1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የርህራሔ ጠብታ ያለታየበት የጭካኔ ተግባር

ረቡዕ፣ ኅዳር 11 2017

በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር ዞን አንዲትን የዘጠኝ ዓመት ሕፃን አግተው ከነሕይወቷ በወራጅ ወንዝ እንድትወሰድ አድርገዋል የተባሉና ገንዘብ የጠየቁ ሦስት ወንጀለኞች ክ21 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

https://p.dw.com/p/4nD4y
ጎንደር ከተማ
ጎንደር ከተማ ፎቶ ከማኅደር ምስል Alemnew Mekonnen/DW

ጥፋተኞች እስከ ዕድሜ ልክ እስራት ተበየነባቸው

 

አቶ ደርበው ተፈራ በጎንደር ከተማ ቀበሌ 18 ሸዋ በር በተባለ አካባቢ ይኖራሉ። አቶ ደርበው ክ20 ዓመታት በፊት ኑሯቸውን የሚገፉት በጋሪ ከቦታ ቦታ ዕቃ እየጫኑ በማውረድ ነበር። በመጋቢት 18 ቀን 1994 በሥራ ላይ እንዳሉ የመኪና አደጋ ያጋጥማቸዋል። ዛሬ ሁለቱም እግሮቻችው ተጎድተዋል። ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱት በአካል ድጋፍ (ክራንች) ነው።

ዘመድ አዝማድ ተባብሮ የተወሰኑ ከፍሎች ያሉት መኖሪያ ቤት ሠርቶላቸው በኪራይ በሚያገኙት ገንዘብ ኑሯቸውን ይገፋሉ። በቤታቸው ከተከራዩ ሰዎች መካከል ባልና ሚስት እንዲሁም ሌላ አንድ መምህር ይገኛሉ።

አዳጊዋ ከነሕይወቷ ወንዝ ውስጥ ተጥላ ተገድላለች

ኬብሮን ደርበው እንደ ዓይን ብሌናቸው የሚያዩዋት ዘጠኝ ዓመት ልጃቸው ናት፣ ለአቶ ደርበው። ነሐሴ 22 ቀን 2016 ዓም ከተከራዮች አንዷ የሆነችው አበባ ዘለቀ በዕለቱ ከረፋዱ 5፡30 ሰዓት ሲሆን የአከራይን ልጅ ኬብሮን ደርበውን አታልላ ከቤት በማስወጣት ባለቤቷ ለሆነው ሙሉጌታ አታሎ ታስረክባለች። ሙሉጌታ አታሎ የሕፃኗ መምህር የሆነውን ያዛቸውውብሥራን ያገኘውና ሕፃኗ ድምፅ እንዳታሰማ አፏን በጭርቅ በማፈን ሲያስቃዩ ይውላሉ። ምሽት 1፡30 ሰዓት አዳጊዋን ልጅ ወደ ወንዝ ይዘው ይሄዳሉ።  ምን እየተደረገ እንደሆነ በግልፅ የማታውቀው ሄብሮን ከነሕይወቷ «ቀያ» ከተባለ ወንዝ ውስጥ ተጣለች። ወንዙ የት እንዳደረሳትም እስካሁን መረጃ የለም፡፡

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሕዝብ ግኙነት ባለሙያw ወ/ሮ ማስተዋል ወርቁ እንደተናገሩት ወንጀለኞቹ በፍርድ ቤት ቀርበው በሰጡት ቃል ልጅትዋን ከነሕይወቷ ወንዝ ውስጥ መጣላቸውን አምነዋል።

የወንጀሉ ተባባሪ መምህር «የማስለቀቂያ ገንዘብ» አብሮ ሲሰበስብ ነበር

ወንጀለኞቹ ልጅቷን በወንዝ እንድትወሰድ ካደረጉ በኋላ «አንድ ሚሊዮን ብር» ማስለቅቀያ ገንዝብ እንደጠየቁ ወላጅ አባት አቶ ደርበው ይገልፃሉ። ገንዝብ ሲሰበሰብ የወንጀሉ ተሳታፊ የነበረው የሕፃኗ መምህር አብሮ ገንዘብ እየሰበሰበ ለሌሎቹ ግብረ አበሮቹ መረጃ ይሰጥ እንደነበር አባት ይናገራሉ።

የፀጥታ አካላት ባደረጉት ያልተቋረጠ ክትትል ሦስቱም ወንጀለኞች በተለያዩ ቀናት በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ሲታይ ቆይቶ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትናንት ኅዳር 10 ቀን 2017 ዓ ም በዋለው ችሎት ወንጀለኞችን ከ21 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ በእስራት እንዲቀጡ ውሳኔ መተላለፉን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሕዝብ ግኙነት ባለሙያዋ ወ/ሮ ማስተዋል ወርቁ ተናግረዋል።

«አንደኛ ተከሳሽ አበባ ዘለቀ ሥራ ፈላጊ፣ ዕድሜዋ 24 ሲሆን በ21 ዓመት እስራት፣ ሁለተኛ ተከሳሽ ሙሉጌታ አታሎ ሥራው ግብርና፣ ዕድሜው 28፣ በዕድሜ ልክ እስራት፣ ሦስተኛ ተከሳሽ ያዛቸው ውብሥራ ሥራ መምህር ዕድሜው 29 በዕድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ ወስኗል» ሲሉ ነው ወ/ሮ ማስተዋል ለዶይቼ ቬሌ በስልክ የተናገሩት።

«ገዳይና አጋቾቻቸው ያልታወቀላቸው ሰዎች ስላሉ በውሳኔው ደስተኛ ነኝ» የሟች አባት

ወላጅ አባት አቶ ደርበው ታፈረ ልጃቸውን እንደወግ ባህሉ መቀበር አለመቻላቸው የእግር እሳት ቢሆንባቸውም በተሰጠው ውሳኔ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የአራተኛ ክፍል ተማሪዋ ሄብሮን በትምህርቷ ጎበዝ እንደነበረች የሚናገሩት አባት ከ90 በታች አማካይ ውጤት ስታመጣ እንኳ አነሰኝ ብላ ታለቅስ እንደነበር አስታውሰዋል። ወንጀለኞቹ ሞት የሚገባቸው ቢሆንም በርካታ አጋቾቻቸው ያልተያዙ፣ የታገቱ ሰዎች አድራሻቸውም ባልተገኘበት ሁኔታ ውሳኔው አንሷል ለማለት እንደማይደፍሩም ተናግረዋል።

በአንዳንድ የአማራ ክልል ከተሞች እገታ ቀደም ሲል ከነበረው አኳያ የተወሰነ መሻሻል እያሳየ ነው ቢባልም አሁንም ግን የኅብረተሰቡ ቀዳሚ የስጋት ምንጭ እንደሆነ ነው ነዋሪዎች የሚገልፁት።

ዓለምነው መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