የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት
ዓርብ፣ የካቲት 8 2016ኢሰመኮ ስለ መርዓዊ የሰጠው መግለጫና የኢትዮጵያ መንግሥት ምላሽ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በምህጻሩ ኢሰመኮ በሰሜን ጎጃም ዞን በመርዓዊ ከተማ ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም. በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እና በታጠቁ ኃይሎች መካከል ከተካሄደው ውጊያ በኋላ የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች “ለፋኖ ድጋፍ አድርጋችኋል” በሚል ምክንያት ቢያንስ 45 ሲቪሎችን መግደላቸውን ባደረገው ክትትል ማወቁን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ነበር ይፋ ያደረገው ።
ኢሰመኮ ከዚህ ሌላ “የፋኖ አባላት ናቸው” በሚል ተጠርጥረው የተያዙ እና ለጊዜው ብዛታቸውን ለማረጋገጥ አልተቻለም ያላቸው ሰዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከሕግ ውጭ መገደላቸውን ለማወቅ መቻሉንም አስታውቋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ በመርዓዊ ከተማ ተፈጽሟል የተባለውን የ45 ሰላማዊ ሰዎች ግድያ አስተባብሏል።የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ በተለይ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ መካከል ግጭት እንደነበር አረጋግጠው “የመከላከያ ኃይሉ የትኛውንም ዐይነት ሲቪል ዒላማ አላደረገም”በማለት ተናግረዋል።ስለ መርዓዊው ግድያ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች የተለያዩ አስተያየቶችን ሰጥተዋል።የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት
ከመካከላቸው ጽንፍ የያዙትንና ዘለፋ ያመዘነባቸውን ወደ ጎን ትተን ሌሎቹን አስተያየቶች ስንቃኝ «ይህ የጊዜ ጉዳይ ነው። ሁሉ ነገር ተቀይሯል። በማለት የሚጀምረው ጌታቸው መልሰው በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረ አስተያየት «ለመርዓዊ ፍትህ ያስፈልገናል፤ በንጹሀን ዜጎች ላይ የሚፈጸመው ግድያ መቆም አለበት የሚል ጥሪ አካቷል። ሰዒድ አራጋው ሀቅ ይጠራል ጊዜው ቢቆይም። ዮሐንስ አሰፋ ጆም በአጭሩ «ያሳዝናል ለሁሉም ጊዜ ይፈርዳል» ብለዋል በፌስቡክ ። የአካሌ ታደገኝ አስተያየት ደግሞ «ፍትህ ይዘገይ ይሆናል። ግን አይቀርም አዎ የዘገየ ፍትህ ግን እንዳልተሰጠ ይቆጠራል ይህን እናውቃለን ይላል። ጥቂት የማይባሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች ኢሰመኮ በመግለጫው የጠቀሰው የሟቾች ቁጥር እጅግ አንሷል ሲሉ ጠንከር ያሉ ወቀሳዎችን አቅርበዋል። ከመካከላቸው ማሙ መር ኮሚሽኑ የቁጥሩን ጉዳይ እንደገና እንዲያጣራ ጠይቀዋል።
ከፍታ ጋዮላ በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረ አስተያየት «የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ግን የሚናገረውን መረጃ እንድናምን የመንግስት ኃይሎች ብቻ ሳይሆን የታጠቁ ሸማቂዎች የፈፀሙትንም ጥሰቶች ማካተት ነበረበት ። አለበለዚያ የሪፖርት አቀራረቡ የገለልተኝነት ጥያቄ ያስነሳል» በማለት ኢሰመኮ ያቀረበው መረጃ ይጎድለዋል ያለውን ጠቁሟል። ሌላው አስተያየት ሰጭ ናቲ ናትዋ በበኩላቸው «መግለጫ ብቻውን ምን ይፈይዳል፤ ካሉ በኋላ «ወረድ ብሎ የእውነት ስራ መስራት እንጂ ወይስ ደግሞ ትናንት እንዲህ ብዬ ነበር። ሰሚ አላገኘሁም፤ለማለት ነው። ያም ሆነ ይህ ሰው እየሞተ ነው ወረድ ብሎ መስራት ይጠይቃል።» በማለት አሳስበዋል። ሙክታር ሸምሱም ከናቲ አስተያየት ጋር የሚቀራረብ ወቀሳ አቅርበዋል። ኢሰመኮ ሀገሪቱ ውስጥ እየተካሄደ ላለው የሰዎች ህገወጥ የመብት ጥሰትና ሞት መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ ዜና መዘገቡን ስትሰማ ሀገር ዓልባ የመሆን ስሜት እንዲሰማን ያደርገናል» ይላል። «ኢሰመኮ ዓላማና ግቡ የሰብአዊ መብቶች ሲጣሱ ማጣራትና ለሚመለከተው የመንግስት ተቋም ማሳወቅ ብቻ ነው ። በዳዮችን ይዞ ለፍርድ ማቅረብ የፖሊስ ነው ኢሰመኮን አይመለከትም።» ሲሉ ጀምስ ባላገሩ የበኩላቸውን መልስ ሰጥተዋል።
የአውሮጳ ኅብረት እና የአሜሪካ መንግሥት በመርዓዊው ግድያ “ገለልተኛ ምርመራ” እንዲደረግ ጥሪ አስተላልፈዋል። አብርሃም አሰፋ በመርዓዊ ሴቶችና ህጻናትን ጨምሮ የተገደሉት ብዙ መሆናቸውን ጠቅሰው በገለልተኛ ወገን ማጣራት እንዲካሄድ ጠይቀዋል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ጉዳዩን በመደገፉም አመስግነዋል። ዶክተር ለገሰ ቱሉ ግን ጉዳዩ የሚመለከተው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ነው ሲሉ ለዶቼቬለ ተናግረዋል።የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት፦ህዳር 14 ቀን 2016 ዓ.ም.
