1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢራንና የአሜሪካ ፍጥጫ

እሑድ፣ ታኅሣሥ 26 2012

ኢራን የጦር ጄኔራሏን ደም ለመበቀል እየዛተች ነዉ።በባግዳድ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲን ጨምሮ የአሜሪካ የጦር ማዘዢያ ጣቢያና የሲቢል ተቋማት የሚገኙበት አረንጓዴዉ ቀጠና የተባለዉ የባግዳድ መንደር ትናንት ማታ በተከታታይ በሮኬቶች ተመትቷል

https://p.dw.com/p/3Vk1d
Iran Ahvaz Airport Überführung Sarg von Soleimani
ምስል AFP/Fars/H. Mersadi

የዩናይትድ ስቴትስ ጦር የኢራንን ከፍተኛ የጦር ጄኔራልን ጨምሮ የኢራንና የኢራቅን ባለስልጣናት ኢራቅ ዉስጥ መግደሉ መካከለኛዉ ምሥራቅን ከተጨማሪ ብጥብጥና ዉጊያ ይከተዋል የሚለዉ ስጋት እየተጠናከረ ነዉ።የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ባለፈዉ አርብ ከሰው አልባ አዉሮፕላን (ድሮን) በተኮሰዉ ሚሳዬል የገደላቸዉ የኢራን ጦር አዛዥ የሜጀር ጄኔራል ቃሲም ሶለማኒያን አስከሬንን በተለያዩ ከተሞች  የሚኖረዉ የኢራን ሕዝብ እየተሰናበተዉ ነዉ።ኢራን የጦር ጄኔራሏን ደም ለመበቀል እየዛተች ነዉ።በባግዳድ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲን ጨምሮ የአሜሪካ የጦር ማዘዢያ ጣቢያና የሲቢል ተቋማት የሚገኙበት አረንጓዴዉ ቀጠና የተባለዉ የባግዳድ መንደር ትናንት ማታ በተከታታይ በሮኬቶች ተመትቷል።ጥቃቱን ያደረሰዉ ወገን ማንነትም ሆነ በጥቃቱ ስለደረሰዉ ጉዳት በይፋ የተባለ ነገር የለም።የዩናይትድ ስቴትስሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ግን ኢራን አሜሪካንን ለመበቀል የአሜሪካ ተቋማትን ከመታች ጦራቸዉ 52 የተመረጡ የኢራን ታላሚዎችን እንደሚመታ ዝተዋል። የኢራቅ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ደግሞ  ዛሬ የአሜሪካ አምባሳደርን አስጠርቶ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ለጉብኝት የተጋበዙ የኢራን ከፍተኛ የጦር መኮንን እና የራሷ የኢራቅ ባለስልጣናትን ኢራቅ ዉስጥ መግደሏን የኢራቅን ሉዓላዊነት «የተደፋረ፣ የኢራቅና የአሜሪካን ስምምነት በግልፅ የጣሰ» በማለት አዉግዛዋለች።የኢራቅ ፓርላማ በበኩሉ ኢራቅ የሰፈረዉ የአሜሪካ ጦር ሐገሪቱን ጥሎ እንዲወጣ ለመወሰን ከሰዓታት በፊት ዉይይት ጀምሯል።በኢራን ይደገፋል የሚባለዉ ሐሸድ የተባለዉ የኢራቅ የፖለቲካ ፓርቲ የአሜሪካ ጦር ከኢራቅ ለቅቆ እንዲወጣ እና የኢራቅ ወታደሮች የአሜሪካ ጦር ከሰፈረባቸዉ አካባቢዎች እንዲርቁ እያስጠነቀ ነዉ።ኢራቅ የሰፈረዉ የአሜሪካ ጦር እስላማዊ መንግድት ከተባለዉ አሸባሪ ቡድን ጋር የሚያደርገዉን ዉጊያና ለኢራቅ ወታደሮች የሚሰጠዉን ስልጠና አቋርጧል።ኢራቅ ዉስጥ 5200 የአሜሪካ ወታደሮች ሰፍረዋል።

ነጋሽ መሐመድ

ታምራት ዲንሳ