የመፈንቅለ መንግስት መሪዎቹ ማንነት
ቅዳሜ፣ ጥር 28 2014
ምዕራብ ፍሪቃ ዉስጥ በተደጋጋሚ የተደረገዉ መፍንቅለ መንግስት አፍሪቃ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር በ1970ዎቹ ወደነበረችበት ፖለቲካዊ ቀዉስ የመመለሷ ምልክት ነዉ የሚል አስተያየት አስከትሏል።የመፈንቅለ መንግስቱ መደጋጋም ከ1990ዎቹ ወዲሕ ብልጭ ያለዉ ዴሞክራሲ ሥርዓት የአፍሪቃዉያንን ፍላጎት ከማርካት ይልቅ የብልጣብጥ ፖለቲከኞችን የስልጣን ጥማት ማርከሚያ እንደሆነ ጠቋሚ ነዉ ባዮችም አሉ።የአፍሪቃ ሕብረት፣ ኤኮዋስ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ሆነ ምዕራባዉያን መንግስታት በየሐገሩ የሚደረጉ መፈንቅለ መንግስታትን ከማዉገዝ ባለፍ በምርጫ ስም ሥልጣን የያዙ ግን ሕዝብን የሚበድሉ ፖለቲከኞችን ለመቅጣት የፈለጉ አይመስሉም።የዛሬዉ ትኩረት በፍሪቃ በቅርቡ የተደረጉ ሶስት መፍንቅለ መንግስታት መሪዎችን ማንነትና የከሸፈዉን አንድ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራን እንዴትነት ባጭሩ ይቃኛል።ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።
ያዉ እንደ ሁሉም ወታደር ናቸዉ።በዉጊያ ጦር ስልቱ በሰል፣ጠበቅ፣ ወደ ፖለቲካዊ ዘንበል ያሉ መኮንን።ወታደርነት የቤታቸዉም ነዉ።አባታቸዉ የማሊ የፖሊስ አዛዥ ነበሩ።ኮሎኔል አሲሚ ጎይታ።እንደ ናስር ገዘፍ፣ መለል፣ እንደ ሳንካራ ቀጠን-ረዘም፣ፈጠን ከማለት ይልቅ እንደ መንግስቱ አጠር፣ቀልጠፍ ደግሞ እንደ ሮሊንጊስ ደልደል፣ ፈርጠም፣ ከጺማቸዉ ቸምቸም ያሉ ናቸዉ።
እንደ ቀዳሚዎቻቸዉ የሶሻሊስታዊ አስተሳሰብ አቀንቃኝ፣ የሥርነቀል ለወጥ አራማጅም አይደሉም።ጊዜዉም አይፈቅድላቸዉም።ግን ዘመኑ-የፈቀደዉን ሥርዓት ለማራመድ ብሔረተኝነታቸዉን ከድርድር፣ ዉይይት ጋር አሰባጥረዉ በዘዴ ለመያዝ እያዘገሙ ነዉ።
ነሐሴ 19፣ 2020 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ፕሬዝደንት ኢብራሒም ቡበከር ክይታን እንዳስወገዱ እንደ ብሔረተኛ ማሊዎች «ከእንግዲሕ የመሳሳት መብት የለንም» አሉ።ዋል አደር ብለዉ ደግሞ መፈንቅለ መንግስቱን ካወገዘ፣ማሊን ከአባልነት ካገለለዉ የምዕራብ አፍሪቃ የምጣኔ ሐብት ማሕበረሰብ (ECOWAS) ጋር እየመረረንም እንደራደራለን አሉ።ብዙ አይናገሩም፣ሲናገሩም ከጦር መሪ-አዛዥነት፣ ከፖለቲካኛ ጣጣኔት ይልቅ እንደ እያት ለስለስ፣ ረጋ፣ ቀዘዝ እያሉ ነዉ።