አማርኛ የአፍሪቃ ኅብረት የስራ ቋንቋ እንዲሆን ኢትዮጵያ መጠየቋ
ኢትዮጵያ አማርኛ የአፍሪካ ኅብረት የሥራ ቋንቋ እንዲሆን በዚህ ሳምንት ነበር የጠየቀችው። አዲሱ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ አማርኛ የአፍሪካ ኅብረት የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ጥያቄ ያቀረቡት በአዲስ አበባ በተካሄደው 44ኛው የአፍሪካ ኅብረት የአስፈጻሚዎች ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ ላይ ነው። እስካሁን ኅብረቱ አረብኛ፤ እንግሊዝኛ፤ ፈረንሳይኛ፤ ፖርቱጋልኛ፤ ስፔንኛ፤ እና ስዋሂልን ቋንቋዎችን ለሥራ ይጠቀማል። ኅብረቱ ባለፈው ዓመት ጉባኤው ነበር ስዋሂሊ ቋንቋን በሥራ ቋንቋነት ተቀብሎ ያጸደቀው። ኢትዮጵያ ለአፍሪቃ ኅብረት ባቀረበችው በዚህ ጥያቄ ላይ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተለያዩ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። ጥያቄው መነሳቱን ያወደሱ ፣ መዘግየቱን የነቀፉ ፣የአማርኛ ቋንቋ በሀገር ውስጥ እንዲጠፋ እየተደረገ ነው የሚሉ የአፍሪቃ ኅብረት ተጨማሪ የስራ ቋንቋ እንዲሆን መጠየቁን የተቹም አሉ።
ልሳኑ ልጆ በሚል የፌስቡክ ስም ጥያቄውን ሚዛናዊ ውጤቱም አዎንታዊ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን የሚል አስተያየት ተሰጥቷል። አበባው ዳኔ ደግሞ እጅግ በጣም ደስ ይላል ሲሉ ጀምስ ተስፋዬ በተግባር ላይ ቢውል አግባብነት ያለው ጥያቄ ነዉ ሲሉ ድጋፋቸውን ገልጸዋል። ኤርሚ ጆክ ቢዘገይም ጥሩ እርምጃ ነው ቀጥሉበት ሲሉ አበረታተዋል።
ፈይሳ ካሳ ግን «በቅድሚያ ወይም ከዚያ በፊት በኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም ክልሎች ያለ ስጋት እንዲወራ ቢደረግ» የሚል ሀሳብ ሰንዝረዋል። አማርሙሄ አምሳሉ አማርኛን በሀገር ዉስጥ እያጠፉ ለአጀንዳ ማስቀየሪያ ይመስል የአፍሪካ ኅብረት የስራ ቋንቋ ይሁን ብሎ መጠየቅ ምን ማለት ነው። መጀመሪያ ለቋንቋው ክብር ይኑራችሁ። ሲሉ ተችተዋል። ኤልያስ አዲስ አማርኛ ቋንቋን ከብሔራዊ ፈተና ቀንሰህ ፤ አማርኛ የአፍሪቃ ስራ ቋንቋ እንዲሆን ጠየኩ ስትለን የምንሰማ ይመስልሃል» ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል። አምባሳደር ታዬ ለጉባኤው ባሰሙት ንግግር አማርኛ ተጨማሪ የአፍሪቃ ኅብረት የስራ ቋንቋ መሆኑ አህጉሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ እገዛ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
የዓለም የራድዮ ቀን
