታ ለዕርዳታ አቅርቦት ምቹ ሁኔታን ቢፈጥርም የሰብዓዊ ድጋፍ ቁሳቁሶች እጥረት በማጋጠሙን አመልክቷል።

https://p.dw.com/p/4V0Hn
Symbolbild Welternährungsprogramm der Vereinten Nationen
ለሰብአዊ እርዳታ የተከማቸ እህል ምስል AP Photo/picture alliance

የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት OCHA

 

ሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ ያገረሸው የጸጥታ መደፍረስ ሰብኣዊ አቅርቦቶችን ክፉኛ እንደሚፈትን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ (UNOCHA) አስታወቀ። ድርጅቱ በምዕራብ ኦሮሚያ ተሻሽሏል ያለው የጸጥታ ሁኔታ ለዕርዳታ አቅርቦት ምቹ ሁኔታን ቢፈጥርም የሰብዓዊ ድጋፍ ቁሳቁሶች እጥረት በማጋጠሙን አመልክቷል። 

እንደ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ (UNOCHA) ሰሞነኛ ዘገባ በኢትዮጵያ አሁን እየተስተዋለ ያለው የፀጥታ ጉዳይ የሰብኣዊ እርዳታውን ሁኔታ ውስብስብ እና ከባድ አድርጎታል። በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ ያገረሸው የፀጥታ ችግር በኪስ ቦታዎች ላሉ የማኅበረሰብ አካላት እርዳታ ለማድረስ ፈታኝ ጋረጣ መፍጠሩን የድርጅቱ ዘገባ ያሳያል። እንደ ዘገባው ከዚህ በፊት በነበረው የጸጥታ ስጋት ምክንያት ወደ አካባቢው ለመድረስ ከባድ የነበረው የምዕራብ ኦሮሚያ አከባቢ አሁን ተሻሽሏል በተባለው የፀጥታ ሁኔታ ሰብዓዊ ድጋፍን ለማዳረስ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። ይሁንና በያዝነው ጎርጎርዮሳዊ ዓመት 2023 በእርዳታ ቁሳቁስ እጥረት ምክንያት በተለይም ምዕረብ ኦሮሚያ ውስጥ ለሚገኙ አራቱ የወለጋ ዞኖች አስፈላጊውን የማቅረብ ጥረቱን ፈታኝ አድርጎታል ብሏል።በምዕራብ ኢትዮጵያ የፀጥታ ችግር ተጽእኖ በእርዳታ አቅርቦት ላይ 

የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ አገምሳ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ንጉሤ ባንጃ ለዶቼ ቬለ በሰጡት አስተያየትም ይህንኑን አረጋግጠዋል። ቢያንስ በከተማ ውስጥ የሰዎች ሰላም እየተሻሻለ ቢመጣም፤ አሁን ፈተና የሆነው የሚላስ የሚቀመስ መታጣቱ ነው ብለዋል። «ምንም የመጣልን አዲስ ነገር የለም ሰው ችግር ውስጥ ነው። ማጣት ድህነቱ ከፍቶ ክረምቱን እንኳ እንዴት እንደሚዘለቅ ግራ አጋቢ ነው። በቂ እርዳታ ስለማይደርሰን ሰው እያቃተው ነው።»

በምሥራቅ፣ ምዕራብ፣ ሆሮጉዱሩ እና ቀለም ወለጋ ዞኖች ላለፉት አራት ዓመታት በነበረው ግጭት እና፤ ከአምስት ዓመት በፊት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ በርካታ ሰዎች በመፈናቀላቸው አሁን በምዕራብ ኦሮሚያ 725 ሺህ ገደማ ተፈናቃይ መኖሩንም ዘገባው ጠቅሷል።

በምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ እና በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ጃርደጋ ጃርቴ ወረዳዎችም የፀጥታ ችግሩ አፈናቅሎ ከተማ ያጎራቸው ወገኖችም በሚሰጡት አስተያየት፤ «በርካቶች በተፈናቀሉባት የአሙሩ ወረዳዋ አገምሳ ከተማ እና በምሥራቅ ወለጋ ብዙዎች በተፈናቀሉባት ኪረሙ እንዲሁም በጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ በቂ የእርዳታ አቅርቦት የለም።» መንገድን ጨምሮ የመሠረታዊ ማኅበራዊ መገልገያ አውታሮችም በበቂ ሁኔታ አገልግሎት አለመስጠታቸው የዕለት ተዕለት ኑሯቸውን ፈትኖ ለእርዳታ እጃቸውን እንዲዘረጉ ማስገደዱን አክለው አመልክተዋል።

UN-Nothilfekoordinator Griffiths
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ አስተባባሪ OCHA ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስምስል Martial Trezzini/KEYSTONE/dpa/picture alliance

በእነዚህ አራት የወለጋ ዞኖች የጸጥታ ሁኔታው ተሻሽሎባቸዋል ተብሎ በታመነባቸው አከባቢዎች እስከ ተያዘው ጎርጎርዮሳዊ ዓመት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት 450 ሺህ ገደማውን ሕዝብ ወደ ነባር ቀዬያቸው የመመለስ ውጥን መያዙንም ነው የሰብኣዊ ድጋፍ ተቋሙ ያሳወቀው። የተፈናቃዮች ወደ ቀዬያቸው ለመመለስ መጓጓት ደግሞ ለዚህ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራልም ተብሏል። ስለዚህ እቅድና ይዞታው ከክልሉ ቡሳ ጎኖፋ ኃላፊ እና ከተቋሙ ኮሚዩኒኬሽን ተጠሪ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ደጋግመን በእጅ ስልካቸው ብንደውልም ምላሻቸውን ባለማግኘታችን አልተሳካም። እንደ ሰብዓዊ ድርጅቱ ዘገባ ከትግራይ ተነስቶ በአፋር አባዓላ፣ ኢዋ፣ ኩኔባ፣ መጋሌ እና ያሎ ወረዳዎችን ያዳረሰው የበረሃ አንበጣ በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን የሚፈትን ሌላው ጉዳይ ሆኗል።  

በክረምቱ የጣለው ዝናብ በስፋት የሚተኛበት አፋር ክልል ዜጎችን ለወባ ወረርሽኝ ማጋለጡን ያመለከተው ዘገባ 6,800 ሰዎች በወረርሽኙ መጠቃታቸውን ገልጿል። በአማራ ክልል የተስፋፋው የኮሌራ ወረርሽኝ ደግሞ ከ2,300 በላይ ሰዎች ማዳረሱንም ጠቁሟል። በወርሐ ሐምሌ ወረርሽኙ 18 ወረዳዎች ውስጥ መከሰቱንም አመልክቷል። በተመሳሳይ የኮሌራ ወረርሽኝ በኦሮሚያ፣ ሶማሌ፣ ደቡብ እና ሲዳማ ክልሎችም 16,346 ሰዎች ላይ መታየቱንም ዘገባው አስታውቋል።

ሥዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