«አንዳዶቹ እርምጃዎች ሕገ-ወጥ፣ኢፍትሐዊ እና ኢሰብአዊ መሆናቸዉ ቢያሳዝነንም፣ የማሊ ሕዝብን ሉዓላዊ ፍላጎትና ኤኮዋስ የተመሰረተበትን መርሕ ለማጣጣም ማሊ ከድርጅቱ ጋር ለመደራደር በሯ ምንግዜም ክፍት ነዉ።ወደ ተረጋጋ፣ ሰላማዊና አስተማማኝ ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓት ለመመለስ ያለን ቁርጠኝነት አይናወጥም።»
ናስር በጄኔራል መሐመድ ነጉብ፣ መንግስቱ በጄኔራል አማን አምዶምና በጄኔራል ተፈሪ በንቲ መጋራጃነት ተከልለዉ ጥቂት ዓመታት እንደገዙት ሁሉ ጎይታም የቀድሞዉን የዓየር ኃይል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ባሕ ንዳዋን በፕሬዝደንትነት አስቀድመዉ የሳሕል በረሐማይቱን፣ የሙዚቃም-የቁርዓን-ሐዲስም፣ ሐገሪቱን ይዘዉሩ ገቡ።
ከወራት በኋላ ግን እንደ ሮሊንግስ በሁለተኛ መፈንቅለ መንግስት ማሊን ሙሉ በሙሉ ጠቀለሉ።ግንቦት 2021።
«ሪፐብሊካዊዉን ሥርዓት በታማኝነትና በቅንነት ለማገልገል ሕገ-መንግስቱን፣ የሽግግር መንግስቱን መመሪያ፣ ሕግን ለማክበርና ለማስከበር፣ለማሊ ሕዝብ ቃል እገባለሁ።»
ምዕራባዉያን ሐገራት አፍቃኒስታንን ኢራቅን፣ ሊቢያን፣ ሶሪያን ሲያፈራርሱ ወደ ሰሜንናና ምዕራብ አፍሪቃ የተሰደደዉ ወይም በአካባቢዉ የተደረጀዉን ታጣቂን በቀጥታ መግጠሙ ስላስፈራቸዉ ከየሐገሩ ጦር ጋር ማጋፈጥን እንደ ጥሩ ስልት ተጠቅመዉበታል።ዛሬም አልተዉትም።ሥልቱን ገቢር ለማድረግም አሲሚ ጎይታን የመሳሰሉ ወጣት መኮንኖችን አሰልጥነዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ፣ ፈረንሳይና የጀርመን ጦር አዋቂዎች ለልዩ ኮማንዶዎች የሚሰጡትን ሥልጠና ጎይታ ተከታትለዋል።አሜሪካኖች ለምዕራብ አፍሪቃ ሐገራት ወጣት የጦር መኮንኖች ከሰጡት ሥልጠና አንዱ የተሰጠዉ ቡርኪና ፋሶ ዉስጥ ነበር።በ2018።በዚሕ ሥልጠና ላይ አሲሚ ጎይታ ከኮናክሪ ከመጣዉ ወጣት መኮንን ጋር ተወዋወቁ።