የዓለም የራዲዮ ቀን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ በተለያዩ ሃገራት ታስቧል። የተመ የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት «ዩኔስኮ» የዓለም የሬድዮ ቀን በየዓመቱ በጎርጎሮሳዊው የካቲት 13 እንዲታሰብ በጎርጎሮሳዊው 2011 ዓ.ም ከወሰነ ከአንድ ዓመት በኋላ የዓለም የሬድዮ ቀን፤ በዓለምአቀፍ ደረጃ መከበር ጀምሯል። ዓላማው ያለፉትን ዓመታት የራድዮ ሰፊ አገልግሎት፣ አሁንም ያልተቋረጠውን ጠቀሜታውንና የወደፊቱን ተስፋ ማክበር ነው። በዘንድሮው የራድዮ ቀን የተከበረውም የራድዮ ታሪክ ብቻ ሳይሆን ራድዮ በኅብረተሰቡ ውስጥ አሁንና በመጪዎቹ ዓመታት የሚጫወተውን ሚና ማክበር መሆኑን የዩኔስኮ ዋና ፀሐፊ ኦድሬ አዙሌይ ዕለቱን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት አስታውቀዋል። ዶቼቬለ ራድዮ በኢትዮጵያ ያለው ሚናና ተፈላጊነቱ እስከምን ድረስ እንደሆነ የፌስቡክ ተከታዮቹን ጠይቆ ነበር። ምትኩ ጥላሁን በፌስቡክ «ሬዲዮ ባለፉት ፣አሁን እና ወደፊት ዘመናት ቴክኖሎጂውን በተረዳ ሰው ዘንድ ጥቅሙ ላቅ ያለ ነው ለምሳሌ እኔ እንግሊዝኛን የቻልኩት ቢቢሲ ሬዲዮ በማዳመጥ ነው። ሲሉ በራድዮ ስላገኙት ጥቅም ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
የቤት ኪራይ መናር፤ የሱዳን ወረራ እና የመንግሥት ምላሽ፤ በረሃብ ሰዎች ሞቱደባሎ አጂማ «ለእኔ ዓለም ጣፋጭ እና የደስታ ምንጭ መሆኗን ለሰው ልጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሳየው ሬዲዮ ነው ባይ ነኝ ሲሉ አዲስ መኮንን በአጭሩ «ሰው አድርጎናል» ብለዋል።
ራብያት ሀሰን በበኩላቸው «ሬዲዮ በኢትዮጵያ ዛሬ የጣቢያ ብዛቱ የጨመረ ቢሆንም ከአንድ ማሰራጫ የሚተላለፍ ይመስላል። ሁሉም የሚያሰራጩት ስለኳስ በመሆኑ ከድሮው ጋር ሳነፃፅረው ምንም ሬዲዮ ጣቢያ የሌለ ነው ሚመስለኝ እርግጥ ነው በርካታ አድማጭ አድማጭ አፍርተዋል ። ብዙ ስለኳስ እውቀት ያለው ወጣት የእያንዳንዱን ክለብ ኳስ ተጫዋቾች የህይወት ታሪክ ከነኪሎአቸው የሚተርክ ትውልድ ቀርፀዋል ።ምንም እንኳን ብቃት ያላቸው ሃገርና ባንዲራ ከፍአስደርገው የሚያኮሩ ተጫዋቾችን ማፍራት ባይችሉም ። ጠንካራ የእግርኳስ ፌዴሬሽን እንዲቋቋም ማድረግ ቢሳናቸውም ምጡቅ የኳስ ትንታኔ የሚሰጡ በርካታ ጋዜጠኞች ና ማሰራጫዎች በሬዲዮ ዘርፍ ዛሬ ሞልተውናል ። ለዚህ ሃገርና ህዝብ ምን የሚኖራቸው ፋይዳ አለ ለሚለው ግን መልሱ ን ጊዜ ይመልሰው። በማለት ሀሳባቸውን አጠቃለዋል። ጌታ ጎፋ « ለእኛ ገጠር ለተወለድን ለሬዲዮ አሁንም አንድ ቤተሰብ ነን።»
«ሬዲዮ በኢትዮጵያ አሁን ያለው ሚና ለገዥዎች ብቻ እንጅ ለሚራበው፣ ለሚጠማው፣ ለሚፈናቀለው፣ ለሚገደለው፣ ለሚሳደደው፣ ህብት ንብረቱ ለሚዘረፈና ቤቱ ለሚፈርስበት ህዝብ ምንም ያለው ነገር የለም።» የሚለው ደግሞ የእንደሻው ደርሶ አስተያየት ነው።
ኂሩት መለሰ
እሸቴ በቀለ