ምን ተባብለዉ ይሆን? ብቻ ያ ረጅም፣ደልዳለ፣ ኮስታራ፣ ሲሄዲም ሲናገርም ነጠቅ ነጠቅ ባይ ወጣት መኮንን ማማዴይ ዶምቦያ ይባላል።የፈረንሳይ ፈጥኖ ደራሽ ጦር 10 አለቃ ነበር።ኋላ ፈረንሳይን ለቅቆ የትዉልድ ሐገሩ የጊኒ ኮናክሪ ልዩ ኮማንዶ ጦር ባልደረባ፣ ጥቂት ቆይቶ አዛዥም ሆነ።ወደ ጊኒ ከመመለሱ በፊት አፍቃኒስታን፣ ኮት ዲቯር፣ ጅቡቲ፣ማዕከላዊ አፍሪ ሪፐብሊክ፣ እስራኤል፣ቆጵሮስ፣ብሪታንያ ዘምቷል።ወደ ሐገሩ የተመለሰዉ ፕሬዝደንት አልፋ ኮንዴ ባደረጉለት ጥሪ ነዉ ተብሎ በሰፊዉ ሲነገር ነበር።መኮንኑ ግን ኮሎኔልም፣ ጊዚያዊ ፕሬዝደትም፣ አንቱም ከሆኑ በኋላ ባለፈዉ ሕዳር በጭራሽ አሉ።
«አይደለም።ከ10 ዓመት በፊት ወደ ሐገሬ ጊኒ የተመለስኩት በራሴ ዉሳኔ ነዉ።ይሕ ግልፅ መሆን አለበት።ፕሬዝደንት አልፋ ኮንዴና እኔ የተገናኘነዉ ሁለቴ ብቻ ነዉ።የመጀመሪያዉ ብሔራዊ የነፃነት ቀን ሲከበር፣ ጥቅምት 2፣ 2018 ነበር።ሁለተኛዉ በአንድ ለቅሶ ላይ ነበር።»
በ2020 እኒያ ከሁለት ዓመት በፊት ቡርኪና ፋሶ ዉስጥ የተዋወቋቸዉ የማሊ የጦር መኮንን አሲሚ ጎይታ፣ ኢብራሒም ቡበከር ኬይታን ሲያስወግዱ፣ ዶምቦያ እንደ ጎይታ ሁሉ የሙሉ ኮሎኔልነት ማዕረጋቸዉን ጭነዉ የፕሬዝደንት አልፋ ኮንዴን አስተዳደር መላሸቅ ከቅርብ፣ ባማኮ ላይ የሚሆነዉን ደግሞ ከርቀት ግን በንቃት ይከታተሉ ነበር።
ከሩቆቹ የናስር፣ የነመንግስቱ፣ የሮሊንግስን፣ ሳንካራን ዓላማ-ሥልት፣ ከቅርብ የአሲሚ ጎይታን መርሕ-ርምጃን መጋራት አለመጋራታቸዉ በዉል አይታወቅም።ልክ እንደ ሁሉም ግን ወታደር፣ እንደ ሁሉም ሐገር ወዳድ እና ፖለቲካን አነፍናፊ የጦር መኮንን መሆናቸዉን ግን መስከረም 2021 ላይ አረጋገጡ።
በሙስና የተተበተበ፣በአስተዳደር ብሉሸነት የላሸቀ፣በግፍ-ግድያ፣ በከፋፋይ ጭካኔዉ ሕዝብ አንቅሮ የተፋዉን የኮንዴን አስተዳደር አሽቀንጥረዉ ጥለዉ የመሪነቱን ሥልጣን ተቆጣጠሩ።
«ከተወሰነ ዓመታት ወዲሕ ሐገራችን ዉስጥ በተከሰተዉ ማሕበረ-ፖለቲካዊ ዉጥረት ምክንያት ያሉት ተቋማት ተሽመድምደዋል።የጊኒ ሕዝብ እርስ በርሱ እንደ ወንድም መተሳሰቡ ቀርቶ እንደ ጠላት እየተያየ ነዉ።የፖለቲካዊ ጠላት ሆኗል።በሐገራችን ያለዉ የምጣኔ ሐብት ዉድቀትም እርምጃዉን እንድን ወስድ አስገድዶናል።»
የሚመሩት ወታደራዊ ሁንታ የዕርቅና የልማት ብሔራዊ ኮሚቴ (CNRD) መፈንቅለ መንግስቱን ያደረገበትን ምክንያት ሲናገሩ የቀድሞዉ የጋና መሪ ጄሪ ሮሊንግስ «ሕዝቡ በልሒቃኑ የሚረገጥ ከሆነ፣ ለሕዝቡ ነፃነቱን መስጠት ያለበት ጦሩ ነዉ ብለዉ ነበር» ብለዉ ከሁሉም ቀዳሚዎቻቸዉ የሮሊንግስ መርሕ ከልባቸዉ መግባቱን አረጋገጡ።
እኚሕኛዉ በዕድሜ ከሁለቱም በጥቂት ዓመታት ይበልጣሉ።41 ዓመታቸዉ ነዉ ዘንድሮ።በማዕረግ ከሁለቱም ባንድ ደረጃ ያንሳሉ።ሌትናት ኮሎኔል ናቸዉ።በትምሕርት ግን ሁሉቱንም ይበልጣሉ።ከፈረንሳይ ዩኒቨርስቲ በወንጀል ምርመራ የማስተርስ ዲግሪ አላቸዉ።
መካከለኛ ቁመት፣ ደልደል ያለ ትከሻ፣ ጎርበጭ ያለች ቦርጭ፣ ፈታ ያለ ፊት፣ ሰፋ ባለ ጭንቅላት ላይ ጠመም ያለች ቀይ መለዮ ጣል ያደረገ ቡርኪናቤ ካያችሁ እሱ ሌትናንት ኮሎኔል ፓዉል ሔንሪ ዳሚባ ነዉ።
ዝነኛዉን የቡርኪና ፋሶ መሪ ቶማስ ሳንካራን በፈረንሳይና አሜሪካኖች ትብብር አስገድለዉ በ1987 የመሪነቱን ስልጣን የያዙት ብሌስ ኮምፓኦሬ በመጨረሻዎቹ የስልጣን ዘመናቸዉ ከነበሯቸዉ ምርጥ ወጣት አንጋቾች አንዱ እሱ ነበሩ።
ኮምፓኦሬ በ2014 በሕዝባዊ አመፅ ከስልጣን ሲወገዱ ወጣቱ መኮንን የሶስተኛዉ ወታደራዊ ዕዝ ባልደረባ ሆነ።ብዙም ሳይቆዩ ርዕሰ-ከተማ ዋጋዱጉን ጨምሮ አካባቢዉን የሚቆጣጠረዉ ጦር አዛዥ ሆኑ።
የፕሬዝደንት ሮች ማርክ ካቦሬ መንግስት ከአማፂያንና ካሸባሪዎች ጋር የሚደረገዉን ዉጊያ ብዙም ትኩረት አልሰጠዉም በማለት ከሚወቅሱ ወጣት የጦር መኮንኖች አንዱ ነበሩ።ከአማፂያን ጋር የሚዋጉት ወታደሮች ምግብ፣ዉኃና በቂ ጥይት እያጡ ለተደጋጋሚ ጥቃት መጋለጣቸዉንም ሲተቹ ነበር።
አምና ባሳተሙት መፅሐፍ ደግሞ ከአማፂያንና ከአሸባሪዎች ጋር በሚደረገዉ የመንግስት ጦር የደረሰበትን ዉድቀት በመዘርዘራቸዉ ወትሮም በካቦሬ መንግስት ላይ ቅሬታ የቋጠረዉ ሕዝብ ባደባባይ የሚያደርገዉን ተቃዉሞ ይበልጥ አቀጣጥሎታል።
ዳሚባ በ1990ዎቹ ኤኮሌ ፓሪስ የጦር ትምሕርት ቤት ሲማሩ ለስልጠና ከመጡት አንድ ምዕራብ አፍሪቃዊ ፖለቲከኛ ጋር ይተዋወቁ።በእድሜ ገፋ፣ በእዉቀት በሰል፣ ባነጋገር ረቀቅ ያሉት ሰዉዬ አልፋ ኮንዴ ይባላሉ።ፕሬዝደንት ኮንዴ ከስልጣን በተወገዱ በ4ኛዉ ወር ጥር ማብቂያ ዳሚባ ሕዝባዊ ተቃዉሞ ያዳከማቸዉን ፕሬዝደንት ካቦሬን ግፍትረዉ የቡርኪና ፋሶን በትረ-ሥልጣን ጨበጡ።የሚመሩት ሁንታ የቡርኪና ፋሶ ተከላካይና ጠባቂ የአርበኞች ንቅናቄ (MPSR) በፈረንሳይኛ ምሕፃሩ ይባላል።ዓላማዉ?
«የMPSR እርምጃ፣ በበርካታ ጉዳዮችና ፅንፈኞች በሁሉም አቅጣጫዎች በከፈቷቸዉ ጥቃቶች በጣም በተዳከመችዉ ሐገራችን በተከታታይ የተከሰተ ሁኔታ ያስከተለዉ ነዉ።የወቅቱ አሳሳቢ ሁኔታ በጦራችን ላይ ከፍተኛ ጫና አሳርፏል።በዚሕም ምክንያት የብሔራዊ ጦራችን የተለያዩ ክፍሎች የቡርኪናፋሶን አንድነትና ክብር ለማስመለስና ሕዝባችን ያገኛቸዉን ድሎች ለመጠበቅ መግባባት ላይ ደርሷል።»
ሶስቱ የምዕራብ አፍሪቃ ሐገራት በፖለቲካ አመራር፣ የሕዝብ ቁጣን ባስተነፈሰ መፈንቅለ መንግስት፣ በዉጪዉ ዉግዘትም አንድ ሆኑ።ለነገሩ የፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ሲያናጥርባቸዉም አንድ ነበሩ።ማሊ፣ ጊኒ፣ቡርኪና ፋሶ።
ጊኒ ቢሳዉም ባለፈዉ ማክሰኞ መፈንቅለ መንግስት ተሞክሮባት አራተኛ ተቀየጠች አሰኝቶ ነበር።ግን ከሸፈ።መፈንቅለ መንግስቱን በጠነሰሱት ወገኞችና፣ በአክሻፊዉ ጦር መካከል በተደረገ የተኩስ ልዉዉጥ አስራ-አንድ ሰዉ መገደሉ ተረጋግጧል።የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ አንድራጊዉ ቡድን ምንነት የመሪዉ ማንነትም አልታወቀም።
ፕሬዝደንት ዑመሩ ሲሶኮ ኢምባሎ እንዳሉት ግን መፈንቅለ መንግስቱን የመሩና ያስተባበሩት አደንዛዥ ዕፅ ነጋዴዎች ናቸዉ።የቀድሞዋ የፖርቱጋል ቅኝ ተገዢ ጊኒ ቢሳዉ ከሁለት ሚሊዮን ብዙም የማይበልጥ ሕዝብ ያላት ትንሽ ሐገር ናት።አደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች እንደሚያዘወትሯት ይታመናል።ቤተ-መንግስት ለመቆጣጠር ይዳፈራሉ ብሎ ማመን ግን ለሩቅ ታዛቢዎች ግራ አጋቢ ነዉ።
መንፍቅለ-መንግስት አድራጊዎቹና አክሻፊዎቹ ቢሳዎ ዉስጥ ያደረጉትን የተኩስ ልዉዉጥ የታዘበችዉ ጋዜጠኛ ኤፒፋኒያ ፌርናንዴስ እንደምትለዉ ሲቢል የለበሱ ታጣቂዎች ከወታደሮች ጋር ሲታኮሱ ነበር።
«አደንዛዥ ዕፅ ነጋዴዎች የከፈሏቸዉ ነብሰ ገዳዮች ይሁኑ ወይም ወታደሮች በርግጠኝነት መናገር አልችልም።ይሁንና ወታደር የማይመስሉ፣ የሲቢል ልብስ የለበሱ ብዙ ታጣቂዎች ወዲያ ወዲሕ ሲሉ አይቻለሁ።»
ሙከራዉን ያደረገዉ ማንም ይሁንማ መፈንቅለ መንግስት መሆኑን የካደ የለም።
ተደጋጋሚዉን መፈንቅለ መንግሥታቱን የአፍሪቃ ሕብረት፣ ኤኮዋስን የመሳሰሉ አካባቢዊ ማሕበራትና ምዕራባዉያን መንግሥታት አዉግዘዉታል።ይሁንና መፈንቅለ መንግስታቱ በሙስና የተዘፈቁ፣ ምርጫን የሚያጭበረብሩ፣ የሕዝብን ጥያቄ በኃይል የሚደፈልቁ መሪዎችን ያስወገዱ በመሆናቸዉ ከየሐገሩ ሕዝብ ድጋፍ አልተለያቸዉም።
ነጋሽ መሐመድ